#ህይወት

ያለምክንያት ከሄድክ በምክንያት አትምጣ"
:
ወዳጄ ህይወት ሰልፍ ውስጥ ሳለህ ልብ ልትላቸው
የሚገቡ እነኚህን 19 ነጥቦች በአጽንኦት አንብባቸው!

➊."ያለፈ ነገር እንደማይቀየር አትርሳ!"
:
ላወቀበት ሰው ግን ያለፈው ለወደፊቱ የራሱ የሆነ
ትምህርት አለው፤ ካለፈው ነገርህ ተማር እንጅ በፍፁም
አታማርር፤
ማማረር ነገህን በጎ አያደርገውም።
:
➋.የሰዎች ሃሳብ የአንተን ማንነት አይገልፅም!
ማንነትህ አንተ ውስጥ ነው ያለው፤ መልካም አድርግ
ሌላውን እርሳው የሁሉም ሰው የህይወት መንገድ (ጉዞ)
ይለያያል፤ ለሁሉም ጊዜ አለውና ጊዜው በደረሰ ሰው ሁኔታ
አትቅና።
:
➌.መኪና ገዛ ብለህ "እኔስ" አትበል!
:
ጊዜህ ሲደርስ መኪናዎች ወይም ‘አውሮፕላን’ ትገዛለህ ፣
ያውም ለመኖር አስፈላጊ ከሆነ ፣ ደግሞስ እንዴት
እንደገዛው የት ታውቃለህ? እርሱን ተወውና በራስህ ላይ
አተኩር ፣ ያለህ ነገር በቂ ነው።
:
➍."ለሰዎች ለደስታቸው እንጂ ለሀዘናቸው መንስዔ
አትሁን!"
:
►በሰዎች ደስታ→ደስ ይበልህ!
:
►ለሰዎች→ክፉ አትመኝ፣

►በሃዘናቸውም→አብረህ እዘን፣

►ሰዎች ሲያዝኑ→አትደሰት፣

►ሰው ከሆንክ→የሰው ነገር ይሰማህ፣

ይህ ማለት ግን ተንኮል እየሰሩ ከሚደሰቱ ሰዎች ጋር
ተደሰት ማለት አይደለም።
ሰው እያስከፋ ብሎም እየገደለ የሚደሰት አለ ፣ አንተ
ከተጎዳው ሰው ጋ ሁን፣ አስተውል።
:
➎."በጊዜ ስራ እንጂ ጊዜ ባንተ ላይ አይስራ!" ጊዜ
የማይፈውሰውና የማይቀይረው ነገር የለም። አንተንም
ጊዜው ይቀይርህ ዘንድ ፍቀድለት፤
በተሰጠህ ጊዜ ለመልካም ነገር ሱሰኛ ሁን።
➏. "መክሊትህን ፈልግ!"
ውስጥህ የሚችለውና የሚያምንበት ተሰጥኦ ምን አለህ?
ምን አይነት ስራ መስራት ትችላለህ? አስተውል ጓደኛህን
አትመልከት ፣ ትለያያላችሁና። አለማችን በትምህርት ብቻ
ወይም በጥበባት ብቻ ወይም በተወሰኑ ዘርፎች አይደለም
እየኖረች ያለችው። በጣም ብዙ ነገሮች ናቸው እየደገፏት
ያቆሟት። አንተም ጥቂትም ብትሆን ያለህን ችሎታ ፈልገውና
አውጣው። ቁፋሮ ነው ወይስ ቾክ ይዞ ማስተማር ነው
ወይስ መምከር መገሰፅ ነው? ቆንጆ ሽሮ ወጥ እየሰሩ
መሸጥ ነው? ድንጋይ ቅርፅ (ኮብልስቶን) እየሰሩ መኖር
ነው? ምንድነው? እባክህ ፈልገው አጎልብተው ጀምረው፣
"ምን ይሻለኛል?" እያልክ ጊዜህ እንዳያልቅ። በእርግጥ
ጊዜህ ሳይሆን አንተ ነህ የምታልቀው።
➐. "መልካም ነገር ሁሉ ከፈጣሪ መጥፎ ነገር ሁሉ ደግሞ
ከሰይጣን እንዳልሆነ አስተውል!" ፈጣሪ መጥፎን ወደ
መልካም የመቀየር ብቃት አለው። ሰይጣንም ያጠፋህ ዘንድ
መልካም የሚመስል ነገር ሊያዘጋጅልህ ይችላል።
መልካም ማሰብና መልካም መሆን መልካም ነገር
እንዲገጥምህ ማመቻቸት ነው፤ መጥፎነት ከአንተ ይራቅ፤
ለአንተም ሆነ ለሰዎች ጉዳት እንጅ ጥቅም የለውም።
➑. "ሰው የዘራውን ያጭዳል" የሚለውን አባባል አስታውስ፤
የሰራኸውና የምትሰራው ነገር የሆነ ጊዜ ላይ ዞሮ ያገኝሃል፤
መጥፎ ከሰራህ እንደስራህ፤ መልካም ከሰራህም እንደዚያው
ይገጥምሃል። ክፉ ነገር እየዘራህ መልካም ነገር አትጠብቅ፤
ራስህን አትሸውድ። ጤፍ ዘርተህ ባቄላ አትጠብቅ፤ ጤፍ
የዘራ ገበሬ ጤፍ እንደሚያጭድ ሁሉ አንተም የዘራኸውን
በእጥፍ ታጭዳለህ።
➒. "ለራስህ ስትል መልካም ሁን፣ በጎውንም አስብ!"
ለራስ ማሰብ ማስተዋል እንጅ ራስ ወዳድነት አይደለም።
ራሱን የማይወድ ሰው ሌላውን አይወድም።
➓. "በማንም ላይ አትፍረድ!"
የመፍረድ ሃላፊነት በፍፁም የለህም። ፍርድ የፈጣሪ ነው።
ለመፍረድ እንከን አልባ መሆን ያስፈልጋል፤ ፍጥረት ሁሉ
ፍጥረት በመሆኑ ብቻ እንከን አለበት፤ ጎደሎ አለበት።
የተሻለ ሀሳብ አለኝ ብለህ ካሰብክና ከቻልክ ምከር ካልሆነ
ዝም በል።
➊➊. "መልካም ጓደኛ ከፈጣሪ የሚሰጥ ጸጋ መሆኑን
አትርሳ!"
የጓደኛህን ስሜት ለመራዳት ሞክር፤ መልካም የሆነውን
ነገሩን አውጣለት፤ አበረታታው፤ እንደማይጠቅም
አትንገረው፤ ለሀዘኑ ሳይሆን ለደስታው ምክንያት ሁን፤
ለስኬቱ እንጅ ለውድቀቱ መንስኤ አትሁን።
➊➋. "መልካም ጓደኛ ሁን!"
መልካም ጓደኛ፦ የማይቀና አሳቢና መካሪ ፣ ከእኔ ይልቅ
ለአንተ የሚል ካለህ አንተ ተባርከሃል ታድለሃል። ከሌለህ
ደግሞ አንተ ራስህ መልካም በመሆን ጀምር፤ ባህሪህንና
ስራህን አይተው ይመጣሉ።
ነገር ግን ያለምክንያት ከሄድክ በምክንያት አትምጣ።
በእርግጥ አንዳንድ ጊዜ በሕይወትህ ውስጥ ጉዳት እንጂ
ጥቅም የሌላቸው ሰዎች በራሳቸው ሰዓት ከህይወትህ
ሲወጡ እጅግ መታደል ነው።
➊➌. "ካጓጉል ሀሳብና ጭንቀት ራስህን ጠብቅ!" ያለ
መጠን ማሰብ ጭንቀትንና፣ ሀዘንን ያስከትላል። ከአቅምህ
ከምትችለው በላይ አታስብ፤ መመለስ በማትችለው ነገር
ላይ አትወጠር፤ የተመለሱ ነገሮችህ ላይ ትኩረት አታድርግ፤
አንዳንድ መልሶች በድጋሚ ጥያቄወች ሆነው እንደሚመጡ
አትዘንጋ። ባልገባን ሳይሆን በገባን ነገር ላይ እናተኩር።
➊➍. "ደግነት አይለይህ!"
ደግነት ዋጋ አያስከፍልም ነፃ ነው፤ "ያስከፍላል" ብለህ
ካሰብክም ምላሹ እጥፍ እንደሚሆንልህ አትዘንጋ። እናም
ዘወትር ደግ ሁን፤ ደግ ሆነው የተጎዱ የሉም፤ ቢኖሩም
ከጉዳታቸው ይልቅ በረከታቸውና ሰላማቸው ልክ የለውም።
➊➎. "ደስታህንና ሰላምህን ካንተ ዘንድ አኑራቸው!"
ደስታህንና ሰላምህን የሆነ ሰው ወይም ነገር ላይ
አታስቀምጥ!" ያ ነገር ወይም ሰው ከአጠገብህ ሲርቅ
ወይም ሲጠፋ ደስታህም አብሮ ይጠፋል። ደስታና ሰላም
በአንተ ውስጥ ናቸው።
በራስህ በአፈጣጠርህ→ደስ ይበልህ፤
ውለህ በመግባትህ→ደስ ይበልህ፤
በአለህ ትንሽ ነገር→ደስ ይበልህ።
➊➏. "ፍቅርን ፈልጋት!"
ለፍቅር ለመውደድ እንጅ ለጥላቻ ለዛቻ ለምቀኝነት ጊዜ
አይኑርህ። በመውደድ የተጠመደ ሰው ለመጥላት ጊዜ
የለውም።
➊➐. "ዘመንህን ከርኩሰት ጠብቀው!"
እድሜህን በተመለከተ፣ የፈጣሪ ፈቃድ ከሆነ ካለፈው
ከተቃጠለው ጊዜህ ይልቅ ወደፊት የምትኖረው ብዙ ነው።
ዋናው ደግሞ የኖርክበት የእድሜ ብዛት ሳይሆን በኖርክበት
ዘመን ያሳየኸው መልካምነትና የሰራኸው ደግነት ነው።
➊➑. "መኖርህ ማንንም ካልጠቀመ መሞትህ ማንንም
አይጎዳም" የሚለውን አባባል አስታውስ!"
የኖሩበት እድሜ ትንሹም ቢሆን በቂ ነው ይባላል።
የማቱሳላ እድሜው እንጅ የሰራው ስራ አይታወቅም፤ "ኖሮ
ሞተ" ብቻ ከመባል ፈጣሪ አምላክ ይጠብቅህ፤
መኖርህ ሰዎችን ካልጠቀመ መሞትህ ላይጎዳቸው
ይችላል፤ መኖር ማለት መጥቀም መጠቃቀም ነው።
➊➒. "ከማማረር ማመስገንን ልመድ!"
የምናማርረው የተሰጠንንና የሆነልንን ረስተን፣ ያልጎደለን
ነገር ላይ "ጎደለን" ብለን በጥያቄ ስለምንሞላ ነው፤ ባለው
ነገር አመስጋኝ የሆነ ይጨመርለታል።
በማማረር መባረክ የለም። ሰላምና ጤና፣ ከመልካም
አስተሳሰብና በጎ ህሊና ጋር ምንጊዜም ከዘመንህ አይለይ።
ለውጥ ከራስ ይጀመራል! እናም አሁኑኑ መለወጥን ጀምር።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

አይሰው

እቴጌ ጣይቱ ብጡል (ብርሀን ዘ ኢትዮጵያ)