Gondar

ጎንደር

ጎንደር በየማለዳው ከፀሐይዋ ጋር አብራ የምትሞቅ ከተማ ነች። ሽር ጉድና ግርግሯም እንደ ፀሐይዋ ቀስ እያለ ነው የሚሞቀው። ጎንደርን ከአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማ ጋር እኩል ያያት ሰው ኢትዮጵያን ያይባታል፤ ጎንደር ቁልጭ እናቷን ኢትዮጵያን ትመስላለች። ተመልካች በከተማዋ ከፍታ ላይ ሆኖ ቢያይ፤ ጸጉሩ ገባ ገባ ይል እንደጀመረ ጎልማሳ፤ ተራሮቿ ተገልጠው ይታያሉ። በእነዚህ የሳሱ ስፍራዎች ላይ ደግሞ ጅምር ዘመናዊ ህንጻዎች በብዛት አሉ፤ አላለቁም። ምንአልባት ሲያልቁ ውበት ሊሆኗት ነበር፤ በጅምር መቅረታቸው ግን ዐይን ይሰብራል። የውበት ማረፊያ ዙፋን የነበረችና የሆነች ጎንደር፤ የቀደሙት አፈር አልመው ተጠብበውና ተመራምረው ቤተመንግሥታት የገነቡባት ጎንደር፤ በ«ዘመናዊ» ጅምር ህንጻዎች ተነካክታለች።
እድገት ጉዞ ነው፤ ሮጠው የሚደርሱበት ጠርዝ አይደለም። የሳር ጎጆዎች ወደ ዘመናዊ ቤት እየተቀየሩ ሰዎች የተሻለ ኑሮ እንዲመሩ ያስፈልጋል። ግን ቀለምን ባያስቀይር ብለን ደግሞ እንመኛለን። እንግዲህ አትቀየሙኝ፤ ጎንደርን የሚመስልና ስለጎንደር የሚናገር ህንጻ እና ቤት ማየት ጉጉት ብቻ ነዉ። 
ከዛ ውጪ ግን እውነትም ለመናገር ጅምር ህንጻዎቹ ለመቀጠላቸው ምንም ምልክት የማይታይባቸው መሆኑም ያሳስባል ። 
ጎንደር መሃል ከተማ ፒያሳ የሚባል አካባቢ አለ። ይህ ሰፈር ልክ እንደ አዲስ አበባ ፒያሳ መልኩ፣ መታጠፊያው፣ ይመሳሰላል ዉበቱ ፅዳቱ ግን ምንም አይመሳሰልም
እና ምንአልባት እነዛ ጣልያኖች በአገራችን ወዲያ ወዲህ ባሉበት ጊዜ የተከሏቸው ህንጻዎች፤ ስለእነርሱ ሳይናገሩ ይቀራሉ ብላችሁ ነው? ጣልያን ይህን ያደረገች እኛስ በገዛ አገራችን ምን ያንሰናል?
ስለጎንደር የሚናገር፤ ጎንደርን በወፍ በረር የሚያሳይ፤ ታሪኳን ቁልጭ የሚያደርግ፤ የነፋሲለደስና የሠርጸ ድንግል ማረፊያ መሆኗን የሚያሳውቅ ምልክት የለም። በዚህ በኩል የጎንደር ዩኒቨርስቲ በዚህ የሚመሰገን ነው። ዩንቨርስቲዉ ከመግቢያው ጀምሮ የጎንደር መሆኑን ይናገራል። እልፍ እንበል፤ የጎንደር ምሽት በአዝማሪዎች ቅኔና መሰንቆ ይደምቃል። ክፍት በር ካገኙ ወደ አገራችን ሙዚቃ ዘርፍ እንደ ንብ እየተመሙ ሊገቡ የሚችሉ ድምጻውያን አሏት፤ ጎንደር። ይግረማችሁ! ሁሉም ደግሞ ገጣሚ ነው።
ባህልንና ታሪክን ብቻ አይደለም፤ ከጎንደር ጥበብ ይቀሰማል። ሻገር ብለን ማክሰኚትና እንፍራንዝን፤ እንዲሁም ጉዛራን አየን፤ የሀገር ስሜት፣ ፍቅርና ቁጭት እዚያ አለ። እስከዛሬ ያላባራ ወኔ ከየጎንደሬው ዐይንና ስሜት ይነበባል። ፍቅሩና ስሜቱ ለአገር ነው፤ ቁጭቱ ደግሞ ለትውልድ። ባለማስተዋል ብሎም በመደንዘዝ እየጠፋ ስላለ ትውልድ ጎንደር አዝናለች። በጥበብ የሚጠሩ የነበሩ እንደ እንፍራንዝ ያሉ ከተሞቿ በጫት ስማቸው ይጠራ ጀምሯል። ወቅታዊ የፖለቲካው ትኩሳትም ደርሷታል፤ ታተኩሳለች። እና ይህ ሁሉ ተደማምሮ እንዴት አይቆጭ!
በየቀኑ አዳዲስ ስንኝ እንደሚቀባበሉ አዝማሪዎች፤ አዲስ ነገሮችን ይዞ እንደሚገኘው ቀን፤ አዲስ ሆና እንደምትወጣው ፀሐይ፤ በጎንደር ሁሌም አዲስ ነገር አለ። 
ጎንደር ውበቷ፣ ክብሯና ድምቀቷ አንድም ሰላሟ ነውና፤ ሰላሟን መጠበቅ ያስፈልጋል 
ጎንደር ቁልጭ እናቷን ኢትዮጵያን ትመስላለች። እንዴት ሳትሉኝ ቀራችሁሳ! ታሪክና ባለታሪክ ያገነናት፤ የብዙ ጥበብና ሀብት ባለቤት። ኩሩና በሥራው የሚመካ ሕዝብ ያለባት፤ ብዙ ሆኖ በአንድ መኖርን አውቆ፤ «አንተ ጎንደሬ…እንደ አገርህ እንደ አገሬ» የሚባባሉባት ጎንደር፤ አዎን! አቃፊዋን እናት ኢትዮጵያን ትመስላለች። እናቷም ልክ እንደእርሷ ናት። የገነነች፤ የታፈረችና የተከበረች አገር። ዘመንና ልጆቿ ከፍ አድርገዋት የነበረ፤ አሁን ደግሞ በየዕለቱ ክፉዋን ላለመስማት ሁሉም በሰቀቀን የሚጨነቅላት።
ጎንደርና ኢትዮጵያ በዚህ ይመሳሰላሉ፤ ዘመንበትውልድ እየገመገመ፤ በአቅም እየፈተነ፤ በፖለቲካ እያነደደ ይከታተላቸዋል። ሁለቱም ግን ተስፋ አይቆርጡም፤ አለን ይላሉ፤ ደኅና ነን ይላሉ

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

አይሰው

እቴጌ ጣይቱ ብጡል (ብርሀን ዘ ኢትዮጵያ)