አይ አሜሪካ



#አይ_አሜሪካ 
#ከምርጫ_በኋላ_በኢትዮጵያ_ብሔራዊ_ውይይት_እንዲደረግ_አሜሪካ ጥሪ_አቀረበች
 ambachewmu3.blogspot.com 
የኢትዮጵያን የወደፊት አካሔድ ለመወሰን እና የአገሪቱን ዴሞክራሲና ብሔራዊ አንድነት ለማጠናከር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሚመሩት መንግሥት እና መላ ኢትዮጵያውያን ከምርጫ በኋላ ለሚካሔድ አካታች የፖለቲካ ብሔራዊ ውይይት ቁርጠኛ እንዲሆኑ አሜሪካ ጥሪ አቀረበች። ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የሚመሩት የአሜሪካ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና ለሠራተኞቹ ጥረቶች እውቅና ቢሰጥም፤ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ የሚካሔድበት ከባቢ“አሳሳቢ ነው” ብሏል። 
የአሜሪካ መንግስትን አቋም የሚያንጸባርቀው መግለጫ ዛሬ አርብ ሰኔ 4፤ 2013 የወጣው፤ አንቶኒ ብሊንከን በሚመሩት የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በኩል ነው። መግለጫው መጪው የኢትዮጵያ ምርጫ አሉበት ያላቸውን ፈተናዎች ዘርዝሮ ሥጋቱን ገልጿል።
“የተቃዋሚ ፖለቲከኞች እስር፣ የገለልተኛ ሚዲያ መዋከብ፣ የአካባቢያዊ እና ክልላዊ መንግሥታት ወገንተኝነት እንዲሁም በመላ ኢትዮጵያ በብሔሮች እና በማህበረሰቦች መካከል የተቀሰቀሱ ግጭቶች ለነፃ እና ፍትሐዊ ምርጫ እንቅፋት ናቸው” ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ መግለጫ ያትታል። 
በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ስም ይፋ የሆነው መግለጫ የዘረዘራቸው ጉዳዮች፤ ኢትዮጵያውያን ምርጫውን ተዓማኒ አድርገው እንዳይቀበሉት ሊያደርግ እንደሚችልም ጠቁሟል። መግለጫው እንደሚለው “በጸጥታ ጉዳይ እና በመፈናቀል ምክንያት በርካታ የመራጭ ክፍሎች እንዳይሳተፉ መደረጋቸው በተለይ አሳሳቢ ነው።”
መግለጫው ፖለቲከኞች እና የማሕበረሰብ መሪዎች ኹከትን እንዲያስወግዱ እና ሌሎችንም ከማነሳሳት እንዲቆጠቡ ጥሪ አቅርቧል። ሁሉም የፖለቲካ ተዋናዮች እና የማህበረሰብ መሪዎች ቅሬታዎቻቸውን በድርድር እና በውይይት ሊፈቱ ይገባል” የሚል ምክር የለገሰው የአሜሪካ መንግሥት፤ ሰላማዊ የውዝግብ አፈታት መንገዶችን እንዲከተሉም አሳስቧል።
ለነፃ ሚዲያ እና ንቁ የሲቪክ ማህበረሰብ የኢትዮጵያ መሪዎች ድጋፍ እንዲሰጡ ያበረታታው የአሜሪካ መንግስት፤ “የዜጎችን ሐሳብን የመግለጽ፣ ሰላማዊ ስብሰባ የማድረግ መብቶች መንግስት እንዲያከብር እና የኢንተርኔት አገልግሎትን ከመዝጋት እና ኔትወርክን ከመገደብ እንዲቆጠብ” ጥሪ አቅርቧል።
“በኢትዮጵያ በርካታ አካባቢዎች በክልሎች እና ብሔሮች መካከል ያለው ልዩነት መካረር የአገሪቱን አንድነት እና የግዛት ሉዓላዊነት ያሰጋል። ከምርጫው በኋላ ያለው ጊዜ ኢትዮጵያውያን ተባብረው እነዚህን ልዩነቶች ለመጋፈጥ ኹነኛ ወቅት ነው”
– የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ
“እነዚህ ምርጫዎች እንደ አንድ ነጠላ ኩነት መታየት የለባቸውም” ያለው የአሜሪካ መንግስት፤ “ወደ ውይይት፣ ትብብር እና ስምምነት የሚመራ የዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሒደት አካል” መሆን እንደለባቸው በመግለጫው ጠቁሟል። §
“በኢትዮጵያ በርካታ አካባቢዎች በክልሎች እና ብሔሮች መካከል ያለው ልዩነት መካረር የአገሪቱን አንድነት እና የግዛት ሉዓላዊነት ያሰጋል” ያለችው አሜሪካ ከምርጫው በኋላ መፍትሔ ሊፈለግ እንደሚገባ አሳስባለች። “ከምርጫው በኋላ ያለው ጊዜ ኢትዮጵያውያን ተባብረው እነዚህን ልዩነቶች ለመጋፈጥ ኹነኛ ወቅት ነው” ብላለች።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

አይሰው

እቴጌ ጣይቱ ብጡል (ብርሀን ዘ ኢትዮጵያ)

ደራሲ ዶ/ር ሀዲስ ዓለማየሁ (ሃዲስ ኣለማየሁ)