ደራሲ ዶ/ር ሀዲስ ዓለማየሁ (ሃዲስ ኣለማየሁ)

ደራሲ ዶ/ር ሀዲስ ዓለማየሁ (ሃዲስ ኣለማየሁ)
ደራሲ ዶ/ር ሀዲስ ዓለማየሁ (ሃዲስ ኣለማየሁ) ከአባታቸው
ከቄስ ዓለማየሁ ሰለሞን እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ደስታ
ዓለሙ በ ደብረ ማርቆስ አውራጃ
በጎዛመን ወረዳ በእንጾር ኪዳነ ምኅረት ቀበሌ በጥቅምት 7
ቀን 1902ዓ.ም. ተወለዱ። ገና
በጨቅላ እድሜያቸው በቤተ ክርስቲያን የሚሰጠውን
ትምህርት በቤተሰባቸው አጠገብና ባባታቸው አገር ደብረ-
ኤልያስ ሄደው የግእዝ ትምሕርት ቤት ቅኔ ተቀኝተዋል።
የቤተክርስቲያን ስርዐታትንና መንፈሳዊ ትምህርትን በጎጃም
ገዳማት በደብረ-ኤልያስ፣ በደብረ-ወርቅና በዲማ ከቀሰሙ
በኋላ ወደ በ1918 ዓ.ም አዲስ አበባ በመሄድ በስዊድን
ሚሽነሪ ትምህርት ቤት በኋላም በራስ ተፈሪ መኮንን
ትምህርት ቤት
ትምህርታቸውን ተከታተሉ። ለትንሽ ጊዜ በአስተማሪነት ሥራ
ተሰማርተው እንዳገለገሉ የፋሽስት ጣሊያን ወረራ ተከሰተ።
የኢጣልያ ወረራ ሲከሰት ከልዑል ራስ ዕምሩ ኃይለሥላሴ
ጦር ጋር በምዕራብ ኢትዮጵያ በአርበኝነት
ሲዋጉ ቆይተው በመያዛቸው ጣሊያን ከልዑል ራስ ዕምሩ
ጋር በግዞት ለሰባት ዓመታት በፖንዞ ደሴት ና በሊፓሪ ደሴት
ታስረው ቆይተዋል። ከዚያም የተባባሪ ኃያላት ወታደሮች
በ1935 ዓ.ም.
ሲያስመልጧቸው በተመለሱበት ጊዜ በትምህርታቸው
እንደገና በኦክስፎርድ ከገፉ በኋላ በተለያዩ የ መንግስት
ተቋማት በተለይም በ ትምህርት ሚኒስቴር ለረጅም ጊዜ
አገልግለዋል።
1936 - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሠራተኛ
1937 - 1938 - የኢትዮጵያ ቆንሱል በኢየሩሳሌም
1938 - በ International
Telecommunications Conference አትላንቲክ ከተማ
፣ ኒው ጄርዚ ወኪል
1938- 1942 - በተባበሩት መንግሥታት ቢሮ
ኒውዮርክ ሠራተኛ
1942- 1948 - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዳይረክተርና
ምክትል
1948- 1952 - የተባባሩት መንግሥታት ድርጅት
የኢትዮጵያ አምባሰደር
1952 - የትምህርት ሚኒስትር
1952- 1957 - የኢትዮጵያ አምባሰደር ወደ እንግሊዝ
ና ሆላንድ
1957- 1958 - የልማት ሚኒስትር
1960 - 1966 - ሴናቶር
ሀዲስ ዓለማየሁ በርካታ የስነጽሑፍ ሥራዋችን
አበርክተዋል። ከነዚህም ውስጥ ታላቅ አድናቆትንና
እውቅናን ያተረፈው ሥራቸው ፍቅር እስከ መቃብር
( 1958 ) በሁለት የተለያዩ መደቦች ውስጥ የሚገኙ
የሁለት ሰዎች የፍቅር ታሪክ ላይ ሲያተኩር፤ በጊዜው
የነበረውን ወግና ልማድ ይገልጻል። እንዲሁም በ1970
ወንጀለኛው ዳኛ በ 1980 ደግሞ ስለ ማህበራዊ ጉዳዮችና
ስለ ጣሊያን ውርስ የሚዳስሰውን የልም እዣት የተሰኙትን
ልብ ወለድ ታሪኮች ለንባብ አቅርባዋል።
ከዚህ ባሻገር:
የአበሻና የወደኋላ ጋብቻ - ተውኔት
ተረት ተረት የመሰረት ትዝታ የተሰኙ ጽሁፎችና የሌሎች
በርካታ ሥራዎች ባለቤት ናቸው።
ሀዲስ ዓለማየሁ በኢትዮጵያ የስነ ጽሑፍ ዕድገት ከፍተኛ
አስተዋጽዖ በማበርከታቸው ከ አዲስ አበባ
ዩኒቨርሲቲ የዶክቶርነት ማዕረግ ተሰጥቷቸዋል። ደራሲው
በኅዳር 26 ቀን 1996 ዓ.ም. በ94
ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
#የኋላው_ከሌለ_የለም_የፊቱ
ከዶቼዌሌ ድህረገጽ የተቀነጨበ...
«በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዉስጥ ብዙ ተራማጆችን ብዙ
አስተሳሰብን የፈጠረዉ እስካሁን ድረስ መነጋገርያ ሆኖ
የዘለቀዉ ፍቅር እስከመቃብር የተሰኘዉ 1948 ዓ.ም የፃፉት
መጽሐፋቸዉ ነዉ። ይህ መጽሐፍ ፍቅርን በዉስጡ ይዞ
ፊዉዳል ኢትዮጵያ ምን ዓይነት ስርዓት እንደነበረና ወደፊት
የምትመጣዋ ኢትዮጵያ ደግሞ እንዴት መገንባት
እንዳለባትም የሚጠቁም መጽሐፍ ነዉ ተብሎ ነዉ በብዙ
ምሑራን የሚዘረዘረዉ» ጋዜጠኛና ደራሲ ጥበቡ በለጠ ስለ
ክቡር ዶ/ር ሀዲስ አለማየሁ፤ የተናገርነዉን ነበር ።
የፍቅር እስከ መቃብር ታሪክ ሲነበብ፣ አንባቢውን በፍቅር
ወጀብ አላግቶ፣ የፍቅር እስረኛ የሚያደርግ ተአምረኛ
መጽሐፍ ነው ይለዋል ጋዜጠኛ ጥበቡ። ሙዚቃና ቴዲ
አፍሮም በዚህ ልብ ወለድ በፍቅር ወድቆ በግሩም ዜማ
ደራሲውን ብሎም ፍቅር እስከ
መቃብርን በራድዮ የተረከዉን አርቲስት ወጋየሁ ንጋቱን «ማር
እስከ ጧፍ" በሚለዉ ዜማዉ ሕያዉ ማድረጉ የቅርብ ጊዜ
ትዝታ ነው።
በእንጊሊዘኛ የተተረጎመዉ የታላቁ ደራሲ የሀዲስ አለማየሁ
ፍቅር እስከ መቃብር አብዛኞችን በፍቅር የጣለ ልብወለድ
መጽሐፍ ነው። ከዝያ በዘለለ በኢትዮጵያ የትምህርት
ተቋማት በተለይ ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-
ጽሑፍ ዲፓርትመንት ውስጥ ላለፉት 50ዓመታት የጥናትና
ምርምር ጽሁፎች ሲሰሩበት የኖረ መጽሐፍ ነው። የዩንቨርስቲ
ተማሪዎች የመመረቅያ
ጽሑፋቸዉን ሰርተዉበታል፡ የሥነ/ጽሑፍ ተመራማሪዎች
ፍቅር እስከ መቃብርን በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተንተርሰው
ጥናት ሠርተዋል። ዘመን አይሽሬውን ብዕረኛ ፤ክቡር ዶ/ር
ሀዲስ አለማየሁን ለተከታታይ ዓመታት ለሦስት ጊዜ ቃለ
መጠይቅ ያደረገላቸዉ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ ሀዲስ
አለማየሁ ለቃለ-ምልልስ ብዙም ክፍት እንዳልነበሩ
ያስታዉሳል። ከብዙዎች ጥያቄ ቢቀርብላቸዉም እንቢታቸዉን
ቀስ ብለዉ ነበር የሚናገሩት ሲል ይገልጻቸዋል። ነገር ግን
ይላል ደራሲ ሀዲስ አለማየሁ በኢትዮጵያ የሥነ-ጽሑፍ፤
የዲፕሎማቲክ ሕይወት እንዲሁም የአርበኝነት እና በፖለቲካ
ሕይወት ዉስጥ በጣም ግዙፍ ቦታ የሚሰጣቸዉ ናቸዉ።
ምክንያቱም ይላል ጋዜጠኛ ጥበቡ በመቀጠል፤
«ምክንያቱም እኚህ ሰዉ በኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ ሕይወት
ዉስጥ ብቅ ያሉት ከኢጣሊያ ወረራ በፊት ነዉ። ከ1928
ዓ.ም በፊት ከተወለዱበትና ከአደጉበት ከደብረማርቆስ
አካባቢ እንዶዳም ኪዳነምህረት፤ ዲማ ጊዮርጊስ አካባቢ
ነዉ የተማሩት። ሀዲስ አለማየሁ የተወለዱበትን ዓመት
መቼ እንደሆን እርግጠኛ እንዳልሆኑ ይናገራሉ። ነገር ግን
1902 ዓ.ም ወይም 1906 ዓ.ም ዓመተ ምህረት ሊሆን
አንደሚችል ይናገራሉ። ዲማ ጊዮርጊስ ቅኔን ቆጥረዋል፤
በኋላም ወደ አዲስ አበባ መጥተዉ ተፈሪ መኮንን ትምህርት
ቤት በዘመኑ የነበረዉን ትምህርት ማለትም እስከ ስድስተኛ
ክፍል ተምረዉ ጨርሰዋል። እስከ ስድስተኛ ክፍል
ትምህርት ማለት በዘመኑ ትልቅ ትምህርት ማለት ነበር።
ከዝያ በኋላም ወደ ዳንግላ ወደ ጎጃም መጥተዉ ሥራ
የጀመሩበት ነበር ። እዝያም ትህርት ቤት እንዳቋቋሙ ነዉ
ታሪካቸዉ የሚናገረዉ።
በዕውቀቱ ስዩም በ1985 ኢትዮጵያዊነት መጽሔት ላይ ስለ
ክቡር ዶ/ር ሃዲስ ኣለማየሁ የፃፈውን ሸገር ብሎግ ላይ
እንዲህ ሰፍሮ አገኝተነዋል እነሆ ተጋበዙልን።
አቶ ሀዲስ አለማየሁ ስለ ኢትዮጵያ ሁኔታ
የሰነዘሩዋቸው አስተያየቶች
አቶ ሀዲስ አለማየሁ በልቦለድ ፀሀፊነታቸው የተጋረደ
የፖለቲካ ሰብእና ነበራቸው። በተለያየ ጊዜ ስለ ኢትዮጵያ
ሁኔታ የሰነዘሩዋቸው አስተያየቶች እንደ ደረቅ ትንቢት
የሚቆጠሩ ነበሩ።
ለዛሬ መጋቢት 19 1985 አመተ
ምህረት ባዲሳባ ዩንቨርሲቲ ካቀረቡት ንግግር የሚከተለውን
ለመቀንጨብ ወደድሁ። በጥሞና አንብበን በሰከነ መንፈስ
እንወያይበት።
የንግግሩ ቅንጫቢ ይሄው-
“…አሁን በይፋ የሚደረጉትን አንዳንድ ነገሮች ስመለከትና
እንዲሁም በይፋ በየመድረኩ
የሚደረጉትን አንዳንድ ነገሮችን ስሰማ በኔ አስተያየት
የኢትዮጵያ ህልውና አስጊ ሁኔታ ላይ ቆሞ የሚገኝ
ይመስለኛል። ይህን የምልበት ምክንያት ዛሬ ራሳቸውን በልዩ
ልዩ የነፃነት ግንባር የሰየሙ ቡድኖች “የህዝቦች የራስን
እድል – እስከነፃነት
በራሳቸው የመወሰን መብት ” ለተባለው ድንጋጌ የተሳሳተ
ትርጓዋሜ ሰጥተው የራሳቸው ነፃ መንግስት
እንዲኖራቸው..ያሰቡት ሀሳብ ፍፃሜ የሚያገኝ ከሆነ ይህ
ከኢትዮጵያ ህልውና ጋር የማይጣጣም ሆኖ ስለሚታየኝ
ነው።
“የህዝቦች የራሳቸውን እድል እስከ
ነፃነት..”የሚለው ድንጋጌ በነፃነት ግንባሮች የተሰጠው
ትርጉዋሜ የተሳሳተ ከመሆኑም ሌላ እንደ ኢትዮጵያ ብዙ
ነገዶችና በነገዶችም ውስጥም ብዙ ጎሳዎችና ንኡስ
ጎሳዎች በሚኖሩባት አገር በቃል የሚነገረውን ያክል
በግብር መተርጎሙ ቀላል ሳይሆን ሊወጡት የማይቻል
ገደል ነው።
በተጎራባች አገሮች መካከል ያለው የወሰን የወንዝ ክፍፍል
የጎሳዎችና የንኡስ ጎሳዎች አስተዳደር የሚያስነሱት
ዘልአለማዊ ሁከትና
ጦርነት ለሀገርና ለልማት ሊውል የሚገባውን ሀብትና
ጉልበት እየበላ ሁልጊዜ አደህይቶና ሰላምን አሳጥቶ የሚኖር
በመሆኑ የሚሸሹት እንጂ እንኩዋንስ ሊይዙት የሚቀርቡት
አይደለም።

ይህ ንኡስ አንቀፅ ተፈፃሚነቱ ለሽግግር መንግስቱ እድሜ
ብቻ እስከሆነ ድረስ የሚፈጥረው ችግር ቢኖር ጎልቶ ላይታይ
ይችል ይሆናል።
አሁን ወደሚረቀቀው ቀዋሚ ህገመንግስት የሚተላለፍ ከሆነ
ግን በየነገዳቸው ህዝብ ላይ ስልጣን መያዝ ለሚፈልጉ ሁሉ
በር ከፋች ሁኖ መጨረሻው ለማይታይ ሁከትና ጦርነት
መንስዔ ሊሆን ስለሚችል ህገመንግስቱን ለማርቀቅ
ሀላፊነት የተጣለባቸው ክፍሎች አጥብቀው ሊያስቡበት
የሚገባ ይመስለኛል። ተመሳሳይ ህገመንግስት
በነበሩዋቸው አገሮች በሶቭየት ህብረትና በዩጎዝላቪያ ዛሬ
የደረሰውም ትምህርት ሊሆነን ይገባል”
ክቡር ዶ/ር ሃዲስ ከዛሬ ሀያ ስድስት አመት በፊት
የተናገሩት ዘንድሮ ቁልጭ ብሎ እየታየ ነው ነገሮችንም
በብሄር እና በዘር ደረጃ ብቻ ማየት ካልተውን ነገሮች ወደ
ባሰ ደረጃ መሄዳቸው የማይቀር ነው። ከምንም ነገር በፊት
ሰብአዊነት ይቅደም።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

አይሰው

እቴጌ ጣይቱ ብጡል (ብርሀን ዘ ኢትዮጵያ)