ዕንቁጣጣሽ_እና_የከንፈር ወዳጅ


#ዕንቁጣጣሽ_እና_የከንፈር ወዳጅ
የኢትዮጵያ ሕዝብ በየዓመቱ በታላቅ ስሜት ከሚያከብራቸውና ከሚያዘክራቸው በዓላት አንዱና ተወዳጅ የዘመን መለወጫ በዓል ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ በየዓመቱ በታላቅ ስሜት ከሚያከብራቸውና ከሚያዘክራቸው በዓላት አንዱና ተወዳጅ የዘመን መለወጫ በዓል ነው።
እንደ ዕፅዋት ሁሉ ሰው በመስከረም ላይ በተስፋ ስሜት ይለመልማል። ከቅዱስ ዮሐንስ ዋዜማ ጀምሮ በየቤቱ ጨፌና ቄጠማ
ይጐዘጐዛል። አበባ በሥርዓት እየተዘጋጀ በየቦታውይቀመጣል። በተለይም ልጆች አዳዲስ ልብሳቸውን ለብሰው በደስታ
ይፈነድቃሉ። በአመሻሽ ላይ ችቦ አቀጣጥለው «እዮሐ አበባዬ መስከረም ጠባዬ፣ እዮሐ የበርበሬ ውኃ፣ በሸዋ በጐንደር በትግራይ
በሐረር... ያላችሁ እንዴት ከረማችሁ፣እንኳን ከዘመን ዘመን አሸጋገራችሁ። እንጉርጉሮገባሽ በየአመቱ ያምጣሽ..» እያሉ ወጣት
ወንዶችና ልጃገረዶች (በተለይ በገጠር) ሲዘፍኑና ሲጨፍሩ ያድራሉ። የሚያበሩት ችቦና የሚያነዱት እሳት በግርማ ምሽት ሲንቀለቀል
ውጋገኑ ካገር አገር ከሰፈር ሰፈር ከቦታ ቦታ ይታያል።በዕንቁጣጣሽ መዓልት በተደመረው አድባር ሰፈርተኞች ከርቀትም ከቅርበትም ይሰበሰባሉ። አባቶች ይመርቃሉ። «ዝናሙን ዝናመ
ምሕረት፣ እህሉን እህለ በረከት ያድርግልን፣ ሰላም ይስጠን፣ እህል ይታፈስ፣ ገበሬ ይረስ፣ አራሽ ገበሬውን፣ ሳቢ በሬውን ይባርክ፣
ቁንጫን፣ አንበጣን፣ ትልን... ያጥፋ፣ ምቀኛን ሸረኛን ያጥፋ፣ ወጡ ገቡ ሰቡ ረቡ የሚለውን ሁሉ እግሩን ቄጠማ ዓይኑን ጨለማ
ያድርገው፣ ያርገው፣ ያረገው፣...» ይባባላሉ። እናት አባት ዘመድ አዝማድ በልጆቻቸውና በወዳጅ ዘመዶቻቸው የተበረከተላቸውን
የዕንግጫ ጉንጉን (የአበባ አክሊል) በራሳቸው፣ እንጀራ ማቡኪያቸው፣ በመሶባቸው፣ በወጋግራቸው... ላይ ያስራሉ።
ይህም የአበባ ጉንጉን ተፈትቶና ወጥቶ የሚቃጠለው በመስቀል ደመራ ዕለት እሳቱ (አመዱ) ላይ በመጣል ነው። ተምሳሌቱም
መጥፎ ውቃቢ እንዲቃጠልና በረከትም እንዲቀርብ ታስቦ ነው። ከምሽት ጀምሮ እስከ ንጋት ድረስ በየቤቱ የተዘጋጀው ድግስ
ይበላል፣ ይጠጣል። በነጋታው የዕንቁጣጣሽ ዕለት ልጃገረዶች በሙሬ ወገባቸውን አስረው የሀገር ባህል ወይም ዘመናዊ ቀሚስ
(ልብስ) ለብሰው አሽንክታብ ጨረቃ ጠልሰም፣ ብር ማርዳ (ዶቃ)፣ ድሪ፣ መስቀል፣ የአበባ ጉንጉን በአንገታቸው ላይ አጥልቀው
ዓይናቸውን ተኳኩለው፣ ፀጉራቸውን ጋሜ ቅርፅ ተሰርተው፣ ራሳቸውን በአደስና በአሪቲ የተቀመመ ለጋ ቅቤ ተቀብተው በራስ
ማሰሪያ ሸብ አድርገው፣ የብር መስቀላቸው ላይ አሪቲ (ሪያ) ሰክተው፣ እጅና እግራቸውን እንሶስላ ሞቀው በክንዳቸው አምባር
አስረው፣ ብር አልቦ በእግራቸው፣ ብር ቀለበት በጣታቸው አድርገው፣ ሎሚ በጉንፋቸው ይዘው አሥር አሥር በመሆን ክብ ይሰሩና
በእጆቻቸው ጭንና ጭናቸውን መሬቱን እየተመተሙ ተንበርክከውና ቁጢጥ ብለው ድሪያይጫወታሉ።
በዕንቁጣጣሽ ዕለት ልጃገረዶች ከከንፈር ወዳጆቻቸው ጐን ለጐን በመሆን አራት የጨዋታ ዓይነቶችን በጭፈራ ያሰማሉ።
በመጀመሪያ አሥር አሥር ይሆኑና በአራት ክብ ተከፋፍለው አርባ ልጃገረዶች ተንበርክከው መሬቱን እየተመተሙ «ዛጐሌ»
የተሰኘውን ጨዋታ ያሰማሉ። «ዛጐሌ ጌታውሎሌ አንደኛ ማር ይተኛ በሰውየው መንገድ ሰውየው ዘለቀ እይኔ እንደበረዶውኃ ሆኖ
አለቀ። ቶፋ ቶፋዬ ንፍሮ ቀቅዬ ብላ ብለው ዛሬስ አመዶ ሊማታ ነው» ሲል ወንዶች ደግሞ ለዕንቁጣጣሽ የተገዛላቸውን እጀ ጠባብ፣
ኮት፣ ተፈሪ ሱሪ ባትተ ሁለት... ለብሰው፣ ቀጭን ኩታ ደርበው፣ አሞግረው የያዙትን ዱላ አስቀምጠው የራሳቸውን ክብ ሰርተው ወደ
ልጃገረዶቹ በመጠጋት የወንዶቹ አቀንቃኝ የሚያፈቅራትን ልጃገረድ በዓይኑ እየቃኘ፣ የሚከተለውን ይላል
«እዩት እዚያ ላይ ግራሩ መንታ፣
ዓይንሽ ያበራል እንደሎሚታ
ተሎሚታውም ያንቺ ዓይን ይበልጣል
እንደመስታወት ያንጠባርቃል።
ዐደይ ዐበባ የመስከረሙ እነጉብሌ ወዴት ከረሙ
ዐደይ አበባ የሶሪ ላባ እፍ እፍ በይን እንደ ገለባ...» እያለ ያሞግሳታል።
የተወደደችዋ ልጃገረድም ከወጣቱ ላይ የእርሷም ቀልብ ያረፈበት መሆኑን ካረጋገጠች በተራዋ፣ «እዩት እዚያ ላይ ከግራሩ ሥር
ድስት ተጥዷል ቋንጣና ምስር
ቋንጣው ይቅርና ይምጣ ምስሩ
አንተን አሰኘኝ የፍቅሬ ዛሩ።
ዐደይ ፈነዳ መስከረም ነጋ፣
እንግዲህ ልቤባንተ ላይይርጋ» ትለዋለች።
ልጃገረዶቹ እንደመሸሽ፣ ወንዶቹ ደግሞ እንደመከተል እያሉ ይቀራረባሉ። ልጃገረዶች የወንዶችን መጠጋት ሲያዩ፣«ኖሩ፣ኖሩ» ይላሉ።
ወንዶቹም «ከበሩ ከበሩ» ብለው ይመልሳሉ።
ከዚያም አንዷ ወጣት ወደምትፈልገው ጐረምሳ ዓይኗን እየወረወረች፣ «ጠላ ጠጣ የኔ ቀበጥባጣ...» ትላለች።
የተወደደውም «ጠጥቻለሁ፣ ላይሽ መጥቻለሁ» ብሎ ይመልሳል።
«ብታየኝ አንደዜሳመኝ፣» ብላ ታስቅበታለች።
«ብስምሽ ይቆጣልባልሽ» ብሎ በተራው ያስቃቸዋል።
ወጣቷም «ባሉ ባሉ እርሱ የት አይቶ፣ ሲቆፍር ተደፍቶ» ትላለች።
«ሲቆፍር ምቺው በድግር፣» ይላታል። «ድግር መና ያፋታልና ገና፣» ትላለች።
«ቢያፋታሽ፣ እኔ አለሁልሽ፣ ውሽማ ይብላ እንጂ በቅቤ ጠለላ ባልማ ምን ይላል ደረቁን ቢበላ፣ ያንቺማ ወዳጅ የኮራሽበት ከዳገት
ቀረ እንደ በሬ እበት» ይላታል ሊሰማት የፈለገው ልጅ።
ያገቡ ባልና ሚስቶች ዓይነት ጨዋታ ሲጨዋወቱ ይቆዩና ሁሉም ጐረምሳ የፈለጋትን ልጅ አባርሮ ይይዝና በነጠላው አከናንቦ
ይሰማታል። ተሳሚዋ በቃ እስክታገባ ድረስ የከንፈር ወዳጁ ሆነች ማለት ነው። ልጃገረዶቹ አንሳምም ብለው ስለሚግደረደሩ በስንት
ትግልና ጉልበት ነው የሚሳሙት። የሳመ ወጣት ሎሚ፣ድሪ፣ አልቦ፣ ብር፣ ማርዳ... ይሰጣል። እነዚህን ጌጣጌጦች አስቀድሞ ነው
የሚያዘጋጀው። የዕንቁጣጣሽ ዕለት ልጃገረድ ደፍሮ ያልሳመ ወጣት በፈሪነቱ ሲሳቅበት ይከርማል። ከዚያ«ፍየሌን ነብር በላት»
የተባለው ሁለተኛው የጨዋታ ዓይነት ይቀጥላል።
የሳመው ወጣት እንደነብር ተመስሎ ይደበቃል። የሳማት ወይም ሊስማት የከጀላት ልጃገረድ ደግሞ በፍየል ግልገል እንድትመስል
ትደረግና ተሸፋፍና ትቀመጣለች። ከዚያም ነብሩ እያጉረመረመ ይመጣል። ከዚያተው አያ ነብሮ ግልገሌን አትውሰዳት፣ አትውሰዳት፣
እያሉ ሴቶቹም ይጮሁበታል። እርሱ ግን እምቢ አሻፈረኝ ብሎ ከግልገሏ ላይ ዘልሎ ይከመርባታል። ይስማታል። ልጆቹ ዋይዋይ
እያሉ የጩኸት ድምፅ ያሰሙና እያጨበጨቡና እየጨፈሩ፣ «ፍየሌን ነብር በላት
ለቅዱስ ዮሐንስ አረዳት
ለገና ብዬ ስደለድላት
እንግጫዬ ደነፋ ጋሻውን ደፋ እንግጫዬ
ሰሌን ልደቁሰው ኩሌን እንግጫዬ
የወሩ ዘረዘረ ዳርዳሩ እንጉብሌሊሄዱ ናቸው
ተጫነላቸው ፈረስ በቅሏቸው፣
ያው አማረበት ዓይነርግባቸው።»
በዕለተ ዕንቁጣጣሽ በተለይ የልጃገረዶች ጭፈራና ጨዋታ እየደራና እየሞቀ ይሄዳል። ተቀባዮቹ ያደይ እያሉ የሚከተለውን
ይዘምራሉ።
«ዕንቁጣጣሽ ያደይ ዕንቁጣጣሽ
በየት ገባና ቆነጠጠ ቆነጠጠኝ ልቤን ልቤን ኩላሊቴን
እናቴን ጥሩ መድኃኒቴን
እሙ ካልመጣች መቸም አልድን
እርሷን ካጣችሁ መቀነቷን
አበባሽ አደይ አበባዬ...»
ከዚያም ወንዶች «እንክሾ እንክሾ አባ ወልክሾ» የተሰኘውን ሶስተኛ ዘፈን እየጨፈሩ ወደልጃገረዶች ይጠጋሉ። በተለይ አንድ ወጣት
ፍላጐት ያለው በአባ ጅቦ ተመስሎ እያነከሰ ወደልጃገረዶች መኸል ይገባና አውውው... ብሎ ይጮሀል። «ምነው አባ ጅቦ» ይሉታል
ልጃገረዶቹ ከመኸላችሁ አንዷን ጥፍጥሬ (ወጣት ማለት ነው) ልጅ ትሰጡኝ ዘንድ ብዬ ነው ይላል።አባ ጅቦ ሐሙስ ተመለስ«
ይሉታል ልጃገረዶች። ጅቡም ሐሙስ ሐሙስ ቶሎ ድረስ እያለና እያነከሰ ወደጫካው ይሄዳል። ከዚያ ይሰነባብትና (ቆይቶ) እንደገና
አውውው... ብሎ እየጮኸ ሲመጣ የሚፈልጋትን ልጅ ጥለውለት ይሸሻሉ። ይሮጣሉ። ጅቡም ወጣቷን ተከታትሎ ይበላታል ማለት
ነው፣ ይስማታል። የተበታተኑ ልጃገረዶች እንደገና ይሰበስቡና አራተኛውን የጨዋታ ዓይነት » ሸንበቆና ሸንበቆ ይጫወታሉ።
ሸንበቅና ሸንበቆ ሲወጣ አየሁ ተጣብቆ አትንጫጩ ልጆቼ እመጣለሁ ሰንብቼ ቋንጣ በለስ በልቼ ቋንጣ በለስ ይሉሻል
ይኸውናቅጠሉ ቀጥቅጭና ቅመሺው ወሮታውን ከቻልሺው ለዚህ ለዚህ ወሮታ አልጋ ሰርቶ መኝታ መሬት ወርዶ ጫጫታ አባ
አበሻው ወንድሜ እኔ ውሃ ስቀዳ እርሱ ጥጃ ሲነዳ ገረፈችው በሳማ ያጤ ወንበር ሳይሰማ አጤ ወንበር ንጉሱ እያስቀዱ ሲቀምሱ
እየዞሩ ሲገምሱ... ዛጐሌ ጌታውሎሌ አነደኛ ማር ይተኛ...» ይላሉ። በዚህ ሁኔታ ሲጨፍሩና ሲሳሳሙ ይውላሉ። የከንፈር ወዳጅ
ያበጃሉ። በከተማው የእንቁጣጣሽ ባህል ደግሞ አበባዬ ሆይ ባልንጀሮቼ.. እያሉ ገንዘብ ይለምናሉ፣ ሲቀበሉም ከብረው ይቆዩን...
ይላሉ። ገጠሬዎች ግን ይጫወታሉ እንጂ አይለምኑም። ambachew44

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

አይሰው

እቴጌ ጣይቱ ብጡል (ብርሀን ዘ ኢትዮጵያ)

ደራሲ ዶ/ር ሀዲስ ዓለማየሁ (ሃዲስ ኣለማየሁ)