አማርኛ

 የአማርኛ ፊደላት (ሆሄያት) ፀጋዎች
* በዚህ ዓለም ስለራስህ ከአንተ በላይ የሚያውቅ የለም!
-
ከድሮ አስተሳሰብ ጋር ተቸንክረው የቀሩ ቆሞ ቀሮች፦
'ስለራስህ ሰዎች ይናገሩልህ እንጂ አንተ ዝም በል' አይነት ይትበሀል እያስፋፉ፤ አባባሉ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ ተንሰራፍቷል።

ሆኖም በአፍአዊ ደረጃ (ስለአንተ ሰው ይናገር) በሰፊው ቢናኝም፤ በተግባር ሲገለጥ በእያንዳንዱ ሰው ንግግር ውስጥ 'ከእኛ' ይልቅ 'እኔ' ጎልቶ መውጣቱ፤ ተቀባይነቱን ብላሽ/ ፉርሽ ያደርገዋል።

በእርግጥም 'ሰዎች ስለአንተ ይናገሩልህ' የሚለው አገላለፅ ትህትናን ያዘለ ቢመስልም ስሁትና የሰዎችን ግለ _ ታሪክ የመቅበር አሉታዊ አቅሙ ከፍተኛ ነው።

* ማነው ከአንተ ጋር ከልጅነትህ ጀምሮ አብሮ የተንከራተተ?
* ማነው ከአንተ ጋር አቀበት ቧጥጦ ቁልቁለት ወርዶ የተፍገመገመ?
* ማነው በውስጥህ ያመቅኸውን ዕንባና ሰቆቃ _ ብሶትና ምሬት የተጋራ?
* ለምሳሌ፦ እንደ Misbah Kedir በወያኔ እስር ቤት አሳር ፍዳህን ስታይ፤ ማነው ከአንተ ጋር 'ቶርቸሩን' የቀመሰ?
ማነው እንደ አንዷለም አራጌ በእስር ቤት ውስጥ አብሮህ ፊቱ የከሰለ? እኮ ማነው ስላንተ ከአንተ በላይ ምስክር?
* ራስህን ካልወደድህ እመነኝ ቤተሰብህን ሀገርህንም ሆነ የሰውን ዘር አትወድም።
(በራስ ወዳድነትና ራስን በመውደድ መሀከል ሰፊ ልዩነት አለ።)

በእኔ ምልከታ ሰዎች ከበርካታ መልካም ሥራዎችህ መሀከል መጥፎውን መዞ የማጉላት ባህሪ ስለተጠናወታቸው ስላንተ እንዲናገሩልህ መጠበቅ፤ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ዐይን የሌለው ጥቁር ድመት የመፈለግ ያህል አዳጋች ይመስለኛል። በተቻለ አቅም ለህሊናህና ለፈጣሪህ ታማኝ ሁን እንጂ ስለአንተማ ተናገር!

አንድ መሥሪያ ቤት ለመወዳደር ስታመለክት፦ CV (Curriculum Vitae) ከአንተ ውጪ ማን ሊያዘጋጅልህ ይችላል? ቃለመጠይቅ ላይስ ስላንተ ማን ይናገራል? ውሀ አጣጭህን ስትፈልግ (በአማጭ ረማጭ) ካልሆነ፤ ስላንተ ማን ይጀነጅንልሀል? የላክኸው ሰው ለትዳር የከጀልካትን ሔዋን 'አናግርልኝ' ብትለው፤ ለራሱ ሊያደርጋት እንደማይችል ምን ዋስትና አለህ? (ለዚህ ተጨባጭ መጥፎ ማስረጃ ላቀርብ እችላለሁ) ስለሆነም ስለራስህ በአግባቡ ግለጥ!

ስለማንኛውም ሰው የህይወት ውጣ ውረድና ገቢር ከባለቤቱ በላይ የሚያውቅ የለም። ማህበረሰባችንም እኮ፦
* 'ከባለቤቱ ያወቀ ቡዳ ነው'
* 'ያለባለቤቱ፤ አይነድም እሳቱ'
* 'ባለቤት ካልጮኸ፤ ጎረቤት አይረዳም'
* 'ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለእዳ አይቀበለውም'
በመሳሰሉ አገላለፆቹ የግለሰብን በራሱ ዙሪያ የላቀ ባለቤትነት ይገልፃል። እልፍ ሲልም ሰዎች ግለ-ታሪካቸውን በመፃሕፍት ደግፈው ለትውልድ ማኖራቸው የሐቲቴ ማጠናከሪያ ይሆናል።

በአንድ ወቅት በዩኒቨርሲቲ ውስጥ የስነምግባር እና ስነዜጋ ትምህርት ሳስተምር "Self Reliance" በሚለው ዐቢይ ርዕስ ስር፦ Self Confidence, Self Esteem, Self Awareness... አያሌ ሰልፎች ነበሩ። የእነዚህ ተቃራኒ የሆነውን ይሉኝታ (Self Censure) ማስወገድ እንደሚገባም የተዘጋጀው የማስተማሪያ መነሻ ሀሳብ አጥብቆ ያስገነዝባል። እንደውም ከአንተ ጥንካሬ ሌሎች ይማሩ ዘንድ እውነትህን በድፍረት ንገራቸው ይላል።

ከዚህም አልፎ፦ 'ፍርሀትህን በውስጥህ ሸሽግ፤ ወኔህን ግን ለሌሎች አካፍል' የሚል አንብበናል።
"አርአያ ሰብእ" ፤ "አውደ ሰብእ" እና መሰል መርሐግብሮች እንዲሁ እንግዳ ጋብዘው፤ የግለሰቡን የህይወት ጉዞ ጫፍ በመያዝ ስለራሱ በሰፊው እንዲያወጋ እድል ሲሰጡት ስለራሱ መናገሩም አይደል?

አንድ የዘነጋሁት የፌስቡክ ወዳጄ በሰሌዳው ያኖረው ሀሳብ መነሻዬን ያጠናክርልኝ ዘንድ በራሴው መንገድ አውዳዊ ትርጉሙን እንደሚከተለው አስቀመጥኩት፦
"When writing about oneself, one should show no mercy."
ይህ ወደ አማርኛው ሲመለስ (ሰው ስለራሱ ሲፅፍ ምኅረት የለሽ መሆን አለበት) የሚል ትርጉምን ይሰጣል። ሀሳቡ የተወሰደው "First Reformed" በሚል ርዕስ በተሰናዳው ፊልም ኢታን ሀውክ (Ethan Hawke) የተሰኘው ገፀባህሪ ካህኑን ወክሎ ሲተውን ነው።

ሲጠቃለል በአሮጌ ልማዶችና አስተሳሰቦች ተቀይዳችሁ ሳትያዙ፤ ያለግነትና ራስወዳድነት፤ ራሳችሁን በመውደድና በመግለፅ በኩል አላስፈላጊ ይሉኝታን አሽቀንጥራችሁ ጣሉ!

NB. በወንዴ ፆታ ስለፃፍሁ ይቅርታ። ወደፊት የማኖራቸውን ሀሳቦች በወል አገላለፅ ለማስቀመጥ ቃል እገባለሁ።
=======================
-----------
=======================
የወል ቋንቋችን (የኢትዮጵያ የጋራ መግባቢያችን) የሆነው አማርኛ በርካታ ውበቶች አሉት።
(ከእነዚህ መሀከል አንዱን ሰበዝ ልምዘዝና ግብረመልሱ ካላረካኝ ስለማነሳው ቀድታችሁ መገልበጥ እንደምትችሉ በትህትና እገልፃለሁ። በአስተያየት በማከል መማማር ይቻላል።)
-
የፊደላት (ሆሄያት) ስያሜ፦
፩ "ሀ" - ሀሌታው ሀ፦
ነገር በምሳሌ፣ ጠጅ በብርሌ፣ ዝማሬ በሀሌ እንዲሉ (ሀሌ) መጀመሪያ
፪ "ሐ" - ሐመሩ ሐ
፫ "ኀ" - አኀዙ ኀ ፦ አኀዝ (ቁጥር)
፬ "ኃ" - ብዙኃኑ ኃ
በሚገባ ዐስተውላችሁ ከሆነ በአንድ መስመር የተፃፉት ተመሳሳይ ቅርፅ እንዲይዙ ሆኗል፤ መሆንም አለበት።
፭ "ሠ" - ንጉሡ ሠ ወይም ሠራዊቱ ሠ
፮ "ሰ" - እሳቱ ሰ
በዚህም መሠረት ንጉሥ፣ እሳት... ብለን እንፅፋለን።
፯ "አ" አልፋው አ ፦ አልፋና ዖሜጋ (አሌፍ)
፰ "ዐ" ዐይኑ ዐ
፱ "ዓ" ዓመቱ ዓ ፦ ዘመን ጊዜ
፲ "ጸ" - ጸሎቱ ጸ
፲፩ "ፀ" - ፀሐዩ ፀ
እነዚህ ፊደላት (ሆሄያት) - ጌጦቻችን መለያዎቻችን እና ቅርሶቻችን ናቸውና መጠበቅ አለባቸው።

ጠልቀው ባለመገንዘብ ድግግሞሽን ለማስቀረት በሚል የሀሰት ዘዴ የሆሄያት ቅርሳችንን ለማጥፋት የሚደረገው ዘመቻ ውሀ አይቋጥርም።
ለምሳሌ፦ (((ፀሐይ ሥሥቴ ናት።))) ተብሎ የዛሬ 100 ዓመት የተፃፈን ፅሑፍ ቀጣዩ ትውልድ ፊደል ተቀንሶ ቢያጋጥመው የሚያውቃቸው ፊደላት።
(((** ይ **ቴ ናት።))) የሚል ይሆናል። ምክንያቱም "ሆሄ በዛ" ባዮችን ብንከተል፤ ቀጣዩ ትውልድ የሚያውቀው "ሀ" "ጸ" እና "ሰ" ዘሮችን ብቻ እንደሚሆን ይሰመርበት።

ቻይና ከ50,000 Characters (Pictographic writing/ Logographic writing) ተነስታ ዛሬም ሺህዎች ፊደል ስትጠቀም እኛ እነዚህን ጥቂቶች በዙብን ማለት ውሀ አይቋጥርም። አምስት ፊደላት ተቀነሱና ምን ይፈጠራል?! የጃፓን ፊደላትም በሺዎች ናቸው። የምትፈልጉ ድረገፅ በርብሩ! (ድህረ ገፅ አይባልም!)
ዝርዝር መረጃዎች (መራራ እውነት በኢትዮጵያ ታሪክ) በተሰኘው መፅሐፌ ውስጥ ይገኛሉ።
------___-----___-----___-----___-----___
እድሜ ለአባቶቻችን ብራና ፍቀው፣ ብርዕ ቀርጸው (ብዕር አልወጣኝም)፣ ቀለም በጥብጠው ያቆዩን በርካታ በረከት አለን። ጠብቀን ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲወርድ ሲወራረድ (ሲዋረድ አልወጣኝም) ብናስተላልፋቸው ጌጦቻችን ናቸው።
ስንፅፍ ብንጠነቀቅ ምን ይለናል?!

አንዳንድ ሆሄያት መለያየትና መብዛታቸው ያለምክንያት አይደለም ራሳቸውን የቻሉ ትርጉሞች አሏቸው።
ለአብነት፦
ድህነት፦ ያጣ የነጣ የቸገረው
ድኅነት፦ መዳን መፈወስ
*
ሣለ፦ ሥዕል አስዋበ።
ሳለ፦ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሳለ።
*
ዓመት = ዘመን ጊዜ 2012 ዓ.ም
አመት = የቤት አገልጋይ
*
አባይ = ቀጣፊ ዋሾ ሌባ
ዓባይ = ትልቅ...
*
የሚከተሉት የተሳሳቱ (ስሁት) አፃፃፎች ማሳያ ናቸው።
እሣት፦ ስህተት / Wrong
እሳት፦ ልክ / Correct
ፀሎት፦ ስህተት
ጸሎት፦ ትክክል
*
ሀ = ሀሌታው ሀ
ሐ = ሐመሩ ሐ
ኀ = አኀዙ ኀ
ኃ = ብዙኃኑ ኃ
ሠ = ንጉሡ / ሠራዊቱ ሠ
ሰ = እሳቱ ሰ
አ = አልፋው አ
ዐ = ዐይኑ ዐ
ጸ = ጸሎቱ ጸ
ፀ = ፀሐዩ ፀ
*
በስፋት የተለመዱ ስህተቶችን ለማሳያ፦
* 'እወዳለው' የሚባል አማርኛ የለም፤ እወዳለሁ ትክክለኛው ነው።
* 'እሄዳለው' አይባልም እሄዳለሁ፤
* 'እባካቹ' አይባልም፤ ትክክለኛው እባካችሁ ነው ወዘተርፈ
* 'እባክክ' (ፀያፍ) = እባክህ ትክክል ነው።
* 'እባካቹ' (ፀያፍ) = እባካችሁ ትክክል ነው።
*
በጣም ከተለመዱ ስህተቶች አንድ ልጨምር፦
መፅሐፍት አይባልም፤ ትክክለኛው *መፃሕፍት ነው።
መዝገብ፦ መዛግብት
መፅሐፍ፦ መፃሕፍት
*
ታዬ የሚል የአማርኛ ቃል የለም። ትክክለኛው ታየ ነው።
ከአሰያየም አኳያ፦ ተስፋዬ ዋጋዬ አካሌ ሺብሬ የግሌ ሀብቴ ወዘተርፈ የእኔነትን ለማሳየት ስለምንጠቀምባቸው በአምስተኛው (ሐምስ) ፊደል ይደመድማሉ። በአንፃሩ ታየ ተዋበ አበበ ተሻለ ተደረገ ወዘተርፈ በመጀመሪያው (ግዕዝ) ፊደል ያበቃሉ።
ለአብነት፦ የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር ላይ
"ታየ ህዝባዊነት ዳር እስከዳር በርቶ" የሚለውን ስንኝ አፃፃፍ ልብ ይሏል።

ሌላው ስንፅፍ አርትዖት (edit) ማድረግ በጣሙን አስፈላጊ ነው።
ለማሳያ፦ በተገኙበት ከሚለው ቃል ውስጥ በስህተት "ገ" የተሰኘው ፊደል ቢረሳ በተኙበት ይሆናል።
... በተገኙበት ተከበረ በማለት ፈንታ በተኙበት ተከበረ።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

አይሰው

እቴጌ ጣይቱ ብጡል (ብርሀን ዘ ኢትዮጵያ)

ደራሲ ዶ/ር ሀዲስ ዓለማየሁ (ሃዲስ ኣለማየሁ)