የታንጉት ምስጢር

ምዕራፍ አንድ
ከፋሲል ዘመነ መንግሥት ጀርሞ የሥልጣን ማዕከል ሆና የኖረችው የጎንደር ከተማ
ማኅበራዊ እንቅስቃሴ፤ ከአዲሱ የቴዎድሮስ ሥርዓት፤ አዲስ የጦር አበጋዞች አዲስ ሠራዊት ጋር
ለመስማማት አዲስ ቅኝት ሲከረክር ድንገተኛ ከባድ እንግዳ ወይም ሠርገኛ ደሶበት የቤቱን ዕቃ
የሚያተረማምሰ ባለቤት መስሏል። የሚተራመሰው ማኅበራዊ ግንኙነት ግን በወጉ ሊቀመጥ
አልቻለም። ሊቀመጥም አይችልም ነበር። ጎንደር ጥንት ከተቆረቆረች፤ ፈጽሞ የተለየ አዲስ
ማኅበራዊ ዛፍና ፍሬ ለምቶባት ነበር።
ከተማ እንደ ማሳ ነው። ማኅበራዊ አኗኗር ማኅበራዊ አስተሳሰብ የዘራዉን ማኅበራዊ
ሕይወት ያበቅላል፤ ያሸታል፤ ያፈራል፤ ማሳው በወቅቱ ካልታረመ ዝባዝንኬው እስከ ገሰሱ
በርክቶ ይገኛል። ማሳው ራሱ በሚገባ ካልተያዘ እንክርዳዱም፤ እረሙም እየበዛ ሔዶ ጠቃሚ
ፍሬ የማይሰጥበት ጊዜ ይመጣል። ዕዳሪ ይሆናል። የጎንደር ከተማ ማኅበራዊ ሕይወትም አንድ
መቶ ስልሳ ዓመት በሚሆን ጊዜ ውስጥ እየተበላሸና ከመልካም ፍሬ ይልቅ፤ ሙጃ የበዛበት ማሳ
እየሆነ ሔዶ ነበር።
ፋሲል፤ ጎንደርን ሲቆረቁር ሠራዊቱ ገና መዝናናት ያልለመደ ለተግባሩ ያልተሰላቸ፤
ምቾት ገና ያላሰናነፈው፤ ትዕዛዝ አቆብቁቦ የሚጠባበቅ ትኩስ አፍለኛ ነበር። አላማም ነበረው።
በሃይማኖት ምክንያት ተነሥቶ የነበረው ሁከትና የርስ በርስ ጦርነት ጨርሶ እስኪረጋጋ ከሥፍራ
ሥፍራ እየተንቀሳቀሰ አጥፊ ይቀጣል። አስቸጋሪ ይነገራል። ሰላም ያስከብራል። ከጦር መሪዎቹ
ሌላ በስብከት፤ በውግዘት፤ በምርቃት መንፈሳዊ ሕይወቱን የሚያንቀሳቅሱና የሚመሩ፤ ከዚያም
አልፎ መስቀል ከሰላጢን ይዘው አብረውት የሚሰለፉ፤ አዲሱን የካቶሊክ ሃይማኖት ነበሩ።
የነጋሹም፤ የአንጋሹም፤ የዘማቹም የቀዳሹም ማኅበራዊ ሕይወትና አስተሳሰብ በአንዳች ዐይነት
የዘመቻና የዘማች መንፈስ የተመራበት ወቅት ነበር። ፋሲል የምድራዊና የሰማያዊ ሥልጣን
መግለጫ አድርጎ የቆጠራቸውን የቤተ መንግሥትና የቤተ ክርስቲያን ሕንፃዎች ማሠራት
የጀመረውንም ምናልባት በዚሁ መንፈስ ነበር። ለሌላ ነገር ቡቃያ፤ ፈር እየቀደዱ መሆኑ ግን
በጊዜው አልታየው ይሆናል።
ከሚያማምሩት ሕንፃዎች አካባቢ መሸታ ቤቶች ብቅ ብቅ አሉ። በቤተ ክርስቲያን አካባቢ
ነጋ ለወሬ፤ መሸ ለዘኬ የሚሉ ጠምጣሚዎች ወጣ ወጣ አሉ። በቤተ መንግሥቱ ዙሪያ ሴት
ሲያጫውት የሚውል ዋልጌ ወታደር እንደ አረም እየበቀለበት ሔደ። በየመንደሩ ሽቶ ተቀብተው፤ ሰንደል ወይዛዝርት መኳንንት ማስተናገድና ማስደሰት፤ ማጫወት ሥራቸው የሆነ
ወይዛዝር ተፈጠሩ። በየዕልፍኙ ከሴት ጋር የሚወዘፉ መኳንንት አቆጠቆጡ።
ከፋሲል የተከተሉት ነገሥታት፤ የየራሳቸው ቤተ መንግሥትና ቤተ ክርስቲያን ሲያንፁ፤
ጎንደር በሕንፃም በነዋሪ ብዛትም እየለማችና እየደመቀች ስትሔድ እንደ አረጀ ማሳ ማኅበራዊ
አራሙጫዋም በዚያው ልክ እየብረከተና እየሰፋ ሔደ። በዘመነ መሳፍንት ደሞ፤ አራሙቻው
ደኅናውን ማኅበራዊ ሰብል ጨርሶ የዋጠው ከሚመስልበት ደረጃ ደረሰ።
ግንቦቹ ሳይቀሩ አርጅተው ነበር። አንዳንዶቹ ግድግዳቸው ፈራርሶ፤ መዝጊያዎቻቸው
ወላልቀው የሌሊት ወፍ ማደሪያ ሆነዋል። ብዙው መንደር ጠፍ መስሏል። ሁሉ ታክቶ፤ ሰንፎ
የተወው ይመልስ ከውጭ በኩል በመልካም ሕይወት እንደውጪ መልኩ ያረጀ፤ የበሰበሰ ዐይነት
ነው። መስፍኑ፤ መኮንኑ የባላገር አፍንጫ እየሰነገ የሚያጋፍፈውን በመቀለብ፤ ለሌላ ተግባር
የማይባክን ጉልበቱን የሚያውልበት ብዙ ዕቁባት በየጉራንጉሩ አስቀመጠ። እንዳሰኘው፤
እንዳደረሰው እምብርት እስኪያብጥ መብላት፤ ጢንቢራ እስኪዞር መጠጣት፤ በዚያው መዘሞት
ነው። ነፍጠኛውና ጭፍራው ከአለቃው የተረፈውን የገበሬ ጎተራና ጎታ እያሟጠጠ እንዳቅሙ
ሁለት ሦስት ውሽማ ይዞ ሲተሻሽ መዋልና ማደር ነው። ለተግባር፤ ለዓላማ የሚቀሰቅሰው መንፈስ
አርጅቷል። ገርጅፏል። ክፉና በጎ ለይቶ የሚሰነጥቀው ሕሊና ዶልዶሟል። የቀረው ለደስታ፤
ለምቾት ለፍትወት የሚንቀሳቀስ ወደ እንሳሳት ስሜት የተቃረበ ሕይወት ነው። ይህም ሕይወት
ግን ለመኖር የለመደውን ያለ ማቋረጥ ለማግኘት ይፈልጋል። በዚህ ረገድ ዕቁባቶችና ውሽሞች
ሌላም ሚና ነበራቸው።
በየመሳፍንቱ በየመኳንንቱ እልፍኝ፤ ጨለማ የዋጠው ሤራ ሲዶለት ያድራል፤ በዚህም
ሤራ ምክንያት ዛሬ የነገሠው በሣልስ ወህኒ አምባ ይጋዛል፤ ወይም የመጨረሻ እስትንፋሱን ውጦ
ይገኛል። ሥልታን እንደ ነፋስ ሳይታወቅ አቅጣጫውን በሚለወጥበት፤ ሹመትና ጉልት ከዋለበት
በሚያድርበት ሁናቴ መካከል ታማኝነትና መታመንም ቋሚ ሊሆን አይችልም። ፊት አይቶ፤
ሚዛን ገምቶ ይለዋወጣል።
ለዚህም ወይዛዝርቱ፣ ዐይን፣ ጆሮና አፍ ሆነው ይሠራሉ። እንደ ሐረግም መሳሳቢያና
መንጠላጠያ ሆነው ያገልገላሉ። እና፣ ይህንን ሚናቸውን በሜባ ይጠቀሙበታል። ራሳቸው
ባይሾሙ ለሹመት ያሳጫሉ። ባይቀጡ ጥርስ ያሰባሉ። ባይዋጉ ያጣላሉ። አንዳንዶቹ ከሁለት
ባላጋራዎች ጋር ሳይቀር ግንኙነትና ወዳጅነት በመፍጠ፥ ከዚህ ወደዚያ ከዚያ ወደዚህ ነገር
እያቀባበሉ፣ ጉልበት እያፈታተሹ፥ አንዱ ቢወድቅ ከሌላው ወደዚህ ነገር እያቀባበሉ፣ ጉበት
እያፈታተሹ፤ አንዱ ቢወድቅ ከሌላው ተንጠላጥለው ይቀራሉ። ቆይተው ሌላ መጠባበቂያ
ያበጃሉ። ነገራቸው ቢጋለጥ እንደ ብልህ፤ እንደ ብልጥ ይታዩበታል እንጂ አያፍሩበትም ነበር።
እንደ ጅል፤ «እንደ ባላገር» የሚታየው የጥንቱን ሥነ ምግባር ልጠብቅ ያለው ግትር ነበር።
ነጋዴው ሳይቀር በዚህ የማኅበራዊ ሕይወት ድቀት ውስጥ ገብቷል። በረሃ አቋርጦ፤ ቆላ ወርዶ፤
ደጋ ወጥቶ በሚነግደው ሸቀጥ ሕሊናው በቅንነት የተመነለትን ትፍር በምዝር ከአለቃ መመንተፉ ያስመረረው ጎንደርን ትቶ ሌላ የንግድ ኬላ መምረጥ አለበት። በጎንደር የቀረው ግን በሚዛን
ማበል፤ በስፍር መሸፈጥ፥ ያካክሰዋል። በጎንደር ሲኖሩ እንደ «የጊዜው ጎንደር» መሆን ግድ
ሆኖበት ነበር። በዘመነ መሳፍንት ፍጻሜ ላይ የጎንደር ማኅበራዊ ኑሮ፣ በሥነ ምግባር የላሸቀ፣
በአስተሳሰብ ያረጀ፣ በሥራ እንቅስቃሴው የደኸዬ ዓላማ የለሽ ነበር።
ቴዎድሮስ የአዲስ ሥርዓት ሰይፍ መዝዞ በድንገት ሲመጣ ወዲያው ቢደናገጥ አይስገርምም።
ከድንገተኛ ድንጋጤው መለስ ሲል ደግሞ፣ የህልውና ነገር ነውና፤ መወጣጫው መንገዱን መፈለጉ
የማይቀር ነበር።
አዲሱ የቴዎድሮስ ሥርዓታዊ ሰይፍ የጎንደርን ሕይወት እንዳስደነገጠው ሁሉ የጎንደር ሕይወት
ያስደነገጣቸው የቴዎድሮስ ወገን ሰዎችም ነበሩ። የገርዬ ሚስት ታንጕት ናት።
ታንጕት የኖረችው በሕፃንነቷ በገጠር፤ በኋላም፣ ባልዋ በዘመተበት፤ ቴዎድሮስ በሰፈረበት
በየጫካው ስትዘዋወር ነው። ቀደም ሲል ያየችው ትልቅ የሕዝብ መኖሪያ ሠፈር ቢኖር፤ የጭልጋና
የመተማ መንደሮች ነበሩ። እነርሱም በጊዜው አስደንቀዋት ነበር። የደረስጌ ጦርነት እንዳበቃ፤ ገብርዬ ቋራ
ድረስ ገሥግሦ በመምጣት ጎንደር ይዘዋት ሲገባ ዐይኗን ማመን አቃታት። ግንቦቹ፤ ሕንፃዎቹ በሰው እጅ
የተሠሩ አልመሰላት አሉ። ራስዋ የለበሰችው ጥበብ ኩታና ቀሚስ የማያሳጣ ቢሆንም ከጎንደር ወይዛዝርት
አለባበስ፤ ሆነባት። የካህናቱ ጥምጥም ሳይቀር ሌላ ነው። የባለሙያን ሁሉ ትንግርት ሆነባት። የካህናቱ
ጥምጥም ሳይቀር ሌላ ነው። የባለሙያን ልቅ ክርክሞሽ ያስንቃል። ድንገት ከሰው መንደር ገብቶ
እንደተናገረ የዱር አውሬ አንዳች ዐይነት ፍርሃት ቢጤ ተሰማት።
«አንትዬ እኛ ማናቸው? አቡኑ?» ስትል ገብርዬን ጠየቀችው፤ በጃኖዋቸው ላይ ካባ ደርበው
ዝማሜ እንደሚወርዱ መቋሚያቸውን እያወዛወዙ በአጠገባቸው ያለፉትን ካህን በዐይንዋ እያመለከተች።
ከኋላቸው ሁለት ደቀ መዛሙርት ይከትተሉዋቸዋል።
«አንድ ቄስ ናቸው!» ገብርዬ በማቃለል ፈገግታ መለሰላት።
«አታውቃቸውም?»
«የጎንደርን ቄስ ሁላ የት አውቀዋለሁ ብለሽኝ!?»
«ኧረ እኚህ ትልቅ ናቸው!» አለች ላለመረታት።
«ግዴለሽም እየቆየሽ ታይዋለሽ።»
«ኧረ አንተዬ» ብላ ሳትጨርስ ተወችው። የሐር ጥላ አሲዛ በሠጋር ግራጫ በቅሎ
የምትፈሥሠውን አንዲ ወይዘሮ በአድናቆት ዐይንዋን ትክል አድርጋ ትመለከታለች።
«ምነው?»
«ያች ወይዘሮ ማናት አንተዬ?»
«የጎንደር ሴት?»
«ማለ - ማለቴ የማን ምሽት ናት?»
«የታባቴን አውቃታለሁ ብለሽኝ?»
‹እህ - ጎንደር ተቀምጫለሁ ትላለህ እንጂ እንደኔው ባላገር ነህ። አንዱንም ሰው አታውቀው»
አለችው በቀልድ ሽጉጥጫ።
«ምን አታክረሽ። ይኼነ ኮማሪት ትሆናለች።»
«እንደዚህ ያለችው?» ማመን አቃታት፤ ‹ዛዲያ ባሎቻችን እነዚህን እያዩ› የሚል የፍራቻ ሐሳብ
ውልብ አለባት።
ማረፊያ ቤታቸውም ቢሆን፣ በመጀመሪያ እንደ ቤተ ክርስቲያን አስፈርቷት ነበር። ከአጣጣሚ
ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ግቢና የግንቡን ጥግ ይዞ የተሠራ ደርብና ምድር ቤት ነው። ከአካባቢዎቹ
ሕንፃዎች ጋር ሲነጻጸር እስከዚህም ትልቅ አይደለም። ደርቡ ሰፋ ያለ አዳራሽ፣ መለስተኛ እልፍኝ፣
በሁለት በኩል አነስ አነስ ያሉ ሁለት ጓዳዎች፣ ከወደኋላው ለብቻ ማድቤትና የዕቃ ቤቶች አሉት። ዱሮ
የደጃዝማች ወንድይራድ የነበረው ይህ ቤት፣ ራስ ዐሊ ከነመኳንንታቸውና ከነሠራዊታቸው ጎንደርን ለቀው
ከሸሹ በኋላ ወና ሆኖ ቆይቷል።
«ይኸን ሁሉ ምን ልናገረው ነው?» ስት ጠየቀች፣ ገብርዬ አስገብቶ እንዳሳያት። ዕቃ የሌለበት
አዳራሽ ከትልቅ ቤተ ክርስቲያን ቅድስት ተሰፋ መስሎ ታያት። «ልጅ የለን ውላጅ የለን» አለች በቅሬታ
መልክ።
«እንግዲህስ መቸስ የቋራ ጎጆ ይዘን አንመጣ። እንደሚሆን አሟሙቂው እንጂ፣ እንግዳም
መምጣቱ አይቀር። እግዚአብሔር ታለ ደሞ!»
ታንጕት ልጅ አለመወለዷ ሁልጊዜ እንደሚያሳስባት ስለሚያውቅ ከፈገግታ ጋር በማባበል
የጉንጩዋን ስርጉዳት በጣቱ ጠቅ አደረጋት።
እንዳለውም ቤቱ ዕቃ ሲገባበት እሳት ሲጤስበት ሰብሰብ ያለ መሰለ። ታንጕትም ቤት ማሰናዳቱ፣
ምግብ ማዘጋጀቱ ጊዜ እያሳለፈላት፣ ፍርሃት ፍርሃት ማለቱ ተዋት። ወደ መጀመሪያ ገደማ አዳዲስ ዕንግዳ
ግን ወደ ቢታቸው አልመጣም። ቤተ ክርስቲያን ስትሄድ ገበያ ስትወጣ፣ በቤተ መንግሥት አካባቢ ስትገኝ
የሚያጋጥሟት እነዚያ የተሽሞነሞኑ የጎንደር ወይዛዝርት፣ የተኮፈሱ መኳንንት ለወጉ ያህል አንገት ቀልበስ
አድርገው በሩቅ ‹ጤና ይስጥልን! እንደምን አደራችሁ? እንደምን ዋላችሁ?› ከማለት በስተቀር
አልቀረቧትም። ጎንደኦች ማን ምን እንደሆነ እያጠያየቁ ነበሩ። የዘመነ መሳፍንት የሥልጣን ከዚህም
ከዚያም መጓተት ብዙ አስተምራቸዋል። ‹አይተነው ጊዜ ወዳደላበት› እንዲሉ፣ እንዲያው ለመወዳጀት
ሲባል ብቻ ዘው ተብሎ ዕውቂያ አይደረግም። በዚህ ላይ የመግደርደሩም ልማድ አለ። አንዳንድ ጊዜ ወደ
ማታ ቤታቸው የሚመጡት የገብርዬ ጦር አበጋዞችና አንዳንድ ቀን ወደ ማታ ቤታችው የሚመጡት
የገብርዬ ጦር አበጋዞችና የታንጕት ቀደም ሲል የምታውቃቸው ሚስቶቻቸው ብቻ ነበሩ።
ዐልፎ ዐልፎ ቴዎድሮስ ይመጣሉ። መስተንግዶውም፣ ጭውውቱም ከወትሮው የተለየ አይደለም።
ስለ ወደ ፊቱ ያወጋሉ፤ ይመካከራሉ፤ ይከራከራሉ፤ በመካከሉ ያለፈ ትዝታ ያወሳሉ። ቀልድ ወይም
ተረብ ቢጤ ጣል ጣል የሚያደርግም አለ። አብዛኛው ግን፤ ቁም ነገር ብቻ ነው። ቴዎድሮስ ስለ ዘመቻ
በሚያወጉበት ጊዜ ዐይናቸው እንደ ጧፍ የሚበሩ፤ ግድግዳውን አልፈው አድማስ የሚመለከቱ ይመስላሉ።
በእንደዚህ ጊዜ ታንጕት፤ አድናቆት አይሉት አዘኔታ አንዳች ዐይነት ስሜት ገረፍ ያደርጋታል።
ከሕፃንነቷ ጀምሮ አብራችወ ኑራለች። አሳድገው ለገብርዬ ድረዋታል። ግን ስለ እርሳቸው ያላት ስሜት
ዐልፎ ዐልፎ ግራ ያጋባታል።
ሴቶቹ፤ ለብቻቸው ወደ አንድ ጥግ ሆነው ዝም ብለው ከማዳመጥ ወይም እርስ በርሳቸው የባጥ
የቆጡን ከመንሾካሾክ በተቀር በወንዶቹ ጭውውት አይገቡም።
አንድ ቀን እንደዚሁ ራት ተበልቶ ሲጨዋወቱ ለማቆላመጥ ባወጡላት ስም «አንጓች?» ሲሉ
ጠሯት። በዚህ ስም ሊጠሯት መጀምሪያ ያወጡላትን ቀን ብዙ ጊዜ ትዝ ይላታል። በወይኒ መንገድር
እናቷ ታማ ቤት ከዋለች በኋላ ነው። ያን ጊዜ ስሙን ባታውቀውም የበፊት ካሣ፤ የአሁኑ ቴዎድሮስ
ከአንድ ሦስት ሰዎች ጋር ቤታቸው ይመጣል። ደጅ ተቀምጣ ትጫወት ነበረ። ‹ነይ ሳሚኝ አንቺ› ሲል
ይስማትና ቤት ይገባል። ከእናትዋ ጋር ረዘም ያለ ጊዜ ቆይቶ ሲወጣ፤ ከምትጫወትበት ቆርጠጥ ብሎ
ይቀመጥና ጉንጭዋን እያሻሸ፤ «ስምሽ ማነው የኔ ድማም?» ሲል ይጠይቃታል፤ ትነግረዋለች። «እኔ
ደግሞ አንጓች ነው የምልሽ።» አንዱን ሰውዬ እንዲሰጣት ያዘዋል። ከዚያም ዳቦ ቆሎውን በቀሚሷ ጫፍ
እያሲያዘ፤ «ስታድጊ ዳቦ ታነጉችልኛለሽ። እሺ?» አልትና ሔደ።
«አቤት! አባ ታጠቅ» አለች ታንጕት ከትዝታዋ ስትመለስ።
«ጎንደርን ተላመድሽው?»
«ኧረ እኔ እንጃ!» አለች የምትመልሰው ግራ ተጋብቷት።
«አይዞሽ ትለምጅዋለሽ። ጎንደሮች አውሬም ያስለምዳሉ። ግና ዋ! ዋ! እነሱን እንዳትመስይ
ወይም ደግሞ ወዬ በነገር እንያደጠምዱሽ! ኋላ ነግሬሻለሁ» አሏት በቀልድ ማስፈራራት።
«እኛ ምንድን ነን አባ ታጠቅ?» ስትል የእንግዳ ምሽት ከጥግ ጠየቀች። እንግዳን ከማግባቷ በፊት
ጎንደር ተወልዳ ያደገች የመኳንንት ዘር ነበረች።
«ኧረገኝ!» አሉ ቴዎድሮስ የደነገጡ መስለው እየሣቁ። ሌሎችም ሳቁ። «አንቺና ተዋበችማ እኛን
መስላችኋል፤ አጥምቀናችሁ!»
አንዳንዶቹ አንዳንድ ቀልድ ካከሉበት በኋላ ያበቃለትና የተረሳ ይመስል ጭውውታቸው ወደ ቁም
ነገሩ ተመለሰ። ድጋሚ አላነሡትም።
ታንጕት ግን ጨዋታው፤ ቀኑም ከዐለፈ በኋላ እንዳንዳች ሟርት፤ እንደ መጥፎ ትንቢት በሐሳብዋ
መጉላላቱ አልቀረም። ‹ምን እንዳያደርጉኝ ነው? ምን እንዳላደርግ ነው? ወይስ ምን እንዳልሆን ነው?›
የዕለት ሥራዋን ስታከናውን ጥያቄዉን ለራስዋ በሐሳብዋ ጠይቃ መልሱን ታሰላስላለች፤ አይመጣላትም።
ግን የጎንደር ወይዛዝርት፣ መኳንንትና ካህን በድንገት ሲያጋጥሟት አንዳች ዐይነት ስሜት ያድርባታል።
ጥላችም አትለውም፤ ፍቅርም አትለውም፤ እየቀፈፋት፤ መጠጋት እየፈራችው ገልጦ የማወቅ ዐይነት
ፍላጎት ነው። ስታብላላው፤ እያደርም እየረሳች ስታስታውሰው ሰነባበተች። በቤት ሥራዋ በማተኮር ጨርሶ ልትረሳውም ትሞክራለች። እንደዚያ ሰሞን ፈትላ፤ እንደዚያ ሰሞን ስንት ዐይነት ስፌት ወጥና
አታውቅም። በዚያ የጎንደር ወይዛዝርት መኻል የገብርዬ ጠባይ፤ ለእርሷም ያለው ስሜት ይበልጥ ያማረ
እንጅ የተለወጠ ሆኖ አልተሰማትም።
መዋል ማደር መቸም መልካም ነውና ቀናት ሲያልፉ፤ ጊዜዋን በሆነውም ባልሆነውም ሥራ
ስታላልፍ፤ ሐሳቧ ደብዘዝ ማለት ሲጀምር፤ መላ ጎንደርን በወሬ ያተራመሰው የሹም ሽር ነገር መጣ።
ቴዎድሮስ፤ ብዙ ጊዜ በውጭ ችሎት ሳይቀመጡ ከውስጥ ብቻውን፤ አንዳንድ ጊዜም ከቤል
እየዋሉ መሰንበቻቸውን ታንጕት ቤተ መንግሥት ስትሔድ ብታውቀውም በከተማው የሚነፍሰውን ወሬ
የምታመጣላት፤ ከአካባቢው የሙያ መሰሎቿ ጋር በቀላሉ የተለማመደችው ገረድዋ በለጡ ናት። ወጣ ብላ
በገባች ቁጥር፤ እንደ አፋራም ሕፃን መዳፍዋን እያፋተገችና ዐይንዋን እያቅለሰለሰች የሰበሰበችውን ወሬ
ትነግራታለች።
ጎንደር በወሬና በጥይይቆሽ ሲታመስ ሰንብቷል። ከጎጃም አባይ ባሻገር ድረስ ድፍን በጌምድርን
ይዞ፤ ከወሎ እስከ አማራ ሳይንትና እስከ ዋድላድላንታ - እስከ ቦረና አጠቃቅሶ በትግሬ የደጃች ውቤ
ግዛት የነበረውን ሁሉ ይዞ፤ በምዕራብ ቆላ ያለውን፤ የጭቆ፤ የቋራ፤ የአዳኝ አገር ማዶ እስከ ገዳሪፍና
እስከ ስናር ያለውን ሁሉ አጠቃሎ፤ የሚገዛ፤ ‹ገዥ ነኝ› የሚል፤ ግዛት ለማግኘት የሚመኝ መኳንንትና
ጭፍራ ያለው የጎበዝ አለቃ ሁሉ ጎንደር ከተማ እየገባ ተከማችቷል። በቀድሞው ለየብቻው የነበረ የሦስት
መስፍን አገር ገብሮ፤ ከትቶ በአንድ ጊዜ ሲገባ አዲስ ነገር ከመሆኑ ሌላ አመጣጡም አዲስ ነገር
ሆኖበታል። ዱሮ የስሜኑ ደጃች ውቤ፤ ለመታረቅም ለመስማማትም ጎንደር ሲገቡ ነጋሪታቸውን
እያስጎሸሙ ነበር። እነደጃች ማሩ፤ እንደ ደጃች ክንፉ፤ እነ ደጃች ተድላ ጓሉ እንደዚሁ እስከ ፋሲል ግቢ
አጠገብ ነጋሪት ያስመቱ ነበር። አሁን ግን መኳንንቱ ነጋሪት ማስመታት ቀርቶ፤ አብዛኛው ሠራዊቱን
በአንገረብና በቀሃ ወንዝ መስክ በድንኳን ሁላ እንደ ሌጣ ከብት ነዳው!› ይባላል።
እንደ ነገ ስብሰባ ተጠርቶ የሹም ሽሩ ሹክሹክታ፤ ሲዛመት አደረ።
‹ሰምተሃል? እገሌ የራስ ወርቅ ሊያስር ነው!› ይላል አንዱ። ‹ደጃዝማች እገሌ ከርብ እስከ
መተማ ሊሾም ነው ተባለ!› ይላል ሌላው። ‹አትለኝም! ኧረ በየት ወንድነቱ?› ሲል አድማጩ ይገረማል።
‹ደጃዝማች እገሌ ወህኒ አምባ ተላኩ አሉ?› ሲል አንዱ መርዶ ያሰማል።
‹አይ አበሳ!› ይላል ሌላው በጭንቀት።
እያንዳንዱ የወደደውን ይሾማል፤ የጠላውን ይሽራል፤ ያግዛ፤ በምኞቱ።
አንድ ቀን ሲቀር ታንጕት ስለ ሹመቱ ገብርዬን ጠየቀችው።
«ምን አስጨነቀሽ?» አላት በማቃለል።
«አይ እንዲያው ወሬው ገርሞ ነው አንጂ!» ከተማው ሁሉ ሌላ ነገር የለውም አሉ። ለመሆኑ
አንተ ምን ትሾማለህ»
«ወቸው ጉድ! ደግሞ እኔዉ፤ ራሴው ነኝ የምመርጠው! ለሁሉስ ነገ ትደርሽበት የለ?» አለና
ጉንጯን ቆንጠጥ አደረጋት።በነጋው ጧት ገብርዬ ከሐር እጀ ጠባብና ሱሪው ላይ የአንበሳ ለምዱን ደርቦ፤ አንፋሮውን ደፍቶ
በግራ ጎኑ ጎራዴውን በቀኝ ጎኑ ሽጉጡን ታጥቆ፤ ታንጕትን በሐር ጥልፍ ቀሚስና ኩታዋ ላይ ጎንደር
መጥታ ከሰነበተች በኋላ፤ ‹ኧረ ጎንደሮች የቋራ ቡትቷም ብለው እንዳይሰዱብሽ!› በለው ቴዎድሮስ
የሰጧትን ሐር ካባ ወደ ቤተ መንግሥት ተጓዙና ሲገቡ፤ እርሱ ወደ መሰሎቹ እርሷም ወደ መሰሎቿ
ተለያዩ።
መኳንንቱ ከነሠራዊቱ ከሠፈሩበት ወይም ከዐረፉበት እየመጡ ወደ ዋናው የፋሲል ግምብ አዳራሽ
ቡ። ትርምስ፤ ግርግር፤ ጩኸት የለም። ከፋሲል ግምብ ግቢ ብዙ ሰዎች ቢኖሩም፤ ብዙም ሳይንቀሳቀሱ
ብዙም ሳይነጋገሩ በታዛቢነት የሚያስተውሉ ይመስላሉ።
ሁሉም ገብቶ በአጋፋሪው እየተመራ በየሥፍራው ከተቀመጠ በኋላ፤ ቴዎድሮስና ተዋበች አቡነ
ሰላማ ትንሽ ቀደም ብለው፤ ገብርዬ ከገሞ፤ ከዓለሜና ከሌሎችም ጋር ሆነው፤ እንደ ሥርዓቱ እስኪቀመጡ
አዳራሹ የነበረው ቆም ብሎ ተቀበላቸው። ታንጕት ይህንን አዳራሽ ቀደም ሲል ደጋግማ ያየችው ቢሆንም፤
ከዚያ በፊት አይታ በማታውቀው ይህንን በመሠለ ሥነ ሥርዓት ከፊትዋ ሲደቀን፤ የመጀሪያ ጊዜዋ ስለነበር
የሚስብ የሚማርክ ትርዒት ሆነባት። ከውስጥ በኩል የሚሰናዳውን፣ የሚቀራርበውን ለመርዳት ወጣ ገባ
ብትልም ዐይንዋ፣ ጆሮዋ፣ ሐሳብዋ ሁሉ በአዳራሹ እንቅስቃሴ ላይ ነበር። ለምን እንደሆነ ራስዋም
ምክንያቱ አልገባትም። ገብርዬ እንደሆነ መሾሙ እንደማይቀር ታውቃለች።
ሊጋባው ከቴዎድሮስ አጠገብ ቁሞ፤ የመኳንንቱን ስም እየጠራ ማዕረጋቸውንና ግዛታቸውን ወይም
ሥልጣናቸውን ከፍ ባለ ድምፅ ሲናገር፤ አንድ በአንድ ብድግ እያሉ ለቴዎድሮስ እጅ ይነሡና ተርታ
በቆሙት አጋፋሪዎች እየተመሩ የዕቃ ቤቱ ሹም ወደ አለበት ክፍል ይሔዳሉ። ከዚያም ቀሚሳቸውን
ለብሰው ሲመለሱ እንደገና እጅ ይነሣሉ።
ሴቶቹ፤ የየራሳቸውን ባል ወይም ወገን ሲሾም ፈንደቅደቅ ሲሉ ታንጕት አብራ ብታጅብም፤
በአብዛኛው የሚሰማት ከተካፋይነት ይልቅ የተመልካችነት ስሜት ነበር። ገብርዬ፤ በፊታውራሪነት ማዕረግ
የጦር አዝማች ተብሎ ሲሾም ብቻ ልብዋ ትርትር አለባት። እንግዳ ‹ራስ› ሲባሉ። የገብርዬ ሹመት
ቢያስደንቃትም፤ ስሜቷ የደስታ ይሁን የድንጋጤ በትክክል አልታወቃትም።
እያንዳንዱ ሹመት ሲነገር መኳንንቱ እርስ በርሱ ይተያያል። አንዳንዱም ቀሚሱን ለብሶ ወደ
ቦታው ሲመለስ ከንፈሩን እንደመንከስ ሲያደርግ ያስታውቃል። እንደ በፊቱ ራስ ወርቁ፣ እንዲያምስ ኢል
የጋብቻ መደለያው፤ ሥልታን ባይኖርበትም ሲጠሩት የሚከብድ ግዛት የሚሰጥ የመሰላቸው ብዙዎች ነበሩ።
አብዛኛዎቹ ያሰቡትን አላገኙም።
ብዙውን መኳንንት ይባስ ያናደደው ሌላም ሹመት ተከተለ። ሊጋባው ላንዳፍታ ገታ አለና፤ ‹ልጅ
ዮሐንስ› ብሎ ሲጣራ ጆን ቤል ተነስቶ እጅ ነሳ። መኳንንቱ ሁሉ የሚሰማውንና የሚያየውን ማመን
እስኪያቅተው ድረስ ተደመመ። ሊጋባው ‹ሊቀ መኳስ› ብሎ ሲናገር ቴዎድሮስ የመኳንንቱ ስሜት
ገብቷቸው ፈገግ አሉ። ስምምነት የሚጠቅ ይመስልም ወደ አቡነ ሰላማ ዘወር ብለው ተመለከቱ።
ሹመቱና ሽልማቱ አብቅቶ፤ ለስሙ ‹ቁርስ› የተባለ ግን ከምሳ የከበደ የእልፍኝ ግብር ሲቀርብ
የብዙው ሆድ ተዘግቶ ነበር። አብዛኛው የፈለገውን አለማግኘቱ ሳይናስ፤ ባሕር አቋርጦ  የውጪ አገር ሰው ‹ሊቀ መኳስ› መባሉ እንደ ትልቅ ክህደት ቆጠረው። ጆን ቤል ከቴዎድሮስ ዘንድ ባለሟልነቱን
ካጠበቀ ወዲህ ተጠምቆ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት መቀበሉን ግን ብዙዎች አያውቁም ነበር።
መጠጥ አሳላፊዎች አስቀድመው እንደታዘዙ ያህል መኳንንቱ ምግቡን ችላ ማለት ሲጀምሩ
ማሳለፉን ትተው በየጥጉ ቆሙ። ሊጋባው አጨበጨበና፤ ‹እስቲ አንደዜ ዝም በሉ!› ሁሉ ከሐሳቡ ጋር
ስለሚነጋገር በፊትም ቢሆን ብዙ ድምፅ አልነበረም። ታንጕትም ተረጋግታ ሁናቴውን ትከታተል ጀመር።
ቴዎድሮስ፤ ዐይናቸውን ተራ በተራ በእያንዳንዱ መኳንንት ላይ አሳረፉት። ሐሳባቸውን
ለመገመት ከመሞከራቸው ጋር፣ ‹ሐሳቤን ተረዱልኝ፤ ፍቅራችሁንና ታማኝነታችሁን ስጡኝ› በሚል
አስተያየት አንገታቸውን ቀን አደረጉና ፈገግታ አሳዩ። ምናልባት ራሳቸው አይታወቃቸውም እንጂ፤
ከፊታቸው ቀድመው ሞትን የሚጋፈጡ ተከታዮች ካፈራላቸውም የተፈጥሮ ወይም የመሪነት ችሎታ ጋር፤
ስስና ዘርጋ ያሉትን ከንፈሮቻቸውን ሲገልጡ ብቅ የሚለው ፈገግታቸውና ጉድጉድ ብለው እንደቡኸር
ዐይን የሚቁለጨለጩት ዐይኖቻቸው አስተያየት፤ አንዳች የመሳብ ኃይል ነበራቸው። ተመልካች፣ በፍቅርና
ትህትና እወነተኛነትና ቆራጥነት አዋሕደው የሚገልጹ መስሎ ይሰማዋል። በአሁኑ ጊዜ ግን ይህንን ተአምር
አልሠራላችሁም። አብረዋቸው ከተነሱት የቅርብ ባላሟሎቻቸው በስተቀር፣ ሹመት በዘር፤ በቀሚስ ለስም
የጠበቁት አብዛኞቹ መኳንንት የሕሊናቸው ትዝብት አገጫቸውን ወደታች እንደ ጎተተው ያህል
አንገታቸውን አቀረቀሩ። ከዘመቻ በፊት፤ ከድል በኋላ፤ የጦር አበጋዞቻቸውንና ሠራዊታቸውን በዙሪያቸው
ሰብስበው መወያየት የሚያዘወትሩት ቴዎድሮስ፤ በአሁኑ አዳራሽ ውስጥ አብዛኛው የቅሬታ ስሜት
መታየቱን መገንዘባቸው አልቀረም። በዙሪያቸው ያለውን ያቀረቀረ ፊት ሲያስተውሉ ለሚያቀርቡት ሐሳብ
ተስማሚ ጊዜ አለመሆኑ ተሰምቷቸዋል። ነገር ግን፤ የዘመነ መሳፍንት ዝብነና ላስለመደው መኳንንት
ቅብጥብጥነት፤ ፊት መስጠት፤ ‹ባለጌን ቢያከብሩት የፈሩት ይመስለዋል› እንደሚባለው የሚሆን
መሰላቸው። ከዚህም በቀር ከጆን ቢለ ጋር ብዙ ከተመካከሩና ከተወያዩ ወዲህ፤ ሐሳባቸው ጊዜ
እንደማይሰጥ ምጥ ከውጽጥ ይገፋቸው ነበር።
«እህህህ!» ሲሉ ጉሮሮዋቸውን ጠረጉና፣ አሁንም ሰዉን እንደገና ቃኝተው ንግግራቸውን
ጀመሩ። «ታሁን በፊትም ቢሆን በዚህ አዳራሽ ሹም ሽር ሲደረግ ቀሚስ ሲሰጥ የኖረ ነው፤ አዲስ
አይደለም። እነ ራስ አሊ፣ እነ ራስ ጉግሣ፣ እነ ራስ ይማም፣ እነ ራስ ማርዬ፣ ኧረ ስንቱ ተቆጥሮ!
አገሬን ላቀና ወገኔን በመልካም ላስተዳደረ ስለሆነ የምሾመው የምሸልመው ለዚህ ይረዳኛል የምለው እንጂ
ሌላውን አይደለም።
በመከፋት አቀርቅሮ የነበረው መኳንንት፣ በማድነቅ ሳይሆን ጉድና መዓት እንደ ሰማ ያህል ቀና
ብሎ እየተመለከተ ያዳምጣቸው ጀመር።
«እናንተም ቢሆን ታሁን በፊት ተሹማችሁ የነበረ አላችሁ። ታሁን በፊት አገር ተሹማሁ
የማታውቁም አላችሁ። ዛዲያ የዛሬው ሹመት እንደ ድሮው ልትቀማጠሉበት ሳይሆን ሕዝቡን
እንድታስተዳደሩበት፣ ዳኝነቱን በሚገባ እንድትፈርዱ ነው። ወንበዴና ወስላታን አጥፍታችሁ አገሩ ሰላም
እንዲሆን ታረጋላችሁ። የምትቀበሉት ግብርም የተወሰነ ይሆናል።»
ብዙዎቹ የባሰ በመገረም እርስ በርሳቸው ሲተያዩ፣ አማርኛ በመጠኑ የሚያውቀው ሊቀ መኳስ
ዮሐንስና አቶ ሳሙኤል ከኋላው ሆኖ የሚያስተረጉሙለት ቆንስል ፕላውንዴን በአድናቆት ራሳቸውን
ያወዛውዛሉ።
«ለዚህ ሁሉ በቅርብ እየተመካከርን የምናወጣው ሕግ አለ። ሕዝቡን የሚበድል፣ ሕግን የሚጥስ
ሹም እንደሌላው ሁሉ ይቀጣል። እንዲያውም አይማረኝ አልምረውም፣ በሾምኩት ሰው ላይ ነው ቅጣቴን
የባሰ የማከብድበት!!»
ቴዎድሮስ፣ ንግግራቸውን ተግ አድርገው እንደገና ከመቀጠላቸው በፊት መኳንንቱን ሁሉ
በዐይናቸው ቃኙት። «ከዚህም በስተቀር ወደ ሀገራችን እንዲገባ የምናስበው አዲስ ነገር አለ። ይኸውም
ሀገራችን እንደወትሮዋ ገናና እንድትሆን በማለት ነው። በዚህ ቤተ መንግሥት» አሉ ቴዎድሮስ የአዳራሹን
ዙሪያ እየቃኙ፤ «መሳፍንቱ፣ መኳንንቱና፣ ነገሥታቱ ሕይወታቸውን ለጠጅ ለጮማና ለዝሙት አውለው
ሲማግጡ ሀገራችን ኢትዮጵያ እየሟማች ሔደች።› ቴዎድሮስ አገጫቸውን እንደ ማሸት አደረጉ።
«አገራችንንም እንደ ድሮው፣ ከድሮዋም የበለጠች ገናና ለማድረግ ምን እንደሚበጀን፤ ቆንስል
ፕላውዴንና ሊቀ መኳስ ዮሐንስ በሐሳብም በምክርም ይረዱናል። የሚረዱን ወዳጅጆችን ያፈሩልናል።
ሊቀ መኳስ!» አሉ ወደ ጆን ቤል ዘወር ብለው፣ «እስቲ ለኔ ብዙ ጊዜ ያጫወትኸኝን ተዚህ ላሉት ሁሉ
ንገርልኝ!»
ሊቀ መኳስ ዮሐንስ ተነስቶ ቁሞአዲስ ከደረበው ቀሚስ በታች ድግድጉን እያስካከለ ቴዎድሮስና
ሌላውን ሁሉ እጅ ነሣ። «አባ ታጠቅ መቸም አንድ አገር ትልቅ፤ ገናና የሚሆን ሥልጣኔ ሲያገኝ ነው።
ሥልጣኔ የሚገኘው ደግሞ በትምህርት ብቻ ነው። ስለዚህ ከሁሉ በፊት ትምህርት ያስፈልጋል።» ጆን
ቤል፤ የሚጠፋውን ቃል ከአቶ ሳሙኤል እየጠየቀ፣ በሚገባ መግለጽ ሲያቅተው እንዲያተረጉምለት
በእንግሊዝኛ እየነገረ የራሱ አገር እንግሊዝ፣ በስፋትም በሕዝብ ብዛትም ስነስተኛ ስትሆን በመሠልጠንዋ
ምክንያት በእንግሊዝ ግዛት ላይ ፀሐይ አትጠልቅም? እስኪባል ድረስ የዓለምን አብዛኛ ክፍል የምትገዛ
መሆንዋን በመተረክ ሥልጣኔ የሚሠራውን ተአምር በሰፊው አስረዳ። በመጨረሻም ትምህርት የሌለው፣
ብሎ ያልሠለጠነ ሕብዝ በጦርነት እስር በርሱ ስለሚፋጅ ደካማ ሆኖ በሠለጠነ አገር መገዛቱ እንዳማይቀር
ተናግሮ አበቃ።
ቴዎድሮስ፣ «ዛዲያ ስለዚሁ ጉዳይ ምን ታስባላችሁ?» ሲሉ ለሁሉም በደፈናው ጠየቁ።
በተለይ በነጻድቁ ዮሐንስ ጊዜ ዳኝነትም፣ አስተዳደርም ተዘውትሮ ይሠራበት የነበረው የሸንጎ
ውይይትና ትችት በዘመነ መሳፍንት ቀርቶ ወደ መረሳቱ ደርሶ ስለ ነበር፤ በመፍራትና በመፈራራት ሁሉ
ለጥቂት ጊዜ ዝም አለ።
«ሊቀ መኳስ ዮሐንስ እንዳጫወቱኝ የሱም ነገር ነገሥታትና ንግሥታት የሚሠሩት ነገር ሁሉ
በመኳንንቱ እየተመከረበት ነው» አሉ። «በኛም አገር፣ ‹አንድ እንጨት አይነድ፣ አንድ ሰው አይፈርድ›
እንደሚባለው ትልቅ ያገር ጉዳይ ስለሆነ ተዚሁ ያለነው ሁላችንም ብንመካከርበት መልካም ነው» ሲሉ
ቴዎድሮስ በድጋሚ አደፋፈሩ።
ፊታውራሪ ሙጤዬ፣ የኩታውን ጫፍ ጎትቶ እያጣፉ ሁሉት ሦስት ጊዜ ለጥ ብሎ እጅ ነሳ።
ጥቅሻ የክንድ ጉሽሚያና ሹክሹክታ ባንዴ ተዳርሶ ከኋላ ከፊት፣ ከቀኝ ከግራ፥ ያለው ሰው ሁሉ ወደርሱ
ዞረ። በአደባባይ ሳይሾም እንዳመቸው ራሱን ‹ፊታውራሪም ግራዝማችም፣ ደጃዝማችም እያለ ሲሠይም
ኑሮ፣ አሁን የፊታውራሪ ቀሚስ በመስጠቱ ይደሰት በትክክል ባይገመትም፣ ከዚያው ከጎንደር ዐለፍ ብሎ
የፈንጠር ተወላጅነቱ ከአዳባባይ ስለሚለይና በአነጋገር የሠለጠነ በመሆኑ፣ የሚያውቁት ሁሉ የሚለውን
ለመስማት ጓጉ። «ጃንሆይ!» ሲል ጀመረ፣ አሁንም ደግሞ እጅ እየነሣ። «መቸም እኝህ የባህር ማዶ ሊቀ መኳስ ስለ ውቀት ጠቃሚነት የሰጡን ምክር እንዲህ ነው አይባልም። ዕውቀት ጠቃሚ መሆኑን መቸስ
ማይ ያብላል?»
ከባህር ማዶ ‹የባህር ማዶ ሊቀ መኳስ› ሲል አሽሙሩ ገብቷቸው በጎሪጥ ተያዩ።
«ዕውቀቱማ መቸም ለሰማዩ ለምድሩም ይበጃል።» አሁንም እጅ ነሣ። «ዛዲያን አሁንም የቅኔ
የትርጓሜ፣ ያቋቋም የዝማሬ መዋእሲት፤ ሊቃውንት የሞሉባት አገር ናት። ሌላው ቀርቶ የጎንደር
ሊቃውንት ለድፍን ኢትዮጵያ ኧረ እንዲያው ሊቀ መኳስ ዓለም ለሚሏት አይተርፉም? እና ጃንሆይ
ዕወቀት ያላቸው ሊቃውንት ካሉን እንዴት ነው ነገሩ ደንቆሮች እንባላላን። ወይ ብዬ ነው!» ሲል
በንግግሩ ማሳረጊያ እጅ ነሣ።
ሊቀ መኳስ ዮሐንስ መልስ መስጠት ቃጣና አቅማማ። የቀለምና የሃይማኖት ትምህርት ብቻውን
በቂ ዕውቀት ሊሆን እንደማይችል ለመግለጽ ትክክለኛ ቃል ጠፍቶት ደንቆሮ ማለቱ ትልቅ ስሕተት
መሆኑን ተገንዝቧል። «እኔ ደንቆሮ ለማለት -» ብሎ መልስ ሲፈልግ ቴዎድሮስ ቀበል አደረጉለት።
«መቸም ሊቃውንትና ካህናትማ ሞተልተውናል» አሉ ቴዎድሮስ በሽሙጥ ዐይነት ወደ አቡነ
ሰላማ እየተመለከቱ። «ፊታውራሪ እንዳለው ሊቃውንት እንዳሉን እውነት ነው። ንግስ፤ የማያውቁትን
የግዕዝ ቁንቋ የሚያነቡ፤ የሚያስነቡትን የማይጽፉ፤ ትርጉሙም ምኑም ሳይገባቸው የሚያዜሙ የሚጸልዩ፤
እንዲያው ሲጠይቋቸው የሚያነበንቡት ነገር ርግማን ይሁን ምርቃት፤ ውግዘት ይሁን ምስጋና መናገር
የማይችሉት ስንት ናቸው? ውሸት አናንገር ከተባለ አብዛኞቹ አይደሉም ፊታውራሪ?»
ፊታውራሪ በመልሱ ትንሽ አቅማማ። «በመላእክት ቋንቋ መናገር መቸም እኔ ዕውቀት እንጂ
ድንቁርና አይመስለኝም» አለ። በሹመቱ የተከፋ መኳንንት መልሱ ቁጭቱን ያወጣለት ይመስላል
በአድናቆት ራሱን አወዛወዘለት።
ቴዎድሮስ፣ ነገሩን ፍሬ ፈርስኪ በማድረግ ዐይነት እንደመሣቅ አሉ። «ነገሩስ ያባቶቻችን ቋንቋ
ነው። የመላእክት ቋንቋስ ቢሆን ትርጉሙን፣ ምስጢሩን ካላወቁት እንደ ደመ ነፍስ እንስሳት ተንጫጩበት
እንጂ መቸ ተነጋገሩበት?» ወደ አቡነ ሰላማ ዘወር ብለው ጠየቋቸው። «ምን ይመስልዎታል አባታችን»
ሳይፈልጉ ጥያቄው የተሰነዘረባቸው አቡነ ሰላማ ከሪዛቸው ጋር ጥቂት አጉተመተሙ። ግዴታ
ካልሆነባቸው በተቀር ከቴዎድሮስ ጋር ብዙም መነጋገር አይፈልጉም። ደጃች ውቤም የሚያነጋግሩዋቸው
እንደ አባት እያከበሩ፣ እያባበሉ ስለ ነበር ጭውውታቸው ይጥማቸዋል። ቴዎድሮስ የሚያነገግሩባቸውና
አንድ ነገር የሚጠይቋቸው ግን በሚያፋጥጥ የክርክር መልክ ነው። «መቸም....መቸም» አሉ ሪዛቸውን
ሳብ ሳብ እያደረጉ፣ «የእግዚአብሔርን ቃል ከአጥናፍ አጥናፍ የሚሰብክ ካህናት ሊመሰገኑ እንጂ ሊነቀፉ
አይገባም።
ቴዎድሮስ ድንገት ከግራሜ ፈንቅሎ የመጣ ሣቃቸውን ለማመቅ ይምሰል አፋቸውን በግራ
እጃቸው ከደን አደረጉ። «እሱንማ መቸ አጣነው፤ አባታችን። ነገር ግናስ እየጠመጠመ ቄስ፤ ካህን ነኝ
ባይ፣ ቆብ እየደፋ መነኩሴ ነኝ ባዩ ሁሉ፣ በዚህም ልቆ ርቆ ካገር ማዶ፤ ባሕር ተሻግሮ በሃይማኖት
መሪነት የሚመጣው ሁላ፣» ቴዎድሮስ ሆን ብለው ከዚህ ላይ ንግግራቸውን ረገጥ ረገጥ አደረጉት።
«የዓለሙን ነገር ሁሉ ትቶ የእግዚአብሔርን የክርስቶስን ቃል ለማዳረስ የዘመተ ነው ብለው ያምናሉ? ሲሉ ከእስክንድርያ ከመነሳታቸው በፊት ብዙ ሺህ ብር እየተከፈላቸው ከመጡም በኋላ በኢትዮጵያ ቤተ
ክርስቲያን በፊት ብዙ ሺህ ብር የተከፈላቸው፣ ከመጡም በኋላ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የበላይነታቸው
የሚሰበስቡትን ስፍር ቁጥር የሌለው ሀብት ወደ አገራቸው የሚያግዙ መሆናቸውን በሚጠይቅ አስተያየት
ተመለከቱዋቸው።
አቡነ ሰላማ፤ የቴዎድሮስን መቅን ዘይቤ በትክክል ባይረዱትም በነገር የተነኩ ወይም የተደፈሩ
መሆናቸው ከሰዉ አስተያየት ስለተሰማቸው ያወለወለ ያ ቀይ ፊታቸው የባሰውን የተሰረበ ጉበት መሰለ።
ግን መልስ አልሰጡም። ነገሩ የገባው በማዘን ከንፈሩን ሲመጥላቸው፣ ሌላውም ለቅጽበት የራሱን ቅሬታ
ረስቶ በወርደታቸው እንደ መሣቅ ሲቃጣው፣ ጸጥ ብሎ የቆየው አዳራሽ ሁካታ አስተጋባበት።
ቴዎድሮስ፣ ሁኔታውን በፈገግታ ለጥቂት ጊዜ ከተመለከቱ በኋላ ዐይናቸውን ወደ ሊጋባው መለስ
ሲያደርጉ «እሺሺ----- እሺታ! እሽታ! ሲል አጨበጨበ። ወዲያው አዳራሹ ጸጥ አለ።
«የጻድቁን የኃጥኡን ጉዳይ አሁን ለርሱ ፍርድ ትተን እንለፈውና፣ እስቲ ሊቀ መኳስ ስለ
ትምህርትና ስለ ዕውቀት እስታሁን በኛ ነገር ስለሌለው እንመካከርበት» ሲሉ ቴዎድሮስ ቀኝ እጃቸውን
እንደ መዘርጋት አደረጉ።
አሁንም ብዙ መኳንንት በማመንታት እርስ በርሱ ሲተያይ፣ ግዙፍ ቁመናው ቂላ ቂል
የሚያስመስለው ቀኛአዝማች አሥማረ ብድግ ብሎ እጅ ነሣ። «ጃንሆይ መቸም የዚህ የኛ አገር ትምህርት
ርባና የሌለው ተሆነ፣ የባሕር ማዶውን ዕውቀት ያሉትን እንዴት ነው የምናመጣው?» እንደ ገራም
አነጋገሩ ጥያቄው አለማወቅ ይመስላል። ቆዳው አሳሳች መሆኑን በቅርብ የሚያውቁት ግን፣ ምክንያት
ያለው ጥያቄ እንደሚሆን አላጡትም። ምንም ቢሆን ከደጃች ውቤ ቤት ያደገ ሰው ነው።
ቲዎድሮስ እንደ መሣቅ አለ። «ቀኛዝማች አሥማረ፣ መቸስ በወርቅ ተገዝታ በስልቻ ተቋጽራ፣
በከብት ተጭና የምትመጣ እንዳትመስልህ!»
«እዛዲያ እንዴት ነው ጃንሆይ?» ሲል አሁንም በገራገር አነጋገር ጠየቀ።
«ነፍጥ መድፍ የሚሠራ አናጢነት፣ ግንበኝነት አንጥረኝነት፣ ሌላውም ጠፍ ከመሆን የደረሰች
አገራችንን ለማልማት፣ ሕዝብን ለማሰልጠን የሚያበጅ ሙያ የሚያስተምሩ ፈረጆች ለማምጣት አስበናል።
በዚህ ረገድ ክርስቲያንዋ የንግሊዝ ንግሥት ግርማዊት ቢክቶሪያ ልትረዳን እንደምትችል....» እያሉ
ቴዎድሮስ ወደ ሁለቱ እንግሊዛውያን ዘወር ብለው ተመለከቱ። «ቆንስል ፕላውዴንና ሊቀ መኳስ ዮሐንስ
አጫውተውኛል።»
መኳንንቶቹ እርስ በርሳቸው ተያዩ። ‹ፈረንጅ - ፈረንጅ› የሚለውን ቃል በሹክሹክታ
ተቀባበሉት።
«አንጥረኛና ግንበኛ ባገራችን መች አጣን፣ ጃንሆይ» የሚል ጥያቄ ከሌላ መኮንን ቀረበ።
«አሄሄ!» አሉ ቴዎድሮስ በቅሬታ መልክ። «ያገሬን ሰው መንቀፍ አይሁንብኝ እንጅ ለጎንደር
ወይዛዝርት አምባርና አልቦ ከመሥራት የሚያስፈልገውን እንደ ባለሙያ ቆጠርከው? አሁን ማ - ይሙት
ከስንት ስንት ዓመት በፊት ባባቶቻችን ጊዜ የተሠራውን ይህንን የመስለ ግንብ የሚሠራ ግንበኛና አናጢዎችንም ዛሬ አለ? እስቲ አምጡልኝና ላሠራው፣ ልሹመው!» በመጋበዝ ወደ መኮንኑ እጃቸውን ዘረጉ። መረታቱን
የተቀበለው መኮንን እጅ ነሥተው ተቀመጠ።
«ጃንሆይ! እንዲያው» ሲል ከቀድሞ ፊታውራሪነት አሁን የግራዝማች ቀሚስ የተሸለመው
ወገሬው ጎበና የሚጠይቀው ነገር የጠፋው ይመስል ከአጠገቡ የተቀመጡትን ሰዎች በዐይኑ ፍለገ።
«እንግዲያው እነዚህ ፈረንጆች ያሏቸው ለማስተማር የሚመጡት፣ እስላሞች ናቸው ወይስ አረመኖች?»
ቴዎድሮስ፣ ሐሳብ የሚጠይቁ ይመስል ወደ አቡነ ሰላማ ተመለከቱ። ጳጳሱ ግን እንዳልሰሙ
በመምሰል አንገታቸውን ቀርቀር አድርገው ጭጭ አሉ። አብዛኞቹ መኳንንት ነገሩ ገባቸው።
ቴዎድሮስም ጥቂት አሰቡበት። በአቡነ ሰላምና በካቶሊክ በአባ ያዕቆብ እንደዚሁም በእነሱና
‹በፕሮቴስታንት› በሚባሉት ሚስዮናውያን መካከል ያለውን ጥላቻ አሳምረው ያውቁታል። ከዚህ ሁሉ
በላይ ግን እንደ ራሳቸው ስሜት የሚያሳስበው አደጋ ሌላ ነው። ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ጉዳይም ከንዚህ
ጠብ ሁሉ በላይ ነው። ግን እዚያ ከፊታቸው የተሰበሰበው መኳንንት ይህንን ነገር አሣምሮ አይረዳውም።
ጎጂውንም፣ ጠቃሚውን የሚያውቅ የተማረ የሠለጠነ ቀልበስ አድርገው ላንዳፍታ እንደመቆዘም አሉ።
«መቸም አገራችን እንውረር፣ እንግዛ የሚሉት ግብጦች፣ ቱርኮችም ያው እስላሞች ስለሆኑ፣ ከእነሱ ጋርማ
እንዴት እንስማማለን ብላችሁ ነው? ከሃይማኖታቸው እንኳን ነገር የለንም በክፋት ስለመጡብን ነው እንጂ
አሁን እኛን እንዲያስተምሩን ያሰብናቸው ግን ክርስቲያኖች ናቸው። ግና ክርስቲያንነታቸው እስተዚህ
ተኛም ቅባት ጸጋ እንደሚባለው ስለሆነ ተዚህ ምናለን?» አሉና መኳንንቱን በአጠቃላይ ትኩር አድርገው
ተመለከቱ። የተቀበላቸው አስተያየት እንደ አለት የጠጠረ ነበር።
«አባታችን፣ አንድ ይበሉኝ እንጂ!» አሉ ቲዎድሮስ ኮስተር ባለ አነጋገር።
አቡነ ሰላማ ሪዛቸውን እየጎተቱ በሐሳብ ስልምልም አሉ። ከየትም ተነሥቶ፤ ራሱን እምሪ አድርጎ
እንዳሰብኩት፣ እንደፈለግሁት ልሥራ ከሚል ቴዎድሮስ ጋር ፊት ለፊት መጣላቱንና መጋፋቱን ቀርቶ፣
መከራከሩን ስለ ሚፈሩ ት እያስታመሙ ቆይተዋል። አሁን ግን ከመኳንንቱ በቀረበው ጥያቂ መሠረት፣
አስተያየታቸውን ከተጠየቁ መልሳቸውን መስጠት የተሻለ አጋጣሚ መሆኑ ታያቸው። የአብዛኛው መኳንንት
ስሜት ገብቷቸዋል። በዚህም ላይ የቴዎድሮስን ፈቃድ መፈጸማቸው ነው። «መቸስ እሱማ አረመኔና
እስላም እስላምና ክርስቲያን አንድ አይደለም፣ ተየት ተቀራርቦ። ግና ደሞ ክርስቲያን በሚባሉት መካከል
የማይስማሙበት ብዙ፤ ብዙ፣ አሉና ከዚህ ላይ ራሳቸው ቃላቶችን በመርገጥ፣ እንደ አስተርጓሚ
የሚረዳውም ረጂያቸው ጣታቸውን በመቀሰር «ጥልቅ ምስጢር አለ» ሲሉ አስገነዘቡ። «ተዚህም የተነሳ
ልክ እኛ የማርቆስ መንበር ሆነን፣ የጴጥሮስ መንበር ነን የሚሉት ብዙ ጉዳት አድርሰውብናል። ይኸ
መቸም በመጣፍ ያለ ነው። በጥንቱ የማርቆስ መንበር ትምህርት መናፍቅ ተብለው የተወገዙት ካቶሊኮችና
ፕሮቴስታንቶች ሲሆን፣ እርስ በርሳቸው እንደዚሁ እንደተፋጁ ነው። ዛዲያ በስመ ክርስቲያን ሃይማኖት
መቸስ....» ሲሉ ትረካቸውን አቋረጡና ጸሎት የሚያደርሱ ይመስል ወደ አዳራሹ ጣሪያ አንጋጠጡ።
አሁንም መለስ ብለው ሪዛቸውን ጎተቱ። እንዳሰቡት የቴዎድሮስ የቅርብ ባለሟሎች ሳይቀሩ መኳንንቱ ሁሉ
ዐይኑን በርሳቸው ላይ ተክሎ የሚናገሩት ቃል እንዳያመልጠው ጆሮዉን ለግቷል። ቴዎድሮስ ብቻ
የመድረኩን ወለል በቀስታ በእግራቸው ይቆረቁራሉ።
«ክርስቲያን ነኝ የሚለው ሁሉ ክርስቲያን ባለ መሆኑ ብርቱ ጥል እንደሚፈጠር በናንተም አገር
መድረሱን መቸም አሳምረው የሚያውቁት ታሪክ ነው።» አቡነ ሰላማ፣ ነገራቸውን ሁሉ እንዲከታተሉ
ሪዛቸውን እየሳቡ አሁንም ተግ አሉ። «በአጤ ሱስንዮስ ዘመነ እዚያ በመንበረ ማርቆስ ላይ የተነሡት
እምነት ተከታዮች መጥተው እንደዚያ በማድረጋቸው ያ ሁሉ እልቂት ደረሰ፣ ያ ሁሉ ሰው አለቀ፣ ያው
እንደሚያውቁት ልጃቸው ፋሲል ነግሦ፣ ‹ሃይማኖት እንደ ባቶቻችን የመንበረ ማርቆስ› ሲል ያ ሁሉ
በረደ፣ ሰላም ወረደ፣ ይኸው ነው የሃይማኖት ታሪኩ» ሲሉ ደመደሙ።
ብዙ ጦር ሜዳ ላይ ስልት እያወጡና እየሠሩ ያሸነፉት ቴዎድሮስ ጋሻቸውን በአጓጉል
አንከርፍፈው እንደ ተመቱ ወዲያው ገባቸው። በአቡኑ መልስ ቆንስለዋል። እንደ ቆስለ እልሃም አውሬም
አሁንም ወደፊት ተጋፈጡ።
«ምኑን ከምን አመሳሰሉት አባታችን። ያ ሌላ፣ የአሁኑ ሌላ።» ቴዎድሮስ ወዲያው መልሰው
አንደበታቸውን ረገብ ለማድረግ ሞከሩ።
«የእኔ ሐሳብ ለሥራ የሚመጡት ወዲያ ወዲህ ውልፍት ሳይሉ ሥራቸውን ብቻ እንዲሰሩ ነው።
አይ ሌላ ነገር ውስጥ እንገባለን ካሉ እኔ የማደርገውን አውቃለሁ። እንኳንስ ከባዕድ አገር የመጡ፤ ተዚህ
ካገራችንም ካህን ነኝ እያለ ሲወላገድ የሚውለው ሁሉ አርሶ፣ ቆፍሮ ወይም የሚያውቀኝ በሌላ ነገር ሁሉ
ሠርቶ እንዲኖር ነው የሚሆነው። መጽሐፉም ‹ብላዕ በአፈ ገጽከ› ብሏል» አሉ ወደ አቡነ ሰላማ ዘወር
ብለው እየተመለከቱ። «አይደለም አባቴ?» ሲሉም ጠየቋቸው።
አቡነ ሰላማ አዎናታ አይሉት አሉታ፣ አሁንም ከንፈራቸውን ውስጥ ከአጉመእመቱ በኋላ፣ «ግና»
አሉ ግልጽ በሆነ አነጋገር «አምላካችን ሁሉንም በየሥራው ደልድሎታል። ሙሴ የእሥራኤልን ሕዝብ
እንዲመራ ሲመርጠው አሮንን ደግሞ ለቤተ ካህናቱ መድቦታል።»
«እውነትዎን ነው አባታችን» አሉ ቴዎድሮስ፣ በሐሳባቸው ላለው ጉዳይ አሁን ደኅና መንገድ
የተከፈተላቸው መሰላቸው። መረጠው። ግና ስንት ዕልፍ ዕማዕላፍ ለሆነው ለቤተ እስራኤል ሕዝብ ምድሩ
ካህን ነው። ዝም ብሎ የሚቀበለው ሁሉ እየሠራ ቢያድር ምን ይመስልዎታል?» ሲሉ ጠየቁ።
አቡነ ሰላማ መልስ መስጠት ባያቅታቸውም ከራሳቸው ይልቅ በዚያ አዳራሽ የተሰበሰበው
አብዛኛውን መኳንንት የበለጠ እንደሚቆነጥጠው በመገመት ለጥቂት ጊዜ ዝም ብለው ጠበቁ። «መቸስ
ቢሆን ቤተ ክርስቲያን ሁላ ይዳፈን አይባል። ዛዲያ፣ ለጧት ኪዳን ለምሽት ቁርባን፣ ለቅዳሴ ለማኅሌት
ቤተ ክርስቲያን ያለ አገልጋይ ካህናት እንዴት ቤተ ክርስቲያን ትሆናለች?» አሉ በመጨረሻ።
«ቤተ ክርስቲያን ይዳፈን አልወጣኝም። ያልታስበ ነገር አያምጡ» አሉ ቴዎድሮስ ትንሽ
የመበሳጨት ቃና ባዘለ አነጋገር፤ «በአንድ ቄስ፣ በሁለት ዲያቆን በሦስት እንደሚቀደስ እናውቃለን። ቢበዛ
በሁለት በሦስት ዲያቆን፣ በአምስ ይሁን። ከዚህ በተረፈ ሥራ ፈትቶ እየተለበ የሚንጋጋው ሁሉ ምን
ይጠቅመኛል? ደሞስ አንድ ሰንበት ጧት ለመቀደስ ሳምንት ሙሉ ሥራ ፈትቶ መቀመጥ ምን ይባላል?
እኔም እኮ ብችል እንደ ጻድቁ ዮሐንስ፣ የሕዝቤን ገንዘብ ባልነካ፣ ሰሌን እየሠራሁ እየሸጥኩ ብተዳደርና
ባስተዳድር ደስ ባለኝ ነበር። ይህ ባይሆንልኝ ቢቀርም፣ ሠራዊቴ ግን እንዳለፈው ጊዜ በየጢሱ እየተመራ
ወይንም ያገሬን ገብሬ ሞሰብ እየደፋ ሳይኖ በቀለብ ሥራት የሚተዳደርበትን ደንብ ገና አወጣለታለሁ።
በሠለጠኑት አገሮች እንደዚህ ነው የሚደረገው አሉ። ስለ ቤተ ክርስቲያን እንደሆነ ሌላው ካህን ነኝ ባይ
ሁሉ አርሶ ነግዶ፣ ወይም በሌላ ሙያው ሠርቶ እንደሚኖር ነው ያለኝ ሐሳብ።» ስለ ጻድቁ ዮሐንስ ሰሌን ሥራ ሲነገር በአድናቆት ከንፈሩን እንደመምጠጥ እያደረገ ፈገግታ
አሳይቶ የነበረው መኳንንት የምጽአት መዓት እንዲሰማ ያህል በድንጋጤና በግራሜ አተመመ።
«ስንት ባሕታውያን የዘጉበትን ገዳም፣ ስንት የቅኔ፣ ያቋቋም፣ የድጓ መንበር የተዘረጋበት ደብር
እንዴት እንዲህ ይሁን ይባላል?» ሲል ጠየቀ አንድ መኮንን።
«መቸም የተቸገረ ጠፍ ደብር ነው በሦስት የሚያስቀድሰው። ስለሆለትማ፣ ሰባትም ዐሥራ
ሁለትም፣ አሁን እርስዎ የነገሡበት ደረስጌ ከሰባት ባነሰ ዓመት ባል ተቀድሶበት አያውቅም ሲል ጠቆመ
ሌላው በተራው።
«መቸምኮ፣ ለቤተ ክርስቲያን የሚያገለግለው ካህን ብቻ አይመስለኝም። ከዚህ ከአባታችንና
ከጨጌው ጀምሮ ትልልቆቹ ሊቃውንት ያለረድዕ አይሆንላቸውም። እንዲያው እንደ ጨዋ ገበሬ ይንከላወቱ
ካልተባለ በስተቀር! አሁንም የሆነ እንደሆነ፣ ቤተክርስቲያንም ከቀዳሹ፣ ካወዳሹ፣ ጋራ ሌላው ቢቀር ገበሬ
መበለት አለው፣ ባገራችን» አለ አንዱ ደግሞ በማብራራቱ።
ድንገት ቀፎው እንደተነካበት ንብ፣ ተራ ሳይጠብቁ መኳንንቱ ከዚያም ከዚያም እየተነሳ
ጥያቄውንና አስተያየቱን በላይ በላዩ አደራረበው። ቴዎድሮስ ባንድ በኩል ላገር ይበጃል ብለው ያቀረቡትን
ሐሳብ መኳንንቱ ለምን በመጥፎ እንደተመለከተው እየገረማቸውና እንደመበሳጨትም እያሉ፣ በሌላ በኩል
ደግሞ በመጨረሻ የሁሉንም አጠቃለው በጥሞና ለማስረዳት ትዕግሥታቸውን እየጨመቁ አዳመጡ።
ከሐሳባቸውና ከቃላቸው የማይወጡት የቅርብ ባለሟሎቻቸው በመካከሉ ግራ ተጋብተው አንድ ጊዜ ወደ
ቴዎድሮስ በጭንቀት ዐይነት ሲመለከቱ ግራ ተጋብተው አንድ ጊዜ ወደ ጊዮርጊስ በጭንቀት ዐይነት
ሲመለከቱ ሌላ ጊዜ ተናጋሪውን በቁጣ ይገለምጣሉ፤ አልተገፋላቸውም።
ቴዎድሮስን ጠቅ የሚያደርግ ጥያቄና አስተያየት በተሰነዘረ ቁጥር አንዱን፣ ‹እሰይ! አበጀህ፣
እንዲያ ነው እንጂ! እያለ በሆዱ ሲቅበጠበጥ በግልጥ ያስታውቃል። በአንድ ጊዜ ብዙዎች ለመናገር
ሲነሡ፤ እንደ ቆረፈደ ቆዳ የሚንቋቋ ድምፅ ያለው አንዱ ቀደመ።
«የጦቢያ ሕዝብ ክርስቲያን ነው። ያዕቆብ ካቶሊክ ባገራችን ምን ይሠራል? ተዚህ ላይ ደሞ አሁን
አጤ፣ ቤተክርስቲያን ይጻፈን ሲሉ እኔ በውነቱ ለማተቤ፣ ለዚች ለማተቤ ብሞትም ግዴለኝ» አለ እንደ
መቁነጥነጥ እንደ መንቀጥቀጥ እየቃጣው። የቴዎድሮስ ዐይን ድንገት እየቀላ ሔደ። «አሁንም የሆነ እንደሆነ
አሁን የታሰበው ግን መናፍቅነት» ብሎ ንግግሩን ሳይጨርስ መጨረሻ የተናገረውን ቃላት ሁሉም ሰው
በሚገባ ሳያዳምጠው ቴዎድሮስ እመር ብለው ቆሙ።
ስስ ከንፈራቸው እየተንቀጠቀጠ፣ በስስ ከንፈራቸው ጠርዝ ድንገት አረፋ እዬወጣ ተፈናጥረው
ተነሥተው ጎራዴያቸውን እስከ ጫፉ አጠገብ ድረስ ላጥ አደረጉት። እፍ እንደተባለ መብራት እርጭ
ባለው አዳራሽ ውስጥ «መይሳው ካሣ!» የሚለው ድምፅ እንደ ነጎድጓድ አስተጋባ።
ታንጕት፣ በዚያ ጎራዴ መላ ሰውነቷ የተሰነጠቀ መስሎ ተሰማት። ድንጋጤ ይሁን ፍርሃት
አልታወቃትም። ብቻ ካለችበት ደረቀች። በቅጽበት ተዋበች ተፈናጥረው ከቴዎድሮስ ወገብ ሲጠመጠሙ
በአጠገብ የነበሩት እነ ገብርዬ እነ ዓለሜ፣ እነ እንግዳ ተረባርበው የተመዘዘው ጎራዴ ጨርሶ ሳይወጣ፣
ቴዎድሮስም ሌላ ቃል ከፍ አርገው ሳይናገሩ፣ በጓደኝነት ገሥጸው ከባብበው ወደ እልፍኝ ሲወዷቸው አላየችም። ዐይኖቿን በመዳፍዋ በመዳፍዋ ሸፍና ሐሳብዋ በተመዘዘው ጎራዴ እንደተተከለ ነበር። ዐይንዋ
ግልት፣ አእምሮዋም መለስ ሲል ወደ እልፍኝ ሔደች። የመጀመሪያዋ ጊዜ ባይሆንም አሁን ግን ለምን
እንደሆነ ምክንያቱን አላሰበችውም ነበር። እግርዋ እንደመራት እንዲሁ ሔደች። ሳታስበው ደርሳ ገርበብ
ካለው በራፍ ግማሽ አካልዋ እንደገባች ድንገት ቆመች።
ተዋበች፣ ከቴዎድሮስ እግር ሥር ተንበርክከው ሁለት ቋንጃቸውን በማቀፍ ከታፋቸው ላይ ደፋ
ብለው በጭንቀትና በፍቅር ይማጠናሉ። «የኔ ጌታ፣ ኧረ ባክህ የኔ ጌታ! ለምን እንደዚህ ትናደዳለህ?»
የቴዎድሮስ ቋንጃ ጭምቅ አደረጉት።
የንዴት ትንፋሻቸውን እንደ ነበልባል በአፍንጫቸው ቡል ቡል የሚለው ቴዎድሮስ ጉልበታቸውን
ለመገፍተር ቃጣውና መለስ አድርገው፤ «ተሰደብኩ፣ ሰብደበኝ እኮ! ምን ላርግ በለሽ ነው ተዋቡ?» አሉ
ምርር ባለ አነጋገር ፊታቸውን በሁለት መዳፋቸውን እየፈተጉ።
«የኔ ጌታ! ዛዲያ እንደዚህ ይኮናል?»
«ስድብ አልወድም!» እንደመራጨት ቃጣቸው።
«እህ! መቸስ ምን ይደረግ?»
«እናቴም! እናቴም ያቺ የምወዳት እናቴም ትመክረኛለች፣ ትገሥጸኛለች፤ ትቆጣኛለች እንጂ
የሚዋርድ ነገር ሰድባኝ አታውቅም።»
«አሁን የተናገረውን ምን ስድብ አለበት?»
«መናፍቅ ቅሎኛል።»
«እኔ እንደሰማሁት ‹መናፍቅ ነው› ነው ያለው። እባክህ የኔ ጌታ!»
«ያው ነው!!» ቴዎድሮስ ጥቂት ተወራጩ።
«ኧረ ባክህ የኔ ጌታ! ያው አይደለም። አንተን መች አለህ?»
«አዎ ያው ነው! ሐሳቡን መናፍቅነት ነው ካለው እኔን ሰድቦኛል። አገሬ ትልቅ እንድትሆን
ባሰብኩ እኔን የሰደበኝ ደሞ አገሬንም ሰድቧል!»
«ታዲያስ መቸስ እየቻሉ ነው እንጂ!»
«የጭነት ከብት ብቻ ነው ቻይ!»
«ኧረ ባክህ ተው የኔ ጌታ!» አሉ ተዋበች ፊታቸውን፤ ቀና አድርገው ዕንባ ባቆረዘዘ ዐይን
ተማጠኗቸው። «ራስህ ምክር፣ ሐሳብ ጠይቀህ እንዲህ ስትሆን ምን ይባላል? ያለ ትዕግሥት አገር
ይገዛል?»
«በምክር ላይ ዛዲያ ዘለፋን ምን አመጣው?»
«ምናልባት ደግ አስብኩ መስሎት ይሆናል።»
«ለምን ሐሳቤ አይገባቸውም ተዋቡ?» ከንዴት ይልቅ አጠያየቃቸው የብስጭት ነበር።
«እነሱ የሚያውቁት የለመዱትን። አንተ እንዳልከው፣ አባቴ ዘመንና ተዚያም በፊት አንሥቶ
መኳንንቱም፣ ሰዉም ግምኛ ሆኖ ከቆዩ አሁን አንተ ላገርህ ትልቅ ሐሳብ ስታመጣበት ባያውቅልህ ምን
ትፈርደብታለህ።»
በተዋበች አነጋገር ተረትተው ቴዎድሮስ በሐሳብ ራሳቸውን አወዛወዙ። «ዛዲያ ምናርግ ትይኛለሽ
የኔ መቤት?» ሲሉ በትካዜ አንደበት ጠየቁ። «ያገሬ ነገር ሆኖብኝ ነው እንጂ ለኔና ላንቺ ሆድማ፣ ቋራ
አውሬ አድነን ብንበላ ያንሰን ነበርን?»
«እረቴ! ዛዲያ ታጋሽ መሆን ነዋ! በትንሽ በልቁ ቢቆጡ፣ ቢናደዱ፣ አሁን እንዳረከው ብታረግ
ሰውን ከማስበርገግ በቀር ፋይዳው የለው!» ተዋበች ከተንበረከኩት ልጥጥ ብለው እንደማስተካከል ዐይነት
የአጼ ቴዎድሮስን ቄንደላ ዳበስ ዳበስ ያደርጉት ጀመር። ቴዎድሮስ ዐይናቸውን በሐሳብ ከደን አድርገው፣
የሚሽታቸው ለስላሳ ትንፋሽ ሲያባብላቸው ንዴታቸው በረድ እያለ ሔደ።
«እባክህ ፈጣሪዬ፣ ትዕግሥቱንም አክለህ ስጠኝ!» አሉ በታከተ ኧንጋገር። «አንቺም እስቲ
ተዋቡ የመታገሻውን መላ አስተምሪኝ!» በበኩላቸው የሚሽታቸውን ትከሻ ዳሰስ ዳበስ አደረጉት።
«አሁን እስቲ ዐረፍ በል የኔ ጌታ» አሉ ተዋበች፣ ከንብርክካቸው ተነሥተው ዋልባቸውን
እየነቀሉና፣ ቀይ የሐር ቀልቢያቸውን እየፈቱ።
«አንቺም እስቲ ዐረፍ በይ የኔ እኅት፣ አንቺንም ጨምሬ መከራ ሥቃይ አሳየሁሽ» ሲሉ
የሚሽታቸውን ፊት በትካዜ ፍቅር አተኩረው ተመለከቱ።
«እኔ ግዴለም እስቲ አንተ ዕረፍ» አሉ ተዋበች መቀነታቸውን እየነካኩ። ታንጕት ከበሩ ላይ ቁማ
ያዩዋት መዘጋቱን ለማረጋገጥ ዐይናቸውን ወደበሩ በመለሱ ጊዜ ነበር። ታንጕትንም «ምን ሆነሽ ነው ተሱ
የቆምሽው?» ሲሉ ጠየቋት። አነጋገራቸው ከግሣጼ ይልቅ የማፈርና የመገረም ቃና ነበረበት። ቴዎድሮስ
ዝም ብለው አስተዋሏት። በሌላ ሐሳብ ውስጥ ይመስላሉ።
«እኔማ - እኔማ አባ ታ - ታጠቅ.....» አለች ታንጕት የምትናገረው ጠፍቷት።
«ምንም ነገር የለም! ሲናደድ ታውቂው የለ?» ሲሉ ተዋበች አሰናበቷት።
ታንጕት ‹አላውቅም› ማለት ቃጣት። ስሜቷ የተቀላቀለ ነበር። በሁለቱ ሕይወት ላይ በማጮለጉዋ
ኃፍረት ተሰማት። ለጊዜው በሁለቱ መካከል የማትፈልግ መሆንዋ ደግሞ አናደዳት። ‹በፊት የማውቀውስ
እኔ ነበርኩ!› አለች በሆድዋ። ደረጃውን እየተንደረደረች ስትወርድ፣ ገብርዬ ከግቢ መውጣቱን
አላረጋገጠችም፣ አልተበቀችም፤ ሩጫ በከጀለው አረማመድ ወደ ቤትዋ ሔደች።
ገብርዬ ቤት ሲመጣ፣ ታንጕት የአዘቦት ልብሷን ለውጥ ፊቷን በጣትዋ እየጠቋቆመች ከመስታወቷ
ጋር ስትጫወት አገኛት። «እህ?» አለና ከጎንዋ ተምቀምጦ በቀልድ ዓይነት ፊቱን ከመስታወቱ ትይዩ
አስተካከለ። ታንጕት፣ ጎንደር እንደሰነበተች ስናር ድረስ ከሚመላለስ አንድ ነጋዴ ዘንድ ካገኘቻቸው ዕቃዎች አንዱ ቁመቱ ወደ ክንድ የሚጠጋ፣ ወርዱ ስንዝር የሚያክል መስታወት ነበር። ዱሮ ፊትዋን
በውሃ ውስጥ እያየች በደስታም በቅሬታም ትጫወት እንደ ነበር ሁሉ አሁን መስታወቱ ብርቅዬ
ሆኖባታል።ገብርዬም ድንገት ቤት ሲገባ ብዙ ጊዜ ከፊቷ ደቅናው አግኝቷታል። አንዳንድ ጊዜ ከራስዋ
ጋር ትሣሣቃለች። ሌላ ጊዜ ከምስሏ ጋር ፊቷን አኮፋትራ የምትሽሟጠጥ ትመስላለች።
ገብርዬ በመጠኑ አጠርና ሰፋ ካለ ፊቱ ዘወትር ከሚያፈጡት ጠባብ ዐይኖቹ፣ አጠር ብሎ
ቀዳዳዎቹ ሰፋፊ ከሆኑት አፍንጫው፣ ‹ሰፌድ› አገጭ የሚል ስም ካሰጠው ሰፊና ጠፍጣፋ ቢጤ ከሆነው
አገጩ፤ በመጠኑ ከርደድ ብሎ ጥቅጥቅ ደን ከመሰለው ጎፈሬው ጋር ተፋጠጠ። ወዲያውም በጠይምነቱ
መኻል እንደ ማሽላ ቆሎ ድንገት የሚፈካውን ጥርሱን በፈገግታ ገለጥ አደረገና ወደ ታንጕት አምሳያ
አተኮረ። ቆንጆ እንደሚባሉት በጣም ስልክክ ሳይል ከበብ ያለው የፊት ቅርጽዋና ከእርሡ ገለጥ ብሎ እንደ
ውሃ የጠራው ጠይምነቷ፤ ከንፈሮቿን በፈገግታ ሳብ ስታደርግ ከጉንጮቿ ላይ ከሚወጡት ስርጉዶች ጋር
የልጅ ውብት፤ የልጅ ለዛ ይሰጣታል። ደስ ያለችው በልቡ፤ የደስ ደስ ያላት ልጅ ናት ያለው፤ ገና ቋራ
ከካሣ ጋር ሲገናኝ ያያት ዕለት ነበር። አልተለወጠችም። ዐልፎ ዐልፎ ጣል ጣል ያደረገባት የኩፍኝ
ጠቃጠቆ ስንኳን እንደ ማርያም ስሞች አንዳች ዐይነት ውበት ጨመረላት እንጂ አልቀነሰባትም። ሌላ ጊዜ
በመስታወቷ ውስጥ ሲፋጠጣት እንደምታደርገው አሁን ግን ስርጉዶቿ በፈገግታ አልወጡም።
«ምን ሁነሻል?» ሲል ጠየቃት።
«እህ? ምን አልኩህ!» አለች ቅዝዝ ባለ አነጋገር።
«በሹመቴ ደስ አላለሽም እንዴ?»
«ለምን ደስ አላለኝም?»
«ዛዲያ ሐሳብ የገባሽ ትመሲያለሽ።»
«ይኸን ነገር የሚያጠፋልኝ ነገር ቢኖር!» አለች ድንገት ችግርዋ የተገለጠላት ይመስል የኩፍኝ
ጠቃጠቆዋን በጣቷ እየጠቋቆመች።
«አብሮሽ የኖረውን አሁን አስጨንቀሽ?»
«ሲያስጠላኝስ?»
«ዛዲያ አላሰላብሽ!» አላት የስርጉዱ ቦታዋን ጠቅ እያደረገ። መልስ ሳትሰጠው መስታወቱን
አስቀመጠችው።
«እውነት አንድ ነገር ሆነሻል ታንጕት?» ሲል እንደገና ጠየቃት።
«እኔስ ምንም አልሆንኩ። ግና አስፈራኝ?» አለች ታንጕት ከሐሳብ ማመንታት ጋር።
«ማን? አባ ታጠቅ?»
ታንጕት፤ በአዎንታ መልክ ዝም አለች።
«ይህን ያህል ዘመን አብረሽው ኑረሽ አታውቂም?»
«እንደዚህ ሲሆን?» ታንጕት መልሳ ጠየቀችው።
«አንቺ የምታውቂው፣ በቤት በጎረቤት፣ በሠፈር፣ ተሆነ ከሁላችን የበለጠ ታጋሽ ነው። በጦርነት
ላገሩ ባለው ሐሳብ ደግሞ ሌላ ይሆናል። ጦር ሜዳ ላይ አላየሽውም?»
«እንደዚህ?» አለች ታንጕት ስቅጥጥ እያላት።
«ምን መሰለሽ ታንጕት» ገብርዬ በማባበል ትከሻዋን በእጁ ጨበጥ አያደረገ «ካሣ እንደ ቀድሞው
ካሣ ልበልው ደግነቱ ትልቅ ነው። ዓላማው ትልቅ ነው። በዚያው መጠን ቁጣውም ትልቅ ሊሆን ይችላል።
«እና... እንደዚህ ቅልት ቅንቅፋት ሲያጋጥመው ደሞ፤» ሐሳቧን አቋረጠችና፤ «እኔስ በጣም
አስፈራኝ!» ሌላውን ሐሳቧን ሁሉ ትታ።
«ታወቅሽ አትፈሪውም! አሁን ይኸን ተይውና ሰው መምጣቱ አይቀርም። ጉድ ጉድ ብትይ
ይሻላል። አባ ታጠቅ እንዳለው ጎንደሮች የሚፈትሹሽ ዛሬ ነው።
ሁለቱም ከደርብ ሆነው በበር በኩል ወደ ውጭ ሲመለከቱ እንኳን ደስ ያለህ ለማለት የሚመጣው
የመጀመሪያው እንግዳ ከግቢው በር ደርሶ ነበር።
ገብርዬና ታንጕት፤ ስለ ሹመቱና ስለ ቴዎድሮስ በሚነጋገሩበት ጊዜ ከግንቦች ግቢ በስተምዕራብ
ትንሽ ወጣ ብሎ በግምጃ ቤት ማርያም ሠፈር ሁለት ሰዎች እንደእነርሱው ስለ ዘመቱ ስለ ቴዎድሮስና
ስለ ገብርዬ በመነጋገር ላይ ነበሩ። ከጥሞና ጭውውትም ወደ ተጋጋለ ክርክር እያዘበሉ ናቸው።
ደብተራ አክሊሉ፣ ከጋረድ ቤት የመጣው ቀደም ብሎ የሹም ሽሩ ስብሰባና ገና መበተን ሲጀምር
ነበር። የጋረድ ቅጥር ሚስት ጋረድ ገና እንዳልተመለሰ ስትነግረው ትንሽ እንደ ተቅበጠበጠና እንደ
ተቁነጠነጠ ቆይቶ እንደ ቤተኛነቱ በምድር በኢቱ ገባና፣ በደርቡ ሰገነት በኩል ሲመለከት የግቢው አካባቢ
ጭር ማለት ጀምሯል። ሥነ ሥርዓቱ እንዳበቃ ዐወቀ። «እኮ የት ቆየ?» አለ ከራሱ ጋራ፣ ጥርጣሬም
የችኮላ ብስጭትም ተሰማው። ‹ደኅና ሹመት አግኝቶ ተስማምቶት በዚያው ለምክክር እልፍኝ ገብቶ
ከቴዎድሮስ ጋር ቆይቶ ይሆን? ይህማ ተሆነ ስንት የለፋሁበት ነገር ሁሉ ተመልሶ ከንቱ መሆኑ ነዋ! ወይስ
ወደዚያች ጋለሞታ ወዳጁ ዘንድ ሔዶ ይሆን? ይህማ ተሆነ ስንት የለፋሁበት ነገር ሁሉ ተመልሶ ከንቱ
መሆኑ ነዋ! ወይስ ወደዚያች ጋለሞታ ወዳጁ ዘንድ ሒዶ ይሆን? ነገሩን ማወቅ መሻቴን እንዴት ችላ
አለው? ግን ከዚያች ጎንደር ካፋጀች ጋለሞታ ወዳጁ ዘንድ ከሔደ ቢናደድ ነው› ሲል አሰበ። እንዲሁም
መጠበቁ አላስችለው አለና፣ ከዚያው አቅራቢያ ወደ ሚገኘው አንዲት የሚያውቃቸው መሻች ቤት ሔዶ
አረቄውን እየደጋገመ ሲጠጣ ቆይቶ ሲመለስ ጋረድ ለጥቂት ቤት እንደገባ ደረሰ።
«የት ጠፋህብኝ ልጅ ጋረድ?» አለ ደብተራ አክሊሉ፤ ከጥያቄ ይልቅ መልክ በሞቅታ ወይም
በሌላ የስሜት ሙቀት ጉበት መስሎ ከግንባሩ ላይ ጅማቱን ተገታትረው ነበር።
«አሄሄ! ዐውቄብሃለሁ የት እንደጠፋህ! የአንተ ጉርምስናና ወንድነት መቸ ይሆን የሚበርደው?»
አለና በጓደኝነት ትከሻውን እንደመታቀፍ አድርጎ ከአጠገቡ ተቀመጠ። «እባክህ ምንላርግ ዛዲያ?» አለ ጋረድ ከቁጣ ወደ መኩራራት መለስ ብሎ።
«ኧረ አበጀህ ወንድሜ!» አክሊሉ የጋረድን ትከሻ ጠብ ጠብ አደረገ፤ ቅጥር ሚሽቱ ወደ
አለችበት ጉዳ በዐይኑ እያመለከተ፣ «ለመሆኑ ታውቃለች?» አለው በጥያቄ ሳይሆን የአድናቆት ምሥጢር
በሚገልጽ ሹክሹክታ። ጋረድ እኔ ምን ቸገረኝ በሚል አኳኋን ትከሻውን ሰበቅ አደረገ። «ብቻ ጠንቀቅ
ነው። ገና ብዙ ዕድል የሚጠብቅህ ሰው የቀናተኛ ሴት ነገር አይታወቅም ልጅ ጋረድ!» አሁንም ትከሻውን
እንደ ማቀፍ አደረገው።
«እሺ እንዴት ነበር?» ሲል አክሊሉ በጉጉት ጠየቀው።
«ኧረ ተወኝ! ሕዝብ አዳሜ ተፋጀ እንጂ! ካሣ የለየለት!!» አለ ጋረድ በንዴት አነጋገር።
«እንዴት?»
ጋረድ የሆነውን በአጭሩ ተረከለትና «እኔም እኮ ያ -ፈንጠሬ ለጥቂት ቀደመኝ እንጂ ተነሥቼ ልክ
ልኩን ልነግረው ነበር» በማለት ፎከረ።
አክሊሉ የደስታ፣ የተስፋ፣ ስሜቱ እየፈካ ሔደ። ጋረድን ቀስ እያለ ከገፋፋው ከአሰበው ድረስ
ይሔድለታል። ትንሽ መጠጥ ቢጨመር ደግሞ ሁለቱንም የበለጠ ያደፋፍራቸዋል። «ዛዲያ የሹመት ቀን
እኮ ነው። ድግስም የለ ተቤትህ?» አለ በቀልድ መልክ።
«ኧረ -- ኤጭ!» ጋረደ እንደ መወራጨት አለና መለስ አድርጎ፣ «ያንንስ እንተወውና ነገሩ ራሱ
ያስጠጣል። አንች ማነሽ! የሚጠጣ ነገር አምጭልን። ምግብ ብጤም ትቀምሳለህ? እኔ እንደሆነ የዚያ
ርጉም ግብር ልውጣ እያለ ይተናነቀኛል።
«እኔም አላሰኘኝም! ለመሆኑ ምን ተሽምክ?»
«ምኑን ብዬ ልንገርህ?»
«አህ? መቸም ተሹመሃል!»
ጋረድ በምሬት ከት ብሎ ሣቀ። «አዎ! መንገድ ላይ ትቸው መጣሁ እንጂ ፊታውራሪ ቀሚስና
ወገራን!»
«ወገራን! ስሜንንም፣ ወልቃይት ጠገዴንም ሳይጨምር?»
«እንደ ቤት ውሻ ተሥር ተሥሩ ቱስ ቱስ ተሚሉት እንትኖቹ በተቀር ሁሉም እንደዚሁ ነው
የደረሰው። የተማሪ ቁራሽ የምታካክል አገር።
«ወገራ? የደጃች ክንፉ ልጅ ወገራን በካሣ ይሾም? ወቸው ጉድ! ዛዲያ አየህልኝ አይደለ የሱን
ነገር?»
«ሽቅብ እስቲለኝ ነዋ!» 
«በፊትም እኮ ነግሬህ ነበር። ዘመዶቹን ነው ቀድሞ የሚጎዳ በአንተ ወንድሙ ላይ ነው ተቀዳድሞ
የሚነሳ ብዬ!»
«ምን በደልኩት? አባቴስ ምን በደሉት?»
«ምንም! ምንም!» አለ አክሊሉ ንግግሩን በመርገጥ። «ደጃች ክንፉ፣ በሰማይ ነፍሳቸውን
ይማርና እኛ ደጉ ሰውማ ታንተ ሳይለዩ እንዳንተ እንደ ልጃቸው አቀማጥለው አሳደጉት እንጂ ደሞ ምን
በደሉት? በፊትም ነግሬሃለሁ» አለ በድጋሚ አክሊሉ።
ጋረድን በቴዎድሮስ ላይ ለማስነሳት ልቡን ማሻከር የጀመረው ገና ራስ አሊ ድል ከሆኑ ጊዜ
አንሥቶ ነበር። መጀመሪያ በአግድሞች አነጋገር ነበር። ከዚያም፣ ቴዎድሮስ ከፋሲል ግንብ ላይ ሆነው
ድፍን ጎንደር በንቅስ ወጥቶ የአዲሱን የአስተዳደራቸውን ዐዋጅ ባስነገሩ ጊዜ ሁለቱ ወደ ዳር ሆነው
እየተመለከቱ፣ ‹አሁን ማ -- ይሙት አንተ እያለህ እርሱ ተዚያ ላይ ይውጣ?› ሲል በግልጽ ነገረው።
የጋረድም ልብ በምኞት ወደ ግንቡ ሰገነት ወጣ። የሙገሳ ማር እየቀባ ዘወትር ተስፋ ሲመግበውም የጋረድ
ምኞት በዚያ በሰገነት ላይ እንደ ተንጠለጠለ ቆይቷል። የአክሊሉ ሥጋ ጋረድ ደኅና ግዛት ይሾምና ልቡ
ይረካ ይሆናል የሚል ነበር። ሥጋቱ ሳይደርስ ቀረለት።
«ዛዲያ በም ምህኛት ነው?» የሚለው የጋረድ ጥያቄ አክሊሉን ከሐሳብ መለስ አደረገው።
«በምን ምህኛት? ቅናት ነዋ! ምቀኝነት ነዋ! ሰው መቸም በሚበልጠው እንጂ በሚያንሰው
እንደማይቀና ታውቃለህ። ትንሽ ሰው ምኑ ይፈራል ምኑስ ይቀናበታል? ዛዲያ አሁንም የሆነ እንደሆነ ካሣ
ባንተ ያልቀና ያልተመቀኘ በማን ይመቅኝ? በኔ ሞት! ወንድ ጀግና ነህ። በሰማይ ነፍሳቸው ይማርና፣
የሕዝብ ፍቅር የነበራቸው የደጃች ክንፉ አንድ ልጅ ነህ። ለዚያው ሥልጣን ካንተ የተሻለ ማን አለና?
እንዲያውም፤ እንዲያውም» አክሊሉ ንግግሩን አንጠጥልጥሎ ተወውና ወደ አረቄ መለኪያው ዞረ።
« ‹እንዲያውም› ያልከውን ጨርሰው እንጂ!» አረድ በበኩሉ አረቄውን ተጎነጨ።
«እህ?» አክሊሉ ለመናገር ያቅማማ መሰለ።
«ምን ነገር ከምላስህ እያደረስክ መልሰህ ትውጣለህ!» አለ ጋረድ ቆጣ ባለ አነጋገር፣ ሁለቱም
የአረቄውን ሞቅታ እየተሰማቸው ሔዶ ነበር።
«ማለቴማ በነፍስህስ ባይመጣ!»
«ሲገለኝ?»
«እህ? ልጃቸውን የዳሩለትን ያንን የመሰለ ጌታ ይኸውና ታገር አጥፍቷቸው የለ? ደጃች
ወንዲራድስ ያንን የመሰለ መኮንን ኮሶ ግቶ አልገደለውም?»
«ሰደበኝ ብሎ ነዋ እሱንማ!»
«ቢሆንስ! ለምሳሌ አሁን እነ ገብርዬ እነ ገልሞ እነ ዓለሜ፤ እንዲህ ጣራ ሲነኩ አንተ ወገራን
በመሾምህ ደምህ ፈልቶ አንድ ነገር ብትናገረው፣ እንደዚያው መሆንህ አይደል? ኧረ ጨካኝነትና እብሪት
ነው!» ጋረድ በዚህ የፋሲል አዳራሽ እንደ መብረቅ ብልጭ ብሎ የወጣው የቴዎድሮስ ጎርዴም በራሱም
አንገት ላይ ሲያንዣብብ ለቅጽበት በሐሳብ ታየውና ፊቱን ጨፍገግ አደረገ። አክሊሉ እንዳያውቅበት ግን
ወዲያው ፈገግታ አሳዬ። «ግና ምን ያህል ብትጠላው ነው እባክህ?» አለው አክሊሉን።
«ምን አገናኝቶን እጠላዋለሁ? እርግጥ አልወደውም።»
«ዛዲያ ባትጠላው ነው፣ ፈረስክን ጫን እንጂ እያልክ እንደዚህ የምትቀሰቅሰኝ?»
«በሱ ጥላቻ ሳይሆን ላንተ ፍቅር ስል ነው። በስማይ ነፍሳችውን ይማርና ለዚያ ለደጉ አባትህ
ውለታ ስል ነው። አንተ ተሱ በታች ውለህ እያየሁ ብል አጥንታቸውስ አይረግመኝም ጋረድ?» በኃዘን
ዕንባው የመጣ ይመስል ዐይኑን ጭምቅ ጭምቅ አደረገ።
«ቢሆንም --- ቢሆንም» አለ ጋረድ በትዝብት መልክ። «ስለኔ ተኔ የበለጠ የምትጨነቅ መቸም
አንተም ቂም ቢጤ ብትቋጥር ነው።
«ማን እኔ? የሕይወታችን ጎዳና ለየብቻ፣ እኔ ዓለም ነገሩን ትቼ ለነፍሴና ለእግዜር ያደርኩ።
እሱ ጊዜ አንሥቶት መሬት ጠበበኝ ያለ። እኔ እንግዲህ ተዚህ በኋላ» እያለ አክሊሉ ጥምጥሙን ነካ ነካ
በማድረግ አመለከተ። «በምድራዊ ሰው ቂም ብይዝ አምላኬስ ይወድልኛል?» ግን ሳይፈልግ ሐሳቡ ስንት
ዓመት ወደ ኋላ ተመለሰበት።
ዐሥራ አምስት ይሁን ሃያ ዓመት ገደማ ይሆናል። ትክክለኛው የዓመታት ቁጥር በቁጭት ጭጋግ
ተሸፍኖበታል። ድርጊቱ ግን ከሕይወቱ ጨርሶ አይጠፋም፣ ውጤቱም እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ አብሮት
ይኖራል።
ካሣ አክሊሉና እርሻ እርሻ የሰለቻቸው፣ ጭቃ ሹምና ምስለኔ ያስመረራቸው ሌሎችም የቅርብና
የሩቅ ጎልማሶች ዕድላቸውን በነፍጠኝነትና በአሽከርነት ለመሞከር ደጃች ክንፉ ቤት በባለሟልነት ገብተ
ነበር። ደጃች ክንፉ እናቱም አባቱም ከሞቱ ወዲህ፣ ለካሣ፣ በአባቱ እንደ ተተኩ አሳዳጊው የሚቆጠሩ
ቢሆኑም፣ አኗኗሩ ከሌሎች ባለሟሎች እምብዛም የተለየ አልነበረም። ከሌሎቹ ጋር ይበላል፣ አብሮ
ይኖራል፤ አብረው አደን ይሔዳሉ፣ ጉግስ ይገጥማሉ፣ ገበጣ ይጫወታሉ፣ አንዱ ከሁሉም ጋር፣ ሁሉም
እርስ በርሳቸው የልብ ወዳጅነት ባይኖራቸውም፣ አብረው በመኖራቸው «የክንፉ አሽከር» እያሉ
በመፎከራቸው አብረው፣ በመዝመታቸውና ጎን ለጎን በመዋጋትቸው፣ ከሌሎች መኳንንት ባለሟሎች ጋር
በአደባባዩ፣ በየመሸታ ቤቱ በመፎከራቸው እንደ ባልንጀራሞች ይተያያሉ። ጠባያቸው ባይስማማ
ይቻቻላሉ። በዚህ መካከል ግን፣ የካሣና የአክሊሉ ኮከብ ከመጀመሪያ አንሥቶ የማይገጣጠም ሆነ።
ውቃቢው የነገረው ይመስል አክሊሉ፣ ካሣ የሚንቀው ይመስለዋል። በዚህ ላይ፣ የካሣ ኩራትና
መንጠራራት ያበሽቀዋል፣ አጉል ድፍረቱ ያናድደዋል። ለምሳሌ አንድ ጊዜ ደጃች ክንፉ ለአደን በለሳ
ወርደው ሲመለሱ የመገጽ ወንዝ ሞልቶ ቆያቸው።
«ማነው እስቲ የሚፈትሽልን ጎበዝ?» ብለው ደጃች ክንፉ ንግግራቸውን ሳይጨርሱ ካሣ ነጠላውን
ወርውሮ ዘሎ ገባ። ወዲያውም ከአረፋው ጋር ይደፍቅ ጀመር። ሰው እየተጯጯኸ፤ ደጃች ክንፉ፤ «ዝም
ብላችሁ ታያላችሁ! ኧረ ልጄን ውሃ በላው!» ብለው ሲቆጡ፤ አንድ መቶ ክንድ እንደተወሰደ ሦስት ብርቱ ዋናተኞች እንደምንም አወጡት። ከዚያም ራሱን ዘቅዝቀው ወደ ሆዱ የገባውን ውሃ እንዲወጣ
ካደረጉና የተዘፈቀ ልብሱን አውልቀው ሌላ ነጠላ ከአለበሱት በኋላ ትንፋሹ መለስ አለለት።
«ኦሆሆ! ኧረ እንኳን አተረፈህ ወንድሜ! አፍላ ሙላት እኮ አደገኛ ነው። ቆለኞች የውሃ ጠባይ
አታውቁም መሰለኝ! ታዲያ የውሃ ነገር ለእኛ ለደምቤዎች?» ሲል አክሊሉ እንደ ቀልድ ተናገረ- በሆዱ
ግን «ይበልህ የቅብጠትህ ዋጋ ሲያንስህ ነው!» ሲል ተመኘ።
«ለደንቤዎቹ? ለጉረኖ ገፊዎቹ? ለአጓት ዛፊዎቹ? ታዲያ ምን ትጠብቅ ነበር? እጅህ በሶ ጨብጦ
ነበር? አለው ካሣ በመጠየፍ አኳኋን ከእግር እስከ ራሱ እየተመለከተ።
«አጓትኮ ያፋፋል» በማለት አክሊሉ መለሰ፤ በቀመሰው አሽሙእር መብሸቁን እንደምን ውጦ።
«ገላ ቢያፋፋ፤ ልብ ያሳሳል!» ሲል ካሣ ሌሎቹ ተሣሣቁ። አሽሙሩ ግልጽ ነበር። ልብ የለህም
ማለቱ ነው። ክንፉን ባይፈራ አክሊሉ ከዚያው በዚያው ፍልሚያ ለመጠየቅ ከጅሎት ነበር። ግን «ይህ
ምላስህና ቅብጠትህ አንድ ቀን» እያለ በማጉመትመት ዘወር አለ።
ደጃች ክፍኑ በአጉል ድፍረቱ ካሣን በመገሠጽ ፈንታ ሽለሙት። ከዚያም «የመይሳው ልጅ!»
እያለ በተጀነነ ቁጥር «ቆማጣ --- ቆመጥማጣ» እያለ ትልቅ ትንሹን በዘነጠለ ቁጥር፣ ብዙው ጎረምሳ
«ካሣ ኮስታራው» ሲለው ጊዜ፤ በሸንጎ ከሽማግሌዎሹ ልቆ ሽማግሌ ልሁን ሲል፤ በዘመቻ ከፈቱ እየቀደመ
ጥላ በሚጋረድበት ጊዜ አክሊሉ በካሣ ተፈጥሮ የባሰውን እየበሸቀ ሔደ።
የጥምቀት ሰሞን አንድ ቀን፤ የደጃች ክንፉ አሽከሮች ለገና ጨዋታ ጉፋያ መስጫ መስክ ወጡና
ካሣና አክሊሉ በተቃራኒ ቡድን ተሰለፉ። ከሠፈር ልጆች በስተቀር በበዓል ጊዜ እንደሚሆን፤ መኳንንት
ለመመልከት ያልተገኙበት የአዘቦት ጨዋታ ነበር። አክሊሉ ግን፤ የቡድን አባት ሆኖ ከካሣ ጋር ሲጋጠም
የመጀመሪያው ጊዜ ስለ ነበር፤ ቁጭቱን ሁሉ የሚወጣበት አንድ አጋጣሚ ያገኘ መስሎ ተሰማው።
በእርግጥም፤ አክሊሉ የቡድን ልጆችን እየመራና እያሠማራ፤ ራሱን ሽንጡን ገትሮ ጥሩ እየተጫወተ
ሲረቱ እንደቆዩ፤ ከሎው አጠገብ በድንገት ከካሣ ጋር ተጋጠሙ። «ሚናህን ብያለሁ፤ ውርድ ከራሴ
እንዳትለጋ!» አለው ካሣ እሩሩዋን በእጁ ቀልቦ። አክሊሉ፣ ወደ ኋላው ፈንጠር ብሎ ከልጉ ማምለጥ
ወይም ደግሞ ወደ ሚናው መግባት ይችል ነበር። ነገር ግን፤ «እስቲ ወንድ!» የሚል ስሜት ላንዳፍታ
ከቆመበት ቸኩሎ ያዘው። ሁለቱም ገናቸውን አንሥተው ዐይን - ለዐይን እንደተጋጠሙ፣ አክሊሉ
ከመመከቱ በፊት የካሣ ክንድ ውልብ ሲልና ሰማይ ምድሩ ሲጨልምበት አንድ ሆነ። ከዚያም በሳንሳ
ተሸክመው ቤት ሲያደርሱት ሁሉ አልታወቀውም ነበር። በሦስተኛው ቀን፤ ካሣ አክሊሉ ቤት መጥቶ
በመጠየቅ ክፋት አለማሰቡን ገልጾለታል። አክሊሉ ፈጽሞ አላመነውም። ማ ይሙት ሁለት ክንድ
በማይሞላ ርቀት የለጋበት ክፋት ባያስብ ነው? እማዋይሽ የተባለችውን ወዳጁን ከአንድ ወር በፊት
ሲወሽምበት ለእርሱ ሲል ደግ መሥራቱ ነበር? አክሊሉ ካሣን ስያነጋግር ፊቱን ወደ ግድግዳው አዙሮ
ሸኘው።
አንድ ወር ያህል ተኝቶ ተነሣ። ከቸቸላ እየተመለሠ መኃኒት የሰጠው ስመ ጥሩው የካይላ ዐዋቂ
የዳነ መሆኑን ቢያረጋግጥለትም፤ እንደወትሮው ሆኖ አለመዳኑን ለማወቅ ጊዜ አልፈጀበትም። በዚያ
ጉርምስናው ሆኖ አለመዳኑን ለማወቅ ጊዜ አልፈጀበትም። በዚያ ጉርምስናው፤ በዚያ በሚያውቀው ዐመሉ
የጎንደርን ቆነጃጅት ሲያይ፤ አንዳችም እንቅስቃሴ የማይሰማው በመሆኑ በመጀመሪያ ጥርጣሬ ብቻ ነበር 
ያደረበት። አይቶ፤ አይቶ ምናልባት ከሴት ወዝ ተለይቼ ስለቆየሁ ይሆናል ብሎ ገመተና ዱሮ
ወደሚያውቃት አንዲት ጋለሞታ ወዳጁ ዘንድ ሔደ። ምንም አልሆነም። የደጃች ክንፉ ባለሟሎች፤
በተለይም ካሣ እንዳያውቁበት በድብቅ እያጠያየቀ የዐይነ ጥላ ክታብ አሠረ። ጎንድ ተክለ ሃይማኖት
ጠበል፤ ዋንዛዬና አለፋ መዋት ሔደ። ሰሚ ሰው ነው ለተባለው ታቦት ሁሉ ተሳለ። መጽሐፍ ገላጭ፤
ቅጠል በጣሽ፤ ሥር ማሽ ዐዋቂ ጠየቀ። አልተሻለውም፤ በመጨረሻ ፍሬው መፍረሱንና መውለድና
መክበድ የማይችል መሆኑን ቁርጡን የነገረው አንድ የታወቀ የፈርንጃ ወጌሻ ነበር። ጉዱን ለቅርብ ጓደኛው
ስንኳ ሳይናገረው በሆዱ ውስጥ ቀብሮ ያዘው። ሌሎቹ የዕድሜ እኩዮቹ፤ ሲያገቡ ሲወልዱ ውሽማ ሲያበጁ
በጎንደር ጋለሞታ ሲደባደቡ የሱ እንዚያም ዝም የማለት ምክንያት እንዳይጠረጠርበት ወደ አንድ የገጠር
ደብር ሔዶ፤ ቅኔ ከቆጣጠረና እስከ ጾመ ድጓ ዜማ ካስኬደ በኋላ ጠምጥሞ ወደ ጎንደር ተመለሰ። እንደ
ዋዛ «ደብተራ አክሊሉ» የሚለው ስም ወጣለት።
አንድ የገላው ክፍል መሞቱን አክሊሉ ማመን ቢፈልግም፤ መንፈሱ ለአካሉ ጉድለት አልገዛለት
አለ። የሴት ወዝ ጥማቱ፤ የሥጋ ፍላጎቱ በተቀሰቀሰ ቁጥር እርሱ ይህን ዋና የሕይወት ክፍል የተነፈገበትን
ዓለም ‹አጥፊው› የሚል ስሜት ይገፋፋዋል። ዐቅሙን ገምቶ ሲመራመር ራሱንም ሲቆጣጠር አስተሠቡ
ከነገሩ መነሻ ላይ ያተኩራል። በካሣ ላይ። አዎ! ቀደም ሲል ባልቀደም ባይነቱ፤ ምኞቱን ጥላ
እንደጋረደበት ሁሉ በዚያ ገና ጨዋታ ደግሞ ወድነቱን ቀጥፎበታል። ዐይነተኛ የሕይወት ጣዕሙን
አጥፍቶበታል፤ የወደፊት ዕድሉን አበላሽቶበታል፤ ይህንን በደል እንደሚቀበል ከራሱ ጋር ደግሞ ደጋግሞ
ተማምሏል። ሲያስብ፤ መንገድ ሲፈልግ ቆይቶ ወደ ጋረድ የተጠጋበት ዋናው ምክንያት ይኸው ነው።
አክሊሉ፤ በራሱ ሐሳብ ተውጦ ለጥቂት ጊዜ ዝም ማለቱ ጋረድንም፤ በሞቃት ፈረሰ በራሱ ሐሳብ
እንዲጋልብ ዕድል ሰጥቶት ነበር.....እርሱም ካሣም የአንድ ቅድመ አያት ልጆች ናቸው። ግን ደጃች
ክንፉና ልጅ ኃይሉ የትና የት ተገናኝተው። ልጅ ኃይሉ ከቋራ ጎጥ ሳይወጡ ነው ያረፉት። አባቱ ደጃች
ክፉን ግን፤ ከርብ እስከ መተማ፤ ሰው ብቻ ሳይሆን ዛፍ ቅጠሉ ሳይቀር የሰገደላቸው መኮንን ነበሩ።
ጎንደር የሚገቡት ነጋሪት እያሽጎሸሙ ነበር። አክሊሉ እንዳለው ከትውልድ ትውልድ ሳያንሰው፤ ከጀግንነት
ጀግንነት ሳይጎድለው መልክ ከቁመና ጋር ሲኖረው፣ እንደ አዳኝ ውሻ ከፊት እየቀደመ ዕድሉን ምኝኖቱን
የነጠቀው ካሣ ነበር። ገና በአፍላ ጉልምስናው ተዋበችን ማግባቱ የሚከፍትለት የዕድል በር ወለል ብሎ
ታይቶት ነበር። ራስ አሊ እየሸመገሉ ሔደዋል። የሚተካ ወንድ ልጅ አልነበራቸውም። ዛዲያ አንዲት ሴት
ልጃቸውን ጋረድ ሲያገባ በእግራቸው የማይተካበት ምን ምክንያት አለ? ምንም! ግን ካሣ፤ ቋራና አዳኝ
አገር ወርዶ ባኮረፈ፣ ራስ አሊ ተዋበችን በሚስትነት ሰጡት። ተቀደመ፤ ዕድሉን ተነጠቀ፤ ደጃች ክንፉ
ሲያርፉ ሲሆን የጥንቱን «ማሩ ቀመስ» አገር፣ ያም ቢቀር የአባቱን ግዛት ለመሾም ተስፋ አድርጎ ነበር።
ግን አሁንም ደጃች ተድላ ጓሉን ሳይቀር ወደ መሃል ጎጃም ገፍቶ ቴዎድሮስ ወሰደበት። በኋላም አፄ
በጉበቱ ካሣ እየበረታ እቴጌ መነንና ራስ አሊ ድል ሆነው ከነመኳንንቶቻቸው ቢበታተኑ፣ ምንም ቢሆን
ሥጋ ነውና የአንድ ደጃዝማች አገር እንደሚሾመው ገምቶ ነበር። ግን ከባለሟልነት ቁም ነገር ስንኳ
ሳያስገባው፤ ከደጃች ውቤ ጋር ለመዋጋት ወገራ ሲዘምት ሳያስከትለው ቀረ። ካሣ ተቀብቶ አልተወለደም፤
ራሱን በራሱ ተቀባ። ወይስ አክሊሉ እንዳለው እኛ እንዲቀባ ተመቸነው?.....
«እና አሁንም የሆነ እንደሆነ የዚህ ዓለም ነገር ለኔ እንግዲህ ምኔም አይደለ። አንተ ብቻ....»
በማለት ጋረድን ከምኞት ሰመመኑ የቀሰቀሰው፤ ቀደም ብሎ ከሐሳቡ ያነቃአው አክሊሉ ነበር።
«እኮ ምናርግ ትለኛለህ? ተነሥቼ ልሸፍት ነው? በምን ሠራዊቴ ነው የማሸንፈው? ‹አያችሁት
ወይ ያንን እብድ፣ አምስት ጋሞች ይዞ ጉራምባ ሲወርድ› ሲባል እሱም ተዘፍኖበት ነበር። እና እንደ እሱ
አድርግ ነው የምትለኝ?» የጋረድ አጠያየቅ ብስጭት የሰፈነበት ነበር።
«አላልኩም።»
«ዛዲያስ?»
«ቀስ በቀስ ዕንቁላል በእግሩ ይሔዳል ተብሏል።»
«ሲቆምስ ገምቶ ይቀራል።»
«እንደሱማ እንዳይሆንማ ነው እኔም የምፈልገው።»
«እሺ ዛዲያ ምናርግ ነው የምትለው?»
«እንደዚህ ረጋ ብለህ ስንመካከርበትም መልካም» አለ አክሊሉ፤ የጋረድ ቅምጥ ሚስት ከጓዳ ገባ
ወጣ እያለች ለስንተኛ ጊዜ የቀዳችለትን አረቄ እየጨለጠ። «እየህ፤ ልጅ ጋረድ አንተ ጀግንነት አለህ
የሰው መውደድ አለህ። እንዳልከውም መኳንንቱ ሁላ ከተከፋእብት ተአሁኑ መንገድ ከፈተልህ ማለት
ነው። እሱ ባወቅ። እና አንተ ነገራችንን በሆድህ ይዘህ ውስጥ ውስጡን ተዘጋጅ፤ እየመረጥክ ሠራዊት
አሳድር፤ ወገራ መሾምህኮ ለዚህ ይረዳሃል። ከመኳንንቱም ወዳጅ አብጅ፤ አብዛ። ሌላውን ለኔ ተውልኝ።
የአንተ ወንድነት የኔ ብልሃት፤ የፈጣሪ ረድኤት አንድነት ሲሆን ግዴለህም» አለ አክሊሉ። የጋረድን ትከሻ
በማደፋፈር መታ መታ አረገውና። «ታንተ ቤት ‹እንኳን ደስ ያለህ› የሚል እንግዳ አልመጣም፤ አሁን
እንግዲህ ተገብርዬ ቤት እንሒድ» አለ።
«ምን› እንኳን ደስ አለህ ልለው እኔ ተገብርዬ ቤት?» ጋረድ ድምፁ ተስረቀረቀበት።
«ምናልባት?»
«በቁሜ ሙቻለኋ!»
«አልሞትክም፤ አትሞትም፤ አየህ ጋረድ፤ ‹ንጉሡ አንተን ሲሉ ለመላ አጎነበሱ› ሲባል
አልሰማህም። ሙያ በልብ ነው። ሔደህ ሸነገልከውና ራስህ ለራስህ ያለ ክብር አልተቀነሰ። ለራስህ ነገር
ስትል ዐውቀህ ነውና ያደረከው።»
«ባልሔድስ?»
«ብትቀር ገብርዬን አትጎዳው። ያሰብነው ነገር ደሞ አትጠመውም።»
«ምህኛቱን አስረዳኝ!» አለ ጋረድ ዐይኑን አያጉረጠረጠ።
«አየህ ገብርዬ ጦር አዝማች ተሹሞ የለ? ‹እሱን ቢያጣ የካሣ ኃይል ምን ይሆናል?› ብለህ
አስብ። ስለ ገብርዬ ሐሳብ አለኝ። ያች ምሽቱም ገና ባላገር ገራገር ናት አሉ። ስለርሷም ሐሳብ አለኝ።
እንዳልኩህ ብልሃቱን ለኔ ተውልኝ! እምነግርህን ስማኝ! አሁን እንሒድ!» አክሊሉ ጋረድን በጨርቁ ሳብ
አድርጎ ሲያስነሳው እንደ ገራም ከብት ተሳበለት።
ከቤት ወጥተው መንገድ ሲጀምሩ፤ አክሊሉ በሞቅታ ውጋገን ከሐሳቡ ቅኔ ፈለቀለት።
«......አያ ጋረድ ጅሌ ከጅልም ጅልሌ፤
አክሊሉ ሲያቀምስህ የምኞት አሞሌ
አጉል ስትጋልብ ወድቀህ ብትሰበር፤
መቸስ ምን ይደረግ እኔ እንደሁ ነገሬ ተዚያ ተከይሲ ጋር» የሚል።
በቅኔው ሥምረት ከራሱ ጋር ፈገግ አለ።
ታንጕት፤ ቀደም ሲል የነበረባትን ሐሳብ ዘንግታ ጭንቀት በሞላበት የደስታና የኩራት ስሜት
እንደዚህ ጊዜ ታውካ አታውቅም። የጎንደር መኳንንትና ወይዛዝር፤ ሹመት የሚፈልግ ደጅ ጠኝ ሁሉም
አሁን ሚዛኑን አይቶ እንደ ዐቅሙ የሹመት መጠየቂያውን እያስያዘ መጉረፍ ጀመረ። ከበድ ያልን
መኳንንት ነን የሚሉ አንድ ሁለት መኳንንት ሽህር ከብት እያስነዱ መጡ። ከነሱ መለስ ያሉት ሌሎች
ብዙዎች መኳንንት ወይዛዝርት ከሙክትና ከሽህር ጋር ማድጋ ጠጅ እያሸከሙ መጡ። አብዛኞቹ ዝቅ
ያሉት ደግሞ ዐሥርና ሃያ እንጀራ ከስድት ወጥ ጋር የሆነላቸውም ገምቦ ጠጅና ጠላ አብረው አስገቡ።
ባዶዋቸውን እየፎከሩ፣ እዬሸለሉ፤ እልል እያሉ የገቡም ነበሩ።
ገብርዬ፣ ከበር ውች ሰዎችን እየተቀበለ፤ ‹እንኳን ደስ አለህ› ሰላምታቸውን በምስጋና እየመለሱ
ሲያስተናግድ፤ ከውስጥ ታንጕት ጉዳ የሚገባውን የበሰለ ነገር ከበለጡ ጋር ከጎረቤት የመጡ የቤት
ሠራተኞችን እያመላከተች በየሥፍራው እንዲቀመጥ ታደርጋለች።
ምን የመስለ ሙክት፤ ማድጋ ጠጅ፤ ሞሰብ እንጀራ፤ ከሁለት ድስት የዶሮ ወጥ ጋር ይዘው
የመጡት አንድዋ ወይዘሮ፣ ከሁላ ራሳቸው እንዳስተዋወቁት ወይዘሮ ደብሬ የሚባሉ ነበሩ። ገብርዬን
በተገቢው ከበሬታ ‹ሹመው ያዳብር› ካሉት በኋላ ውስጥ የተቀመጠውን ሁሉ እጅ ነሥተው እንደቆሙ፤
ታንጕትን ጥቂት አስተዋሏት። ቁመታቸው ብዙ ወንዶችን ወደ ታች ሊያስመለክታቸው የሚችል ቢሆንም
በደጓሣ አጥንትና ይህንን ባለበሰ ሙሉ ሥጋ ተውጧል። ግን ከፊት የቦርጭ ወይም ከሁላ የዳሌ ግርጌ
ግፊት አይታይባቸውም። መላ ቁመናቸው ተመጣጥኖ፣ ተስተካክሎ የወጣ ነው። ወደ ቀይ ዳማ የሚያደላው
መልካቸው፤ አሁን የዕድሜ መሥመር ቢታይበት፤ በጊዜው ብዙ ወንድ ያፋጅ እንደነበር ያስታውቃል።
ዐይኖቻቸው አሁንም እንደ ኮረዳ የሚቁለጨለጩ ብሩህ ናቸው። በዚህ ላይ እንደ ተለመደው የጎንደር
ወይዛዝርት ሹርባ ሳይሠራ፤ ወይም በሻሽ ሳይታሰር በእንዝርት ዛቢያ ነቀስ እንቀስ ተደርጎ የተዘረዘረ
የሚመስለውና እንደ መስከረም አደይ አበባ፤ ሽበት በልግሥና ከተበተነበት ጎፈሪያቸው ጋር፣ የለበሱት ሰፊ
አረንጓዴ ጠለት ቀሚስና ድርብ ኩታ፤ ደርባባነታቸውን ተጨማሪ ግርማ ሰጥቶታል። «ኧረ ባባጃሌው!
አንቺ ነይ እንጂ ሣሚኝ!» አሏት ዓመት ሙሉ ናፍቆት እንደ ከረመ አክስት።
ታንጕት፣ የቴዎድሮስ ማስጠንቀቂያ ትውስ አላትና፣ ድንገት አዳኝ እንደ አየ አውሬ በድንጋጤ
ወደ ኋላ በስሜት በረገገች። ወዲያው ትኩር ብላ ስትመለከታቸው ፈገግታቸው ሳባት። ጥርሶቻቸው እንደ ካላቸው ደጓሣ ናቸው። በሌላ ሰው ፊት ላይ ቢሆኑ ፍልጥ ጥርስ ይባሉ ነበር። ነገር ግን፤ በወይዘሮ ደብሬ
ላይ ቢሆኑ ትልልቅ አልመሰሏትም። አብረው የሚሥቁ ከሚመስሉት ዐይኖቻቸው ጋር ተቀናጅተው አንዳች
የፈካ ማሽላ አበባ፤ ቃሙኝ ቃሙም እያሉ የሚጋብዙ ዐይነት ናቸው። ዕድሜ የዘረጉባቸው የፊታቸው
መሥመሮች ስንኳ የሚስብ አንዳች ውበት ነበራቸው። «ኧረ ባባጃሌው ነይ እንጂ!» ሲሏት ድጋሚ፣ ጠጋ
ብላ ጉንጯን እያገላበጠች ሰጠች። ባዳ እንደሚስማት አልቀፈፋትም። በኋላ ቆይታ ስታስበው ራሷም
ገርሟታል። ብዙ ጊዜ የተለየችው ሰው የተገናኘች መስሎ ነበር የተሰማት። «በይ ሒጂ ወደ ሥራሽ!»
ብለው ወደ ማድቤቱ ገፈተሩዋት።
ታንጕት፤ ጉዳ - ገባና ወጣ እያለች ስትመለከት ወይዘሮ ደብሬ ሁሉንም የሚያውቁ፣ ሁሉም
የሚያውቃቸው ይመልስ ከሁሉም አቅጣጫ ጨዋታ እየቀረበላቸው ከሁሉም ጋር ተዝናንተው
ጭውውታቸውን ቀጠሉ።
ከጥቂት ጊዜ በኋላ ተከትለዋት ጓዳ ገቡ። «ኧረ ባባጃሌው ምን እያረግሽ ነው አንቺ ልጄ!»
አሏት ከልብ የተቆጣ የማይመስል ፊታቸውን አኮሳትረው።
ታንጕት፤ ምን አገባዎት የሚል ቁጣ ከጀላትና አወልጣላት አለ። «ምነው?» አለች በመገረም
ጥያቄ።
«እኮ ምን እየሠራሽ ነው?» አሉ ወይዘሮ ደብሬ፣ እንደ ልጅ ለመቆንጠጥ ይመስላል ጣታቸውን
ወደ ጉንጭዋ እየዘረጉ።
«ምን ሠራሁ?» ታንጕት አሁንም ጥርጣሬዋና የአቀራረባቸው ድፍረት ያሳደረባት ስሜት ጨርሶ
አልጠፋም። ግን አሁንም የቁጣ ፊት ማሳየት አልቻለችም።
«አንቺም፣ እሱም» አሉ ገብርዬ ወደ አለበት ወደ በሩ በዐይናቸው እያመለከቱ፣ «አዬ እናንተ
የጫካ ሰዎች ነገር። ዝም ብላችሁ ሰውን ሁሉ ባንድነት በመደዳ ታስቀምጡታላችሁ?»
ታንጕት ነገሩ ስላልገባት በጥያቄ መልክ ተመለከተታቸው።
«አየሽ!» አሉ ወይዘሮ ደብሬ ጠጋ ብለው በማንሾካሾክ፣ «ሰው እኮ የሚጨዋወተው ከመስሉ ጋር
ሲሆን ነው። ታለ ማዕረጉ ሱጥሉትም አይለውም። መሸስ ይኸው ነው፤ ጎንደሮች፣ ተኔ ጀምሮ የለመድነው
ወግ።»
«አሁን ዛዲያ ምን ላርግ?» አለች ታንጉት፣ ሁሉም እንደገባ ባገኘው እንደ ተቀመጠ ገብቷል።
«አሁንማ ምን ታረጊያለሽ። ከተቀመጠበት ተነሡ ማለት የባሰውን ማስቀየም ነው። እንግዲህ
የተቀመጠው እየወጣ ሲሔድ አዲስ የሚገነባውን እንደ ምንም ማድረግ ነው። እናንተ መቸም
አታውቋቸውም፣ እኔ ላግዛችሁ?» ሲሉ ጠየቋት። ታንጕት፣ ግራ ከሚያጋባት ከዚህ ሁናቴ ይልቅ ወደ ጓዳ
ሥራዋ መመለስዋን አልጠላችውም።
ወይዘሮ ደብሬ የአዳራሹን አስተናባሪና እንደ ባለቤት ይዘው ጥቂት ከቆዩ በኋላ፤ አሁም ጓዳ ገቡና
አሁንም በውሸት ቁጥ ዐይናቸውን በታንጉት ላይ አፈጠጡባት። «ምነው እማማ?» አለች ታንጕት የመጨረሻው ቃል ሳይታወቃት ወጥቶ፣ እንዳጠፋ ሕፃን
በሚመስል ጥያቄ።
«ኧረ እንዲያው ምናችሁም አያምረኝ!» የተማረሩ መሰለ።
«እህ! ምን አረግነ አሁን ደሞ?»
«ምን አረግነ? ምግቡን መጠጡን ዝም ብላችሁ እግረ መንገዳችሁ እንዳደረሳችሁ አይደል
የምታቀርቡት?» ሲሉ ወደ በለጡ ወደ ሌሎችም የቤት ሠራተኞች ጣታቸውን ቀስረው ጠየቁ። ከታንጕት
ጀምሮ ሁሉም ነገራቸው እንዳልገባቸው ከአስተያየታቸው ያስታውቅ ነበር። ለጥቂት ጊዜ ተፋጥጠው ቆዩ።
«ኧረ ባባጃሌው! መቸም የተሰናዳ ምግቡም መጠጥም በቤት አለ!» ሲሉ በመጠየቅ ሳይሆን
በማረጋገጥ ዐይነት ጠየቁ።
«አለ እንጂ!»
«ዛዲያ እሱ ብቻ አይደለ ለመጣው ሁሉ የሚቀርብ! ለሁነኛው፤ ለቤተኛውስ ምን ይትረፈው
ብላችሁ ነው። ደግሞስ የመጣው ምግብና መጠጥ ሁሉ አውጥቶ አይጣል! ምን እየሰራችሁ ነው?» ሲሉ
አፋጠጡ።
«ተሱምኮ እያቀረብን ነው» አለች በለጡ።
«እሱንማ አይቻለሁ። እግር እንደጣላችሁ፤ ጠላውን ተዚያ፣ ጠጁን ተዚህ ዶሮ ወጡን
ለዚያኛው፣ ሥጋውን ለዚህኛው --- የቱ፣ የት እንደሚቀርብ ሳታዩ?»
ከታንጕት ጀምሮ ሁሉም በሐሳብ እንደ ማቀርቀር አሉ። «ቅድም ሰው እንደመለሱ እንዳልኩት
ነው። እንዳይበላሽ የመጣው መበላት መጠጣት አለበት። ግን እንደመሰሉም ሲባል፣ አንድ ሰው፣
ያመጣውን ምግብ መልሰሽ አታቅርቢለትም። ይኸ ያመጣውን ለዚያ እየተደረገ ነው።» በጓዳ
የተደረደረውን ከወዲያ ወዲህ ቃኙ። «ሞልቷል። ተብለቶ፣ ተጠጥቶም አያልቅ። አሁን እንግዲህ
አሰናዱትና አመለክታችኋለሁ! እሺ?» አዲስ እንግዳ ለማስቀመጥ ወደ አዳራሹ ተመለሱ። ታንጕት፣
«ወቸ ጉድ! ‹ሳይደግስ አይጣላም› አሉ?» እያለች በሐሳብዋ ከሠራተኞቹ ጋር በመገረም ተያየች።
ወደማምሻ አቅራቢያ አንግዳው ጥቂት ቀለል ማለት ሲጀምር፣ ገብርዬ፣ ‹ስቲ አባ ታጠቅን
አይቸው ልምጣ። በዚያው ተነ ዓለሜ ብቅ ልበል› ሲላት እንደ መጀመሪያው ቢኖር ኖሮ ታንጕት፣ ‹እኔን
ብቻየን ጥለኸኝ› ስትል በተጨነቀች ነበር። አሁን ግን ‹እንዳፈቀደህ!› አለችው።
ከግቢው ትንሽ ፈቀቅ ብሎ ጋረድና አክሊሉ እጆቻቸውን እያወዛወዙ በመከራከር ላይ ነበሩ።
ጋረድ፤ የገብርዬን ቤት ብሩቅ ሲመለከት ድንገት ሐሳቡን ቀይሮ አልገባም ብሏል። የሰጠው ምክንያት ባዶ
እጃቸውን መምጣቱ ነውር መሆኑን ነው። ትንሽም ይሁን ትልቅ አንዳች ነገር ይዞ ቢመጣ ደግሞ፤ እንደ
እጅ መንሻ እንደሚቆጣጠርበት፣ ይህም የባሰውን ቢመጣ ደግሞ፤ እንደ እጅ መንሻ እንደሚቆጠርበት፣
ይህም የባሰውን ለርሱ ውርደት መሆኑን ግን ሕሊናው ይነግረው ነበር።
«ኤዲያ! እኔ ቁም ነገረኛ መስለኸኝ» አለ ደብተራ አክሊሉ በንዴት አነጋገር። «ወትሮውውንስ -
- ወትሮውንስ!» ሳይጨርስ ተወው።
«አሃሃ! ይች ባቄላ ያደረች እንደሆነ አትቆረጠምም» አለ ጋረድ በሞቅታ ቁጣ። «ዐቅምህንም
የረሳህ መሰለኝ!»
የአክሊሉ አንደበት ወዲያ ለዘብ አለ። «ምናረኩ?»
«እንዲህም ትናገር ጀመር?»
«እኔ መቸስ ላንተ ለአብሮ አደግ ወንድሜ ብዬ ነው እንጂ፤ ደሞ ሰው ተወንድሙ ጋር ሲጫወት
እንደ ባዳ አፉን አይቆጥብ!»
ገብርዬ ከአጠገባቸው ሲደርስ ንግግራቸውን አቆሙ።
«ምነው በዛሬው ቀን ብቻችሁን ጎዳና ላይ ቁማችኋል ልጅ ጋረድ? ኧኸ ፊታውራሪ ልበልህ
አንጂ!» አለ ገብርዬ የእግዚአብሔር ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ።
«እኛማ ወደርስዎ ቤት መመጣችን ነበር» ሲል ደብተራ አክሊሉ ቀድሞ መሰለ። ጋረድ በክፉ
ዐይን ገረፍ ቢያደርገውም ሊያስተባብል አልከጀለም።
«ኑዋ ግቡ!» ገብርዬ እጁን በመዘርጋት መራቸውንና የሚተዋወቁበትን ጊዜና ሥፍራ ለማስታወስ
የሚሞክር ይመስል አክሊሉን ትኩር ብሎ ተመለከተው። «መሪጌታ አክሊሉ አባታችን ቤት፣ ተኔም
ተካሣም ጋራ አብሮ አደጋችን ነው። አሁን ተኛ ተለይቶ የሎዛ ማርያም አልቃ ሆኗል» ሲል ጋረድ
አስተዋወቀው። ‹ቴዎድሮስ ብሎ መጥራትም ይቀፈዋል ማለት ነው?› አለ ገብርዬ በሆዱ። ቴዎድሮስና
ጋረድ የሥጋ ወንድማማቾች ቢሆኑም የደጃች ክንፉ ልጅ በመሆኑ ብቻ ጋረድ ምኞት እንዳለው በዚህም
ምኞቱ ምክንያት ከርሱ ልቀው በሚያያቸው ላይ ሁሉ ምቀኝነት እንደሚያድርበት ሰምቷል።
ቴዎድሮስ ራሳቸው የጋረድ ነገር ሲነሣባቸው ‹ምን ኤዲያ! አይረባም። አጉል መንጠራራት ብቻ
ነው። አሁን እሱ የክንፉ ልጅ ነው? ተምናቸውም የለ። እበት ትል ይወልዳል ነው፤ ለነገሩማ ተርሱ
የቀረበ ወንድም መቸ ነበረኝ!› ይላሉ። ወገራንም የሾሙት እስቲ ተሞክሮ ይታይ በሚል ሐሳብ
ይመስላል። ገብርዬ ስሜቱን በፊቱ ላይ አላሳየም።
የቴዎድሮስ ዘመድ በመሆኑም ይሁን ወይም የኩራት ስሜቱን ስለሚያውቁ፣ ከገብርዬ ቤት
የነበሩት ሰዎች ሁሉ ለጋረድ የአክብሮት ሰላምታ አቀረቡለት። ገብርዬ ታንጕትን ጠርቶ አስተዋወቃት።
«ልጅ....እህ? ፊታውራሪ ጋረድ ማለት እሱ ነው። መቸም ወሬውን ሰምተሻል።» ታንጕትስ ስለ መልከ
መልካምነቱ ሰምታ ነበር። ረጅም፣ ቀይ ጸጉረ ዞማ፤ ከአፍንጫው፤ ከከንፈሩ ከዐይኑ ይህ ጎደለው
የማይባል የጎንደር ወይዛዝርት ሁሉ የሚፈዝበት ነው እየተባለ ይነገርለት ነበር። ግን አሁን ስታየው ብዙም
አላስደነቃትም። ባትጠላውም አልወደደችውም። ይህ ነው ብላ የአትጠቁመው አንዳች ነገር የሚጎድለው
ተሰማት። ምናልባት ከፈገግታው ይሆናል። ጥርሶቹ ውብ ቢሆኑም ከንፈሩን ገለጥ ሲያደርግ የሚያሽሟጥጥ
ያስመስለዋል። ደብተራ አክሊሉን ግን ከነአካቴውም በሚገባ አልተመለከተችውም።
«እንደምን ሰነበቱ ወይዘሮ ደብሪቱ?» አላቸው ጋረድ። «እንዴት ከረምሽ አለኝ እንጂ! ኧረ የት ጠፋህ?! አላደርስህ አለ ማዳረሱ?» አሉት በቀልድ
አሽሙር።
«በቀደም መጥቸ አጣሁዎት።»
«እኔን ልትጠይቅ? ወይስ ያችን ሞለፈጥ? ኧረ ባባጃሌው!» አለ ወይዘሮ ደብሪቱ፤ የሚማጠኑ
ይመስላል በቤት ያለውን ሰው እየቃኙ። «እኔስ ዲቃላ ማሳደጉ ሰለቸኝ። እሷ ተቤት ተቋጥራ ስትቆየኝ
እሱ ተጎረቤት ይዞ ሲመጣ በመሃል ቤት እኔ.... ብቻ ግዴለም ጸጋ ነው።» አንድ ወንድና አንዲት ሴት
ልጆቻቸውን ማለታቸው ነበር። ሰዉ ሁሉ ሣቀ። ታንጕት አብራ ከት አለች። ‹ስለ ልጆቻቸው በሰው ፊት
እንዲህ ሲናገሩ አያፍሩም? ወቸው ጉድ!› እያለች በሆድዋ።
በመካከሉ ገብርዬ፣ «በሉ ተጫወቱ» በማለት እንደ ዘበት ወጣ።
«ወይዘሮ ታንጕት፣ አባቴን ያውቁታል?» ሲል ጋረድ ድንገት ጠየቃት ገብርዬ አለመኖሩን
ከአረጋገጠ በኋላ።
ለምን እንደ ጠየቃት ምክንያቱ ለጊዜው ሊገባት አልቻለም። ‹ስለኔ የሚያውቀው ነገር ይኖር
ይሆን? ታወቀስ በአሽሙር መንካቱ ነው? ወይስ አባቱን ድፍን አገር የሚያውቃቸው መሆኑን ለማስረገጥ?
ወይስ እኔን ለማነጋገር የሚያወራው ሲጠፋው?» ከሐሳብ ጥያቄዋ ተመልሳ «ኧረ የታባቱን ዐውቄያቸው?»
አለች።
«እጅግ ታላቅ ሰው ነበሩ። በዛ ሲባል» አለ ጋረድ ደረቱን እንደ መንፋት እያደረገ። «ካሣን
እንደዚያ አርገው ያሳደጉትና ለዚህ እንዲበቃ ያደረጉት የኔ አባት ናቸው።» ደረቱን በእጁ መታ መታ
አደረገ። «የኔ አባት ባይኖሩ ኖሮ ካሣ ይኸኔ፣ ገብርዬም ቢሆን....»
አክሊሉ ጎንተል አደረገው። ጋረድ ከዚህም ከመጣ በኋላ ያከለው ጠጅ የቆየ ሞቅታውን አብሶበት
በከፊል ከራሱ ጋር የሚወጋ መስሎት ነበር። «እህ?» ብሎ እንደ መባነን ሲል፤ አክሊሉ ከወይዘሮ ደብሪቱ
ጋር ሌላ ጭውውት ለጠቅ አደረገ።
«ወይዘሮ ደብሬ፣ ምነው ሎዛ ማርያምን ረሱዋት?»
«ኧረ ባባጃሌው!! አምና ሁለት ማድጋ መገበሪያ ስንዴ አላመጣሁም መምሬ?»
«መገበሪያ መች አጣና! ባላገር ሁሉ የሚያመጣው ነው። ሲሆን ድባብ፤ ታለበለዚያ የባሕር
ማዶውን የሐር ጥላ ነው እንጂ!»
«አዬ መምሬ! ደንቢያን የምገዛ መሰልኩዎት!»
«ማሩ ቀመሰ ደንቢያን ይዞ ያባቴ ግዛት ነበር!» አለ ጋረድ በመካከል ገብቶ።»
ብዙዎች ሰዎች ሞቅታውን ስላወቁ በትዝብት ፈገግታ ይመለከቱታል። አንዳንዶቹም በጥርጣሬ
ያስተውሉታል። የቴዎድሮስን የፍቅር ልብ ለማግኘት ሲል በማስመሰል ነገር ሊያወጣቸው እንደሆነስ?
ቴዎድሮስ ራሳቸውን አልባቤ ሰው መስለው ከሥፍራ ሥፍራ በመገኘት ስለ አስተዳደራቸው ሕዝብ
የሚለውን ያዳምጣሉ የሚል ሐሜት አለ። መቸም ቢሆን ሥጋቸው ነው። ማን ያውቃል? ማን ይሞኛል? የጋረድ ስሜት ግን ሆድ ያባውን ብቅል ያወጣዋል ዐይነት ነበር። ከቴዎድሮስ ጋር ከአሁን ተፊት
ለፊት ድፍረቱ ለመፈታተን ፈልጎ ሳይሆን የማመዛዘን ችሎታቸውን ደብዘዝ ያደረገበት ሞቅታ እንደ ፈለገ
ብቻ ያናግረዋል። «አንቺ ታላጣው ሹመት አንቺንስ ለምን አልሾመሽም እንደኔ?» አለ ጋረድ እጁን ወደ
ታንጕት እያጣቀሰ።
«ኦሆሆ!» ብላ ታንጕት ወደ ጓዳ በር ገብታ ተጋረደች።
«ኧረ ባባጃሌው! ሴት ደሞ ልትሾም? አንተስ ጉደኛ እየሆንክ ሔደሃል። አባትህ ይሄን ጉድ
አላዩ» አሉ ወይዘሮ ደብሬ ለመጀመሪያ ጊዜ ከልብ የተኮሳተሩ መስለው። ግን ይህም በሙሉ
አልተዋጣላቸውም። ቁጣችው ከልባቸው አለመሆኑ የሚያሳጣቸው ከዐይን አገላለጣቸው፣ ከከንፈር
መሥመራቸው አንድ ልዩ ምልክት ያለ ይመስላል።
«ለምን አትሾምም ይኸው ተዋበች ተሹማ የለ?» አለ ጋረድ በመጠጡ ኃይል ርግጥ አድርጎ፤
«ያውም የመጨረሻውን!»
«ኧረ ባባጃሌው፤ ያ ሌላ ይኼ ሌላ» አሉ ወይዘሮ ደብሬ ነገሩን በማቃለል።
ብዙ ሰው ግን ግራ ተጋብቶ፣ ተገርሞ ዝም አለ። የጋረድ አሽሙር የታንጕትንም እንደ መርፌ
ጠቅ አደረጋት። አዎ፤ እርሷም በአደባባይ ክብርና ማዕረግ ማግኘቱን ትወደው ነበር። ግና አላገኘውም።
እርግጥ አባ ታጠቅ እንደልጅ አሳድጎ፤ ከዚያ ባላነሰ ፍቅር እንደሚያመለክታት ይታወቃታል። ከዚህ
በተረፈ ግን የፍቅሩ መሠረት ለሰው በግልጽ አይታወቅም። እንዳሳደጋት የቤት በምሥጢር ነው። ዛዲያ
ፀሐይ ካላየው ወዳጅና ጠላት ካላወቀው ምን ርባና አለው? ተዋበች ግን ከርሷ በኋላ መጥታ እንሆ ጋረድ
እንዳለው በአደባባይ የመጨረሻውን ቀሚስ ለብሳለች። ታንጕት ከዚህ ሐሳብ ላይ ስትደርስ፣ ራሷን ይዛ
እግዚኦ ማለት ቃጣት፤ እንደ ትልቅ እህት ትወዳታለች። ለካሣ መንገር የማትደፍረው ግን እንዲሆንላት
የምትፈልገውን የምታማክረው ለተዋበች ነበር። ካሣን፣ የአሁኑን ቴዎድሮስ ከራስዋ ይልቅ ተዋበች
እንደሚረግፍ አበባ ተንከባክባ እንደምትይዘው ታውቃለች። ‹ታዲያ እኔ በተዋበች ማዕረግ ልቅና?› ስትል
ራሷን ጠየቀችና ራሷን በምሬት ለመውቀስ ሞከረች። ወዲያው መልሳ፤ ‹ግና ደግሞስ እኔስ ብሆን›
የሚለው ጥያቄ ከጋረድ አነጋገር ጋር አስማማት። ሐሳብዋን ሁሉ ሲማታባት፤ ወደ ጓዳ ገብታ
በተደረደረው ምግብና መጠጥ መካከል ዘፍ አለችና፤ አገጭዋን በመዳፎቿ አስደግፋ ዝም ብላ ተቀመጠች።
በአካልም፤ በሐሳብም ደከማት። ከአዳራሹ የሰው ንግግር ይሰማታል።
ጥቂት ቆይቶ ቅልል ሲላት፤ በአንዳች ዐይነት ምሥጢር ያውቁ ይመስላል ወይዘሮ ደብሬ
መጡና፤ «ኧረ ባባጃሌው! ነይ እንጂ እንግዳሽን ሸኝ!» አሏት። የድካም ፈገግታ እያሳየች ተከተለቻቸው።
ጋረድ ቀደም ሲል በአክሊሉ ተገፋፍቶ ወጥቶ ስለ ነበር አላገኘችውም። «ያ ቋረኛስ እንደሆነ
እየቀባጠረ ሔዷል» አሏት ወይዘሮ ደብሬ ሐሳቧን የተረዱ ይመስል። ሌሎችም አንዳንዱ፤ ከአንገቱ
ቀልበስ፤ ሌላው ከትከሻው ሰበር፣ ወይም ከወገቡ አጠፍ እያለ ተሰናብቶ አለቀ።
«በይ እንግዲህ እንዳሻሽ!» አሉና በመጨረሻው ወይዘሮ ደብሬ ተሰናበቷት።
«መሔድዎ ነው!»
«ኧረ ባባጃሌው! ዛዲያ ከዚህ ላድርልሽ ነው?»
እንግዶች ሁሉ ሔደው፤ ሠራተኞች ሁሉ ተሰናብተው ታንጕት ከበለጡ ጋር ብቻቸውን ከቀሩ
በኋላ፤ «ጉድ አይደለም?» አለቻት።
«ኧረ! እሜቴ ደስ የሚል ዓለም ነው!» አለች በለጡ በመቅበጥበጥ።
ከዚህም ከዚያም ስታሟላና ስታገላብጥ ቀማምሳ ነበር።
«ዝብርቅርቅ አልሆነብሽም በለጡ?» አለች ታንጕት በአብዛኛው ከራሷ ጋር። የወይዘሮ ደብሬን
ከጋረድ ጋር፣ ብዙ ከማይናገረው የሎዛ አለቃ እየፎከረ ለያዥ ለገላጋይ አሰግሮ የተሰኘው አንድ ደጅ
ጠጥቶ --- የገብርዬን አሽከር ሲል እየፎከረ ለያዥ ለገላጋይ አስቸግሮ የተሸኘው አንድ ደጅ ጠጅ መሳይ
ጋር ሁሉንም አነጻጸረችው።
«ኧረ ቢሆንም ውብ ዓለም ነው» አለች በለጡ በድጋሚ። «ምንም አልቀመሱትም እኮ እትዬ!»
ስትል ብርሌ ጠጅ አመጣችላት።
በእውነት ጉሮሮዋ ደርቆ ነበር። በአብዛኛው በሐሳብ። ጎንጨት አደረገችና፣ «ምኑን እናውቃለን
ብለሽ። እስቲ መጨረሻውን ያሳምረው» አለች።
#ምዕራፍ ሁለት ይቀጥላል 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

አይሰው

እቴጌ ጣይቱ ብጡል (ብርሀን ዘ ኢትዮጵያ)