ሞሶሎኒን በገዛ ሀገሩ ያርበደበደው ጀግና አብዲሳ አጋ (ከ1911-1970)

ሞሶሎኒን በገዛ ሀገሩ ያርበደበደው ጀግና አብዲሳ አጋ
(ከ1911-1970)
ጀግናው አብዲሳ አጋ በ1928 ዓ/ም የጣልያን ወረራ ወቅት
ተማርኮ ወደ ጣልያን ከተወሰደ በኋላ ብርድ ልብሱን ቀዳዶ
በመቀጣጠል በመስኮት አምልጦ በርካታ ጀግንነቶችን
የፈጸመ የኢትዮጵያ ወታደር ነው።
ኮሎኔል አብዲሳ አጋ የተወለደው በ1911 ዓ.ም በኦሮሚያ
ክልል ፣ ወለጋ ዞን ነበር። በ12 ዓመቱ አባቱ በንዴት
ወንድማቸውን በመግደላቸው ሲታሰሩ አብዲሳ አባቱን
ለማስፈታት የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ቢያደርግም ሳይሳካ
በሞት ተቀጥተዋል።
በኋላም በ14 ዓመቱ የኢትዮጵያን ጦር በመቀላቀል ሀገሩን
ማገልገሉን ሀ ብሎ ጀመረ። አብዲሳ ጦሩን ከተቀላቀለ
ከሁለት አመት በኋላ የአድዋን ሽንፈት ለመበቀል የዛተው
ፋሺስት ሙሶሎኒ በድጋሚ ኢትዮጵያን ሲወር ሀገሩን
ለመከላከል በ16 ዓመቱ ወራሪውን ጦር መዋጋት ጀመረ።
ውጊያ ላይ ባጋጠመው የመቁሰል አደጋ ህክምና ላይ ከቆየ
በኋላ አዲስ አበባ ውስጥ ፒያሳ አካባቢ በሚገኝ ቤት
በቁም እስር ላይ ነበር። በኋላ ጣልያን ኢትዮጲያን
እንዲያስተዳድር በሾመችው ግራዚያኒ ላይ የመግደል
ሙከራ ከተደረገ በኋላ አብዲሳ አጋ እና ሌሎች 37 የሚሆኑ
የቁም እስረኞች ተጠርጣሪ ተብለው በከባድ ስቃይ እስር
ቤት ከቆዩ በኋላ በወቅቱ የጣልያን ግዛት በነበረችው
በሶማሊያ በኩል ወደ ጣልያን ተወስዶ በሲሲሊ ደሴት
በሚገኝ እስር ቤት እስረኛ ተደረገ።
ከእስር ቤት ማምለጥ እና የአማጽያን ጦር ማደራጀት
አልሸነፍ ባይነት መለያው የሆነው አብዲሳ ሁሊዮ ከተባለ
ዩጎዝላቪያዊ የጦር እስረኛ ጋር በመተባበር ከባድ ጥበቃ
ከሚደረግበት እስር ቤት ለማምለጥ ማሰላሰል ጀመረ።
ተሳክቶለት ቢያመልጥ እንግዳ አገር እንደሚጠብቀው
ቢያውቅም በነጻነቱ የማይደራደረው አብዲሳ የተሰጠውን
የብርድ-ልብስ ቀዳዶ በመቀጣጠል በመስኮት በኩል
አመለጠ። ከዛ በኋላ ግን ሽሽት አልነበረም የጀመረው
አብዲሳ።
ከጥቂት ቀናት በኋላ በማታ ወደ እስር ቤቱ በመመለስ
ጠባቂዎቹ ላይ ጥቃት በመፈጸም እስረኞቹን በመሉ ነጻ
ማውጣት ችሎ ነበር። ያመለጡት እስረኞች ከእስር ቤቱ
ጠባቂዎች በወሰዱት መሳሪያ በመታገዝ የአማጽያን ጦር
ያደራጁ ሲሆን ጦሩን እንዲመራም የመረጡት ጀግናውን
አብዲሳን ነበር።
ከዛም የተለያዩ የጣልያን ወታደራዊ ሠፈራዎች ላይ ጥቃት
በመፈጸም ወራሪዎቹ ጣልያኖች ኢትዮጵያ ውስጥ ከነበረው
የአርበኛ እንቅስቃሴ ያልተናነሰ ጥቃት በሀገራቸው
ያጋጥማቸው ጀመር። በአብዲሳ ጦር እጅግ የተረበሹት
ጣልያኖችም በርካታ ስጦታዎችን ቃል በመግባት
ውጊያውን እንዲያቆም እና የነሱን ጦር እንዲቀላቀል
ለምነውት ነበር። አብዲሳ ግን ከፋሺስት ሥርዓት ጎን
እንደማይቆም በማስረገጥ ጥያቄውን ውድቅ አደርጎ
ጣልያኖችን በሀገራቸው ማስጨነቅ ቀጠለ።
የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተሳትፎ በወቅቱ እየተጋጋለ
የመጣው የጀርመን ናዚ ሥርዓት ሁለተኛው የዓለም ጦርነትን
ሲጀምር ፋሺስት ሙሶሎኒ ከጀርመኖች ጋር ሲያብር
እንግሊዝ ፤ፈረንሳይ እና አሜሪካን ጨምሮ በርካታ
የምዕራብ አገሮች የሕብረት ጦር መስርተው የሙሶሎኒን
ጦር መውጋት ጀምረው ነበር።
በወቅቱ ይህ የሕብረት ጦር የአብዲሳን ዝና በመስማታቸው
ጣልያንን ለማዳከም ለአብዲሳ ጦር የቁሳቁስ ድጋፎች
ማድረግ ጀመሩ። በድጋፉ በመጠናከር ፋሺስቱን ሰራዊት
ማርበድበድ የቀጠለው አብዲሳ የጣልያን ጦር ተሸንፎ ዋና
ከተማዋ ሮም በአሜሪካን እና እንግሊዝ የሚመራ ጦር እጅ
ስር ከወደቀች በኋላ የሚመራቸውን ከተለያዩ አገር የወጡ
ወታደሮች በሙሉ ክንዳቸው ላይ የኢትዮጲያን ባንዲራ
እንዲያስሩ በማድረግ የሃገሩን ባንዲራ እያውለበለበ ሮም
ከተማ ሲገባ በአለም አቀፉ ህብረት ጦር ትልቅ አቀባበል
ተደርጎለት ነበር። ከዛም በኋላ ከተጨማሪ ወታደሮች ጋር
በአለም አቀፉ ህብረት ስር የሚመራ ጦር መሪ በመሆን
ጀርመንን ለማሸነፍ በሚደረገው የመጨረሻ ውጊያ ላይ
ተሳትፎ ግዳጁን በሚገባ በመወጣት የኢትዮጲያን ባንዲራ
ከእጁ ሳይለይ በርካታ የጀርመን ከተሞችን ነጻ ማውጣት
ችሎ ነበር።
ከጦርነቱ መገባደድ በኋላም የእንግሊዝ፣ የካናዳ እና
የአሜሪካ መንግሥታት ጦራቸውን ተቀላቅሎ እንዲቀጥል
በርካታ ጥቅማ ጥቅሞችን አቅርበውለት ነበር። አብዲሳ ግን
ኢትዮጵያ ምንም ያህል ድሃ ብትሆንም ሕዝቡን እና
መንግሥቱን ጥሎ እንደማይሄድ አስረግጦ በመናገር
ጥያቄውን ሳይቀበል ቀረ። ወደ ኢትዮጵያ መመለስ
ተቀላቀለን የሚለውን ጥያቄ ውድቅ ማድረጉ
ያልተዋጠላቸው አንዳንድ የሕብረት ጦሩ አባላት ሁለተኛ
የዓለም ጦርነት ካበቃ በኋላ በወንጀል ከሰው አብዲሳን
እስር ቤት አስገብተውት ነበር።
በኋላም እስሩ ወደ ገንዘብ ቅጣት ተቀይሮ ገንዘቡ ተከፍሎ
አብዲሳ ለዓመታት ወደተለያት ሀገሩ በክብር ተመለሰ።
ከዛም ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በክብር ከተቀበሉት በኋላ
በጊዜው የመከላከያ ሚኒስቴር ወደ ነበሩት ራስ አበበ
አረጋይ መርተውት ነበር። ሚኒስቴሩ ውደመሩት ወደ ሆለታ
ወታደራዊ ሠፈር የገባው አብዲሳ አነስ ባለ ወታደራዊ ቦታ
የተወሰነ ጊዜ ከቆየ በኋላ ለጉብኝት የሚመጡ የውጭ
ሀገር የጦር መሪዎች ስለ ዝናው ሲያወሩ የሰሙት ቀዳማዊ
ኃይለ ሥላሴ ወደ ቤተ-መንግሥታቸው በማምጣት
በኮሎኔልነት ማዕረግ የንጉሡ ጠባቂ ሆኖ አድርገው
ሾሙት። እስከ ንጉሣዊ ሥርዓቱ መውደቅ ድረስ በቦታው
ያገለገለው ስመጥሩው አብዲሳ አጋ ከዛሬ 41አመት በፊት
በዛሬዋ ቀን ከዚህ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

አይሰው

እቴጌ ጣይቱ ብጡል (ብርሀን ዘ ኢትዮጵያ)

ደራሲ ዶ/ር ሀዲስ ዓለማየሁ (ሃዲስ ኣለማየሁ)