እቴጌ ጣይቱ ብጡል (ብርሀን ዘ ኢትዮጵያ)

እቴጌ ጣይቱ ብጡል (ብርሀን ዘ ኢትዮጵያ)
«ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ » በሚል ቅፅል ስም የታወቁት እቴጌ
ጣይቱ ከአባታቸው ደጃዝማች ብጡል ኃይለማርያም እና
ከእናታቸው ወይዘሮ የውብ ዳር ነሐሴ 12 ቀን 1832 ዓ/ም
በጌምድር ውስጥ ደብረ ታቦር ከተማ ተወለዱ። በ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ስርዓት
መሠረት በተወለዱ በ 80 ቀናቸው ጥቅምት 27 ቀን
1833 ዓ/ም በደብረ ታቦር ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ክርስትና
ተነሡ። በልጅነት ዘመናቸው በዚሁ ደብር ውስጥ ዳዊትን
ሲከታተሉ ከቆዩ በኋላ በጊዜው ይሰጡ የነበሩትን ሌሎች
የሃይማኖት ትምህርቶች በየታላላቁ አድባራት በመዘዋወር
ያጠናቀቁ ስለመሆናቸው ታሪክ አዋቂዎች ይናገራሉ።
የተማሩባቸውም መፃሕፍት ተጽፈው ይገኙ የነበረበትን የ
ግዕዝ ቋንቋ አጣርተው ያውቁ ነበር። እናታቸው ወይዘሮ
የውብዳር ከባለቤታቸው ደጃዝማች ብጡል ኃይለማርያም
ከሞቱ በኋላ በጅሮንድ መዩ የተባሉትን የዓፄ ቴዎድሮስን
ባለሟል አግብተው ነበር። እሳቸውም ጣይቱ ብጡል
ትምህርት እንዲቀስሙ ለማድረግ ልዩ መምህር
ቀጥረውላቸው እንደነበር ይታወቃል። እቴጌ ጣይቱ
በማኅደረ ማርያም ሆነው ሲማሩና መፃሕፍትን ይቀጽሉ
በነበሩበት ጊዜ ለቤተክርስቲያን መጋረጃ መሥሪያ በትርፍ
ጊዜያቸው ፈትል እየፈተሉ ያቀርቡ ነበር። በበገና ቅኝትና
ድርደራም በኩል የታወቁ ባለሙያ እንደነበሩ
ይተረክላቸዋል።
እቴጌ ጣይቱ (ያኔ ወ/ሮ) ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ
በጥበብና በህይወት ፍልስፍና የላቀ ችሎታ ባለቤት
መሆናቸው እየታወቀ መጣ:: ፀሐፊ ትዕዛዝ ገ/ሥላሴ
እንደፃፉት ይህንን የጣይቱን ዝና ከሰሙ ልዑላን መካከል
አንዱ በጐንደር ከአፄ ቴዎድሮስ ጋር ይኖሩ የነበሩት ወጣቱ
ምኒልክ ተጠቃሽ ናቸው:: አቤቶ ምኒልክ ስለ እቴጌ ጣይቱ
ዝና የሰሙት አብረው ይኖሩ ከነበሩት አሉላና ወሌ ብጡል
ይባሉ ከነበሩት የእቴጌ ወንድሞች ነው:: በወቅቱ የምኒልክ
ሞግዚት የነበሩት አቶ ናደው (በኋላ ደጃዝማች) ከሌሎች
ቅርብ ሰዎቻቸው ጋር ተማክረው ጣይቱንና ምኒልክን
ለማጋባት ሙከራ አድርገው ነበር:: የእቴጌ ዘመዶችም
በጉዳዩ ላይ ከመከሩ በኋላ ሁለቱን የነገሥታት ዘሮች
እንዲጋቡ ቢያደርጉ የአፄ ቴዎድሮስ ወገኖች በበጐ
እንደማይተረጉሙት በማሳወቅ የጋብቻውን ጥያቄ
ሳይቀበሉት ይቀራሉ:: ምኒልክ ሰኔ 24 ቀን 1857 ዓ.ም.
ከመቅደላ አምባ አምልጠው ሸዋ ከገቡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ
የእቴጌ ጣይቱ ወንድሞች ራስ ወሌ (ያኔ ባላምባራስ) እና
ልጅ (በኋላ ፊታውራሪ) አሉላ ብጡል ከራስ መንገሻ
አቲከም ጋር በመሆን ለንጉሥ ምኒልክ ገቡላቸው:: ንጉሥ
ምኒልክ ሸዋ ውስጥ ስልጣናቸውን አደላድለው ወlሮ
ባፈናንም አግብተው ለ12 ዓመታት እንደቆዩ ከቀን ወደቀን
ዝናቸው እየገዘፈ የሚሰማውን ጣይቱ ብጡልን ለማግባት
ውሳኔ ላይ ደረሱ::
ፀሐፊ ትዕዛዝ ገ/ሥላሴና ቀኛዝማች ታደሰ ዘወልዴ በፃፉት
ታሪክ እንዳብራሩት ንጉሥ ምኒልክ በሚያዚያ ወር 1869
ዓ.ም. ወደ ባህር ዳር ተጉዘው በእናታቸው በወlሮ
የውብዳር ቤት ዘመድ ወዳጅ በታደመበት ከወ/ሮ ጣይቱ
ብጡል ጋር ተጫጩ:: በ1971 ዓ.ም. አለቃ ተክለማርያም
ወልደሚካኤል በሚባሉ የንጉሥ ምኒልክ ቅርብ ሰው
የሚመሩ ደንገጡሮችና አጃቢዎች ተልከው ከወራት አድካሚ
ጉዞ በኋላ ጣይቱን አጅበው ከጐጃም ደብረብርሃን በደረሱ
ጊዜ ንጉሥ ምኒልክ የደመቀ አቀባበል አደረጉላቸው:: ንጉሥ
ምኒልክ በዚያን ጊዜ ከወ/ሮ ባፈና ጋር የሚያደርጉትን ፍቺ
አላጠናቀቁም ነበርና ጣይቱ በወንድማቸው በራስ ወሌ ቤት
እንዲያርፉ ተደረገ:: ጋብቻቸው ሳይፈፀምም ለአራት
አመታት ቆየ:: የእቴጌ ጣይቱና የንጉሥ ምኒልክ ጋብቻ
በፍጥነት እንዳይፈፀም ምክንያት ከሆኑት መካከል በግዛት
ይገባኛል ተከታታይ ጦርነቶች ስለነበሩ እና አንዳንድ ወግ
አጥባቂ የሸዋ መኳንንት ደግሞ "የእቴጌነቱ ቦታ ተላልፎ
ለሰሜኖች መሰጠት የለበትም" የሚል አቋም ይዘው
በመከራከራቸው እንደሆነ የሚጠቁሙ ወገኖች አሉ:: ንጉሥ
ምኒልክ ግን እቴጌ ጣይቱን እንዲያገቡ የሚያስገድዷቸው
በርካታ ምክንያቶች ስለ ነበሩ በሃሣባቸው ፀኑ::
አንደኛው ምክንያታቸው እቴጌ ጣይቱ የተማሩ፣ ብልህና
ቆንጆ ሴት ስለነበሩ ነው::
ሁለተኛው ምክንያታቸው እቴጌ ጣይቱ በጐጃም፣
በጐንደርና በወሎ ከሚገኙ ታላላቅ መኳንንት የሚወለዱ እና
ከትግራይ መኳንንት ጋርም ቤተሰባቸው ከቅድመ-አያታቸው
ከራስ ገብሬ ዘመን አንስቶ የጋብቻ ዝምድና የፈጠሩ ናቸው::
በዚያም ላይ ቅርብ ቤተሰቦቻቸው በተለይም አባታቸው ራስ
ብጡል፣ አያታቸው ደጃዝማች ኃይለማርያም እና ቅድመ-
አያታቸው ራስ ገብሬ በመላው በጌምድር (ከፊል ወሎን
ይጨምራል) የታወቁ መሪዎች ነበሩ:: የአባታቸው ወንድም
ደጃዝማች ውቤ ኃይለማርያምም አማቻቸው አፄ ቴዎድሮስ
እስከ ሚነግሱ ድረስ ሰሜኑን ኢትዮጵያን እስከ ምፅዋ ድረስ
ለ34ዓመታት ገዝተዋል:: ይህን ሁሉ ታሪክ የሚያውቁት
ንጉሥ ምኒልክ እቴጌ ጣይቱን ማግባት ማለት ከሰሜኑ
የኢትዮጵያ ክፍል ጋር መዛመድ ማለት መሆኑን ጠንቅቀው
ያውቁ ነበር::
ሶስተኛው ምክንያታቸው ደግሞ ከዘመነ-መሳፍንት
አንስቶ ትንቢት ነበር:: ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወ/ሥላሴ
የህይወት ታሪክ በተባለው መፅሃፋቸው ይህንኑ ስለእቴጌ
ጣይቱ የተነገረውን ትንቢት አስመልክተው ሲፅፉ እንዲህ
ብለዋል:: "ጣይቱ በምትባል ሴት የኢትዮጵያ መንግሥት
ታላቅ ትሆናለች እየተባለ ሲነገር ይኖር ነበርና ከአፄ ምኒልክ
አስቀድሞ የነበሩ አንዳንድ ነገሥታት ስሟ ጣይቱ የምትባል
ሴት እየፈለጉ ማግባት ጀምረው ነበር:: ነገር ግን ጊዜው
አልደረሰም ነበርና አልሆነላቸውም:: ዘመኑ በደረሰ ጊዜ ግን
አፄ ምኒልክ እቴጌ ጣይቱን አገቡ::
እቴጌ ጣይቱም አዕምሯቸው እንደ ወንድ ነበረና
በመንግሥቱ ስራ ሁሉ አፄ ምኒልክን ይረዱ ነበር::
እንደንግሩም ቃል ኢትዮጵያ በእቴጌ ጣይቱ ዘመን ታላቅ
ሆነች” ብለዋል። ይህን ሁሉ አጥንተው የሚያወቁት ንጉሥ
ምኒልክ ሚያዚያ 25 ቀን 1875 ዓ.ም. በአንኮበር
መድኃኒዓለም ቤተ-ክርስቲያን ከእቴጌ ጣይቱ ብጡል ጋር
በቁርባን ጋብቻውን ፈፀሙ:: አምስት ዓመታት ቆይቶም
ጥቅምት 27 ቀን 1882 ዓ. ም. ጣይቱ ብጡል እቴጌ
ተብለው ተሠየሙ:: በዚህ ጊዜ ንጉሥ ምኒልክ "ንጉሠ-
ነገሥት ዘኢትዮጵያ" ከተባሉ ሶስተኛ ቀናቸው ነበር::
አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ ዳግማዊ አጤ ምኒልክ በተሰኘው
መፅሃፋቸው እቴጌ ጣይቱ ለዚህ ታላቅ ሥልጣን በበቁ ጊዜ
የተፈጠረውን ስሜት ሲገልፁ "የሸዋ ቤተ-መንግሥት ዓለሙ
የዚህን ቀን ተጀመረ:: የሸዋ ቆሌ፣ የሸዋ ደስታ የዚህን ቀን
ተጀመረ:: የሸዋ ቤተ-መንግሥት ከጣይቱ ወዲያ (በኋላ)
ውቃቢ ገባው፣ ግርማና ውበት ተጫነው፣ጥላው ከበደ፣
የእውነተኛው አዱኛ፣ የእውነተኛው ደስታ ከጣይቱ ብጡል
ጋር ገባ” ብለዋል ::
ንጉሡ «አፄ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ» የሚለውን
ስም በተቀዳጁ በማግሥቱ ጥቅምት 27ቀን 1882 አ/ም
ወይዘሮ ጣይቱ ብጡል እቴጌ ተብለው ተሰየሙ። የስርዓተ
ዘውዱ አፈፃፀም በከፍተኛ መሰናዶ የተጠናቀቀ በመሆኑ
እጅግ ደማቅ እንደነበር ከተፃፉ ፅሁፎች ለማወቅ ይቻላል።
እቴጌ ጣይቱም ጳጳሱ አቡነ ማቴዎስ ከንጉሠ ነገሥቱ እጅ
የተቀበሉትን ዘውድ ደፉላቸው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በታወቁበት «እቴጌ ጣይቱ ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ» በሚል የክብር ፥መስምም ማኅተም ተቀረፀላቸው። እነዚሁ ታሪካዊ
ሂደቶች እቴጌይቱን በኢትዮጵያ ዱኛዊ፣ ወታደራዊና ማኅበራዊ ኑሮ ውስጥ ከፍተኛና ብሩህ ሚና ለመጫወት የቻሉ አድረገዋቸዋል።
እቴጌ ጣይቱ ከሕዝቡ ጋር በነበራቸው ግንኙነት በተለይም
ያሳዩት በነበረው ርህራሄና ልግስና በጣመ የተወደዱና
የተመሰገኑ በመሆናቸው በሚያውቋቸው ዘንድ በሰፊው
ይወራላቸዋል። ግልፅ የሆነው የፖለቲካ አስተያየታቸውና
ጽኑ የሆነው ተግባራዊ ውሳኔያቸው፣ ዘዴንና ሥልጣንን
እንዲሁም ምክርን ኃይልን ምን ጊዜ በእንዴት ያለ መጠን
መጠቀም እንዳለባቸው በትክክል የመገመት ችሎታቸው
ሲታይ በዓለም ከታወቁት የፖለቲካ አርበኞች ውስጥ ሊወሳ
የሚገባ ታሪካዊ ስፍራ እንዳላቸው አጠራጣሪ አይሆንም።
ስመጥሩነታቸውን ለማትረፍ ካስቻላቸው ጉዳዮች ጽኑ በሆነ
መንፈሳዊ ኑሮአቸው አኳያ የሚታየው የልግስናና የቤተ-
ክርስቲያን ነፃ ተግባሮች አንዱና ዓይነተኛው ነው። ይህ
ከሃይማኖት መሪዎች ጋር ልዩ ግንኙነት ለመመስረት
ያስቻላቸው ከመሆኑም በላይ የፖለቲካ ሥልጣናቸውን
ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳደረገ ከሌሎች ታላላቅ
የፖለቲካ ሰዎች ታሪካዊ አነሳስ ለመገንዘብ ይቻላል።
እቴጌ ጣይቱ በሀገራቸው የማይደራደሩ ቆራጥ የሴት ጀግና
ነበሩ ይሄንንም ስለ ውጫሌ ውል የተናገሩት ይመሰክራል
«እኔ ሴት ነኝ ጦርነት አልወድም። ሆኖም ይህን ኢትዮጵያን
የኢጣሊያ ጥገኛ የሚያድርግ ውል ከመቀበል ጦርነትን
እመርጣለሁ» በአድዋው ጦርነት ላይ ከባለቤታቸው እኩል
በመዝመት እና ዘዴ የተሞላበት አመራር በመስጠት
ጀግንነታቸውን አስመስክረዋል።
ባላቸው ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ከሞቱ በኋላ በልጅ እያሱ ና
በደጃዝማች ተፈሪ መኮንን መካከል በተፈጠረው የሥልጣን
ሽኩቻ አማካኝነትና ባስከተለው በጦሩ መሃልም መከፋፈል
በመታየቱ በልጅ ኢያሱ አስተዳደር ዘመንም እቴጌይቱ ከቤተ
መንግሥት ተወግደው በግዞት ላይ ለአንድ ዓመት ከመንፈቅ
ከሃያ ሁለት ቀናት ተቀመጡ።
እቴጌ ጣይቱ የደረሰባቸውን ፈተና ሁሉ በትዕግስት
ተቀብለው ጥቂት እፎይ ካሉ በኋላ ከዓፄ ምኒልክ ጐን
ሆነው የኢትዮጵያን አንድነትና ጥንካሬ ለማረጋገጥ ሲታገሉ
ያለፉት ዘመን ከዕለታት አንድ ቀን ትዝ ስላላቸው ከሰገነት
ላይ ብቅ ብለው «ያ ቤት የትኛው ነው» ብለው ሲጠይቁ
ከደንገጡሮቹ አንዷ «የእመቤቴ እልፍኝ ግምጃ ቤት ነበር»
አለች። እሳቸውም ትንሽ ተከዝ ብለው ከቆዩ በኋላ ቀበል
በማድረግ «ነበር ለካስ እንዲህ ቅርብ ኖሯል» አሉ
ይባላል።
እቴጌ ጣይቱ ሰኞ የካቲት 4 ቀን 1910 ዓ/ም በመንፈቀ
ሌሊት ህመም ፀንቶባቸው ከሚወዱትና ከሚወዳቸው
ሕዝብ በሞት ተለዩ። የእረፍታቸውን ዜና የሀዘኑንም ሥነ
ስርዓት ለማወጅ የቤተ መንግሥቱ*መድፍ ሃያ አምስት ጊዜ
ድምፁን አሰማ። በሀዘኑ ስርዓትም ላይ እቴጌ በአድዋ ጦር
ሜዳ ላይ ያሳዩትን*የቆራጥነትና የጀግንነት ሙያቸውን
እየጠቀሱ*በግጥም እየገለጡ በማሞገስ ይሸልሉ
ይፎክሩና*ያቅራሩ ነበር። የእቴጌም አስክሬን በወርቅ ሀረግ
በተከበበ የእንጨት ሳጥን ተደርጐ በብረት ሳጥን ውስጥ
ከገባ በኋላ በቀድሞ ቤተ ፀሎታቸው ውስጥ*ሸራ ቤት
እየተባለ ይጠራ በነበረው መንበረ ፀሐይ እንጦጦ ማርያም
ቤት ውስጥ በታላቅ ክብር አረፉ።
ለተሰበሰበው ሕዝብ ትልቅ ግብዣ ተደርጐ የቀብሩ ፍፃሜ
ሆነ። እቴጌ ጣይቱ ከማረፋቸው አስቀድመው ለ ንግሥት
ዘውዲቱ «ልጄ ማሚቴ ሆይ አደራዬን ሰጥቼሻለሁ» ብለው
መናዘዛቸው በታሪክ ይወሳል። በዚሁ መሠረት ንግሥት
ዘውዲቱ በ ታሕሣሥ ወር 1920ዓ/ም የዓፄ ምኒልክን
ዓፅም ከቤተ መንግስቱ አስወጥተው ለማረፊያው በታዕካ
ነገሥት በዓታ ቤተ ክርስቲያን አሳንፀው በነበረ ጊዜ
የእቴጌንም ዓጽም እዚሁ እንዲያርፍ ቢፈልጉም የእንጦጦ
ማርያም ካህናት እቴጌ ጣይቱ ለኛም እናታችን ናቸውና
መታሰቢያነታቸውን እንሻለን በማለት የተቃውሞ ድምፅ
አሰሙ። ቢሆንም የኑዛዜውን ቃል አብራርተው
በማስረዳታቸው ፈቅደውላቸዋል። በመጨረሻም የእቴጌ
ጣይቱ፣ የዓፄ ምኒልክና የንግሥት ዘውዲቱ መካነ መቃብር
በታዕካ ነገሥት በዓታ ቤተ ክርስቲያን ምድር ቤት ውስጥ
በመንበሩ ትይዩ ሳጥኖች ተፈልፍለው በተሰሩ እብነ በረድ
ታሽገው እንደቆዩ በወለሉ ላይ መደዳውን ተቀምጠው
ይገኛሉ።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

አይሰው

ደራሲ ዶ/ር ሀዲስ ዓለማየሁ (ሃዲስ ኣለማየሁ)