ወርቃማ አፈር

ወርቃማው ዐፈር ⚜


















በአጼ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት በርካታ ተጓዦች ሃይማኖታቸውን ለማስፋፋት፣ ለጉብኝት እና ለስለላ ወደ ኢትዮጵያ ይመላለሱ ነበር፡፡ እነዚህ ተጓዦች ባብዛኛው ይመጡ የነበረው ከአውሮፓ አህጉር ሲሆን በመላው የኢትዮጵያ ምድርም ተዟዙረው ይጎበኙ ነበር፡፡

ከሰሜን ጫፍ ተነስተው እስከ ደቡብ ጫፍ ድረስ ከተጓዙ በኋላ እንደገና ደሞ ከምስራቅ ጫፍ ይጀምሩና እስከ ምዕራብ ጫፍ ድረስ ይጓዙ ነበር፡፡ በጉዞአቸውም የተራሮችን ጫፍ ይረግጡ ነበር፡፡ ወንዞችንም ይሻገሩ ነበር፡፡ በሸለቆዎች መሃል ለመሃልም ሰንጥቀው ያልፉ ነበር፡፡ በረሃዎችንም ያቋርጡ ነበር፡፡ እንዲህ እንዲህ እያሉ ጎብኝተው ሲያበቁ ያዩትን መልከዓ ምድሮች በሙሉ በካርታ አዘጋጅተው ለአጼ ቴዎድሮስ በስጦታ አስረከቡ፡፡

አጼ ቴዎድሮስም ካርታውን ከመረመሩ በኋላ “ካርታው እጅግ በጣም ጥሩ ነው፡፡ በዚህ ካርታ አማካኝነት የአባይን መነሻ ማወቅ እንችላለን፡፡ በዚህ ካርታ አማካኝነት የተራሮቻችንን ጫፍ ምን ያህል ከፍታ እዳለው መገንዘብ እንችላለን፡፡ የአገራችን ወንዞች የት የት እንደሚገኙ በቀላሉ መረዳት እንችላለን፡፡ ስለዚህ በሥራችሁ በጣም ተደስተናል፡፡ መልካም ሥራ ነው ያከናወናችሁት፡፡ ስለዚህ በጣም ተደስቼባችኋሉ፡፡” ብለው ለጎብኚዎች ትልቅ ግብዣ አደረጉላቸው፡፡ በግብዣው ወቅት እንጀራውና ወጡ፣ ጠላውና ጠጁ፣ ጮማው ሁሉ ሳይቀር የተትረፈረፈ ነበር፡፡ ግብዣው ካበቃ በኋላ ንጉሱ ለአውሮፓውያኑ የወርቅና የብር ስጦታም አበረከቱላቸው፡፡ ጎብኚዎችም በጣም ተደሰቱ፡፡

ይህ ከሆነ ከጥቂት ቀናት በኋላ ተጓዦቹ ወደ አገራቸው ለመመለስ ተነሱ፡፡ አጼ ቴዎድሮስም በርከት ያሉ አሽከሮቻቸውን ጠርተው “በሉ እነዚህን ተጓዦች መርከቡ ድረስ ሸኟቸው፡፡” ሲሉ ትዕዛዝ ሰጡ፡፡ አሽከሮችም እሺ ብለው የተጓዦችን ሻንጣዎች ተሸክመው ወደቡ ድረስ አድርሰው መርከቡ ላይም ጫኑላቸው፡፡ ነገር ግን ተጓዦቹ መርከቡ ላይ ሊወጡ ሲሉ፣ ከአሽከሮቹ መሃል አንደኛው መርከቡ ላይ እንዳይወጡ አገዳቸው፡፡ አገዳቸውናም ጫማዎቻቸውን እንዲያወልቁ ጠየቃቸው፡፡እንግዶችም ነገሩ እንግዳ ቢሆንባቸውም የተጠየቁትን ለመፈጸም አላንገራገሩም፡፡ አሽከሩም ጫማዎቻቸውን ከተቀበለ በኋላ እያንዳንዱን ጫማ በጥንቃቄ ያጥብ ጀመር፡፡ አጥቦ ካበቃ በኋላም የሁሉንም ጫማ መለሰላቸው፡፡ በዚህ አሽከር ድርጊት በጣም የተገረሙት ተጓዦች ለምን ጫማዎቸውን እንዳጠበ ጠየቁት፡፡

እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፡፡ “እናንተ ሁላችሁም የኢትዮጵያ ክፍል ተዘዋውራችሁ አይታችኋል፡፡ በዚህም ምክንያት አገራችን እንዴት ያለች ውብ እንደሆነች ተረድታችኋል፡፡ እኛም አገራችንን በጣም እንደምንወድ አውቃችኋል፡፡ እኛ አዝርዕቶቻችንን የምናበቅለው፣ ምግባችንን የምናሰናዳው በአገራችን በኢትዮጵያ ዐፈር እንደሆን ሳትገነዘቡ እንዳልቀራችሁ እንገምታለን፡፡ የሞቱ ወገኖቻችን የምንቀብረው በዚህቺው በኢትዮጵያ ዐፈር ውስጥ ነው፡፡ የምትመለከቱት የእግር መንገድ ፈለጉን ያገኘው በቤተሰቦችን የእግር ዳናዎች የተነሳ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ዐፈር አባታችንም እናታችንም ነው፡፡ ወርቅና ብር ልንሰጣችሁ እንችላለን፡፡ ዐፈራችንን ግን በጫማችሁ እንኳን ይዛችሁ እንድትሄዱ አንፈቅድም፡፡ እናም በዚህ ምክንያት ነው ጫማችሁን ሙልጭ አድርጌ እንዳጥብ ንጉሡ ያዘዙኝ” አለና ወደ መርከቡ እንደወጡ ከመንገዱ ገለል አለላቸው፡

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

አይሰው

እቴጌ ጣይቱ ብጡል (ብርሀን ዘ ኢትዮጵያ)