Ethiopia
ambachewmu3.blogspot.com>
ብዙዎቻችን ትንቢቶችን ተረት ፣ የደብተራ ቅዠት ወዘተ ብለን ስናናቅ ነበር የከረምነው። ትንቢት አትናቁ። የአበውን ቃል አትናቁ። የኢትዮጵያ መፍትሔ ፦ የእግዚአብሔር መንገድ ነው። በእግዚአብሔር መንገድ ውስጥ እውነተኛ ሰላም ፣ ፍትህ ፣ ጥበብ እና ተስፋ አለ።
አንዳንዴ በምናየው ልክ ነው የምናስበው። ያላየነው የህይወት ገፅታ ስላላየነው አይሆንም የለም ማለት አይደለም። አንዳንዶች አሻግረው ተመልክተው የተለያዩ ገፅታዎችን ይመለከታሉ። ይህ የብስለት ጉዳይ ነው። የመንፈስ ብስለት አንድም ደግሞ የነፍስ ንቃት እና ትጋት ውጤት ነው።
ኢትዮጵያ ትንሳኤ አላት የላትም ንትርክ ውስጥ መግባት አያስፈልግም። ትንሳኤውን አሻግረው ለተመለከቱ ትንሳኤው በፈቃደ እግዚአብሔር ጊዜውን ጠብቆ ይገለጥላቸዋል።
ኢትዮጵያ ትንሳኤ እንዳላት ማመን እጅና እግርህን አጥፈህ ተቀምጠህ ጠብቅ ማለትም አይደለም።
ሁሉም ነገር የትጋት ውጤት ነው። ነጥቡ እንዴት ነው የምንተጋው ነው። ቅኝ ገዥዎችህ ባስተማሩህና በሰሩልህ የፓለቲካ ርእዮተ ዓለም ነው በጥንቱ የአባቶችህ በነዮቶር ስርአት ነው ለኢትዮጵያ የምትተጋው ???
በኢትዮጵያ ትንሳኤ የምናምነው ስራ ፈት ስለሆንን አይደለም። በቅዱሳት መፃሕፍት ፣ በቅዱሳን አባቶች ትንቢት እና በትውፊት ስለምናምን ነው። የኢትዮጵያን ትንሳኤ መጠበቅህ በእምነትህ ያጠነክርሃል እንጂ አያዝልህም።
የዚህ ትንሳኤ መገለጥ ዝቅ የሚያደርጋቸው ስማዝያውያን (ሃያላን መንግሥታት) የኢትዮጵያ ትንሳኤ ሳይገለጥ ለማዳፈን እጅግ የረቀቁ ሴራዎችን አድብተው ሰርተዋል እየሰሩ ነው።
ይህ ስልት አገር ውስጥ ባሉ የእናት ጡት ነካሾም የሚደገፍ ነው። አንዳንዶቹ ደግሞ በኢትዮጵያ ትንሳኤ ስም እየማሉ ከተዋህዶ ህዝቡን ሊለዩ የሚዳክሩትም የዛኑ ያህል ብዙ ናቸው።
ትንሳኤውን ለማየት የቀራንዮን የስቃይና የፈተና መንገድ ማለፍ የግድ ነው! የሕዝባችን ወቅታዊ ሁኔታም ይህ ነው! ከመንገድ መሀል ነን! ጉዞ ላይ ነን! ከግቡ አልደረስንም! የትንሳኤውን ብርሀን እንድናይ የፈተናውን መንገድ ማጠናቀቅ አለብን! ጌታችን መድሀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በህይወታችን ውስጥ ያሉትን ፈተናዎችና መሰናክሎች የምናልፍበትን ጥበብ ትዕግስት ማስተዋል እና ፅናት እንዲሰጠን እመኛለሁ! የትንሳኤውን ብርሀን ለማየት ያብቃን!
ውድ ኢትዮጵያውያን ሀገራችን ካለችበት ወቅታዊ ችግር በቅርብ እንድትላቀቅ ሁላችንም ሀላፊነት ስላለብን የምናስተላልፋቸው መልዕክቶችና መረጃዎች ሀላፊነት የሚሰማን እንደሆንን የሚመሰክሩ ሊሆኑ ይገባል ፈጣሪ ደግ ዘመን ያምጣልን !
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ