መሲሁ

 ስለ መሲሑ የዓለም መድኅን ኢየሱስ
ክርስቶስ መወለድና የበዓሉ አከባበር፤
ዝርዝር ሐተታ ከመሄዳችን በፊት ገና ማለት ምን ማለት እንደሆነ
ትርጉሙ እነሆ፡፡
ገና ማለት ከጽርዕ /ግሪክ/ ቋንቋ የተወረሰ ነው፡፡ 
ትርጉሙም ልደት ማለት ነው፡፡
እንደሚታወቀው ሁሉ አዳም አባታችን ወዶ በሠራው ኃጢአት
ምክንያት የዓለም መድኅን ኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ተወለደበት
ጊዜ ድረስ ዓለም በጨለማ ጒዞ ይጓዝ ነበር፡፡ /ኢሳ. 9፡2/
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተወለደ በኋላ ግን
በጨለማ ጥላ ሥር ይንከራተትና ፍዳውን ይቈጥር ይኖር
የነበረ ሕዝብ ብርሃን አየ፤ ተስፋ ያልነበረው ሕዝብ የተስፋ
ባለቤት ሆነ፣ የጨለማና የኀዘን የሥቃይ፣ የፍዳ፣ የገፊና
የተገፊ መናኸሪያ የነበረው አሮጌው ዓለም በክርስቶስ
ኢየሱስ አዲስ ዓለም ሆኗል፡፡ /ኢሳ. 9፡2፣ ሮሜ.13፡12/
2. ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ ወደዚህ ዓለም
የመጣው ለምን ይሆን?
ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን ብዙ ብዙ መንፈሳውያን
አባቶችና የዓለም ሊቃውንት ብዙ ብለዋል፡፡ ብዙ ጽፈዋል፡፡
የሁሉንም ሐሳብ አጠቃሎ የምናገኘው ግን እነሆ እውነቱን
ከሐሰት በመለየት አምላካዊ ቃል ብቻ የያዘ ቅዱስ መጸሐፍ
ሲሆን እሱም ትንቢቱን ከፍጻሜው ፍጻሜው ከትንቢቱ
በማገናዘብ የትንቢቱ ተናጋሪና የትንቢቱን ፍጻሜ ምዕራፍና
ቁጥሮች በትክክል በማያሻማ መልኩ እንደሚከተለው
ቀርቧል፡፡
3. ትንቢት ማለት ወደ ፊት
የሚሆነውን፣ ወይም የሚመጣውንና ጊዜው ሲደርስ
የሚፈጸመውንና ጊዜው ሲደርስ የሚፈጸመውን ነገር ገና
ከመድረሱ በፊት የማወቅ ዕድልና ስጦታ ነው፡፡
በዚህ ቃል የሚጠቀሙበት መጽአያትን ሁሉ አስቀድመው
አውቀው፣ በእንደዚህ ያለ ዘመን ውስጥ እንዲህ ይሆናል፡፡
ብለው ትንቢት የሚናገሩትን አዋቂዎች ነቢያት ተብለው
ይጠራሉ፡፡ ትንቢትም ሲባል በሁለት ክፍል የተመደበ ነው፡፡
1. በእግዚአብሔር መንፈስ ለሰው ልጆች የሚገለጽ ትንቢትና
ራእይ፤
2. ለጥቅም ፍላጎት ጸላዕያነ ሠናያት ከሆኑ ከልዩ ልዩ ረቂቃን
መናፍስት የሚገኝ ሐሰተኛ ትንቢት ነው፡፡ በሁለተኛ ቊጥር
የተጠቀሰው የትንቢት ዓይነት ጥንቆላ እንጂ ትንቢት ሊሆን
አይችልም፡፡
እንግዲህ የሐሰቱን እንተወውና ወደ እውነተኛው ትንቢት
እንሻገር፡፡
አዳም በእባብ ምክንያት ከምድረ ርስት /ገነት/ ቢሰደድም
እግዚአብሔር አምላክ ግን አልተወውም፤ በኋለኛውም ዘመን
እንደሚያድነው ለዚህም የባሕርይ ልጁን ተቀዳሚና ተከታይ
የሌለውን አንድያ ልጁን እንደሚልክ፣ የድኅነት ተስፋ ሰጥቷል፡፡
የአዳም ልጆችም ይኽንን የድኅነት ተስፋ ቀን ለማወቅና
ለመረዳት ፈልገው ያች የሚወለድባትን /የድኅነት/ ቀን
ለማግኘት እኩሌቶቻቸው በጨረቃ፣ እኩሌቶቻቸው ደግሞ
በከዋክብት፣ በፀሐያዊ ብርሃን ሲቈጥሩ ኑሯል፡፡
እግዚአብሔርም የዘመኑ /የመከራ መዋዕል/ ፍጻሜ በደረሰ
ጊዜ የወዳጆቹ ትንቢት ይፈጸም ዘንድ አንድያ ልጁን ወደዚህ
ዓለም ላከ፡፡ /ዮሐ. 3፡16/
4. ትንቢት
1. በአንተና በሴቲቱ መካከል በዘርህና በዘርዋ ጠላትን
አደርጋለሁ፡፡ ርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፡፡ አንተም ስኮናውን
ትቀጠቅጣለህ፡፡ /ዘፍ. 3፡15/ እግዚአብሔር፤
2. ከአንተ መካከል ከወንድሞችህ እንደኔ ያለ ነቢይ
ያስነሣልሃል፣ ርሱንም ታደምጣለህ፡፡ /ዘዳ.18፡15/ ነቢዩ
ሙሴ፡፡
3. የምድር አሕዛብ ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ /ዘፍ. 22፡18/
እግዚአብሔር፡፡
4. አየዋለሁ አሁን ግን አይደለም፣ ከያዕቆብ ኮከብ
ይወጣል /ዘኁ.28፡17/ በዓለም፡፡
5. እነሆ ድንግል ወልድን ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል
ትለዋለች /ኢሳ.7፡14/ ነቢዩ ኢሳይያስ
6. "ሕፃን ተወልደ ለነ ወልድ ተውህበ ለነ" ህፃን
ተወልዶልናልና ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና አለቅነትም
በጫንቃው ላይ ይሆናል /ኢሳ.9፡6-7/
7. አንቺ ቤተልሔም ኤፍራታ ሆይ .... ከአንቺ አወጣጡ
ከቀድሞ ጀምሮ ከዘለዓለም የሆነ በእስራኤል ላይ ገዥ
የሚሆን ይወጣልኛል /ሚክ. 9፡9/ ነቢዩ ሚክያስ፡፡
8. አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ እጅግ ደስ ይበልሽ /ዘካ.9፡9/
9. ነቢዩ ዳንኤል የተናገረው የተነበየው ጌታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ ስለሚወለድበት ጊዜና ስለሚጠመቅበት፣ ራሱን
አሳልፎ ስለሚሰጥበት፣ ከሰው ልጆች ጋር ቃል ኪዳን
ስለገባበት ጊዜ ለይቶ ያስረዳል፡፡ /ዳን. 7፡25-28/
5. ፍጻሜ
1. የዘመኑ ፍጻሜ /ቀጠሮ/ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ልጁን
ላከ ከሴትም ተወለደ፡፡ /ገላ.4፡4/ /ቅዱስ ጳውሎስ/
2. ሙሴም ለአባቶች ጌታ አምላክ እኔን እንደ አስነሣኝ ነቢይን
ከወንድሞቻችሁ፤ ያስነሣላችኋል፣ በሚነገራችሁ ሁሉ እርሱን
ስሙት ያንም ነቢይ የማትሰማ ነፍስ ሁሉ ተለይታ ትጠፋለች /
የሐዋ.3፡22/ ቅዱስ ጴጥሮስ፡፡
3. የዳዊት ልጅ የአብርሃም ልጅ የኢየሱስ ክርሰቶስ ትውልድ
መጽሐፍ /ማቴ.1፡1/ /ቅዱስ ማቴዎስ ገላ 3፡8-18/ ቅዱስ
ጳውሎስ፡፡
4. የንጋት ኮከብ እኔ ነኝ /ራእ. 22፡16/ ቅዱስ ዮሐንስ፡፡
5. /ማቴ.1፡18/ /ፊልጵ. 3፡18/ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር
ከሆነ ማን ይቃወመናል /ሮሜ.8፡38/ ቅዱስ ጳውሎስ፡፡
6. እርሱ ታላቅ ነው የልዑልም ልጅ ይባላል፡፡ ጌታ አምላክም
የአባቱን የዳዊት ዙፋን ይሰጠዋል /ሉቃ.1፡32/ ቅዱስ
ገብርኤል፡፡
7. ማብራሪያ ሚክያስ የተነበየው ኢየሱስ ክርስቶስ
ስለሚወለድበት ቦታ ነው፡፡ /ማቴ. 2፡1-6፣ ዮሐ.7፡32/፣
8. ዮሐ.12፡19፣ ማቴ. 21፡6-11፡፡
6. በዓሉ መከበር የተጀመረው መቼ ነው? ቀኑስ
ምን ቀን ይውላል?
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበትን
እርግጠኛውን ዕለት ለማወቅ የአስትሮኖሚ፣ የአርኬዎሎጅና
የታሪክ ምርምር ሰዎች /ሊቃውንት/ ብዙ ጥናት አድርጓል፡፡
ዳሩ ግን በአንድ ሐሳብ ሊስማሙ ባመቻላቸው፣ የክርስቲያኑ
የቀን መቈጠሪያዎች በዚሁ ሁኔታ አንድ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡
ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ መከበር የተጀመረው ከአራተኛው
መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ እንደሆነ ታሪክ ያስረዳል፡፡ ለዚህም
በጎርጎርዮሳውያን የዘመን ለቈጣጠር የሚጠቀሙት የዓለም
ሕዝቦች የክርስቶስን ልደት እኛ ኢትዮጵያውያን ከምናከብረው
የልደት በዓል 13 ቀን ቀድመው ያከብራሉ፡፡
የሮም ቤተ ክርስቲያን የጌታችን ልደት በታኅሣሥ 25 ቀን
ታከብር እንደ ነበር ከ336ዓ.ም ጀምሮ ግልጽ ነው፡፡ ይህ ቀን
በአህዛብ ዘንድ የፀሐይ በዓል እየተባለ ይከበር ስለነበር
ክርሰቲያኖች ይኽንን የጣኦት አምልኮ ጠባይ ያለውን በዓል
ለማጥፋት ሲሉ የጌታን ልደት በዚሁ ቀን ማክበር ጀመሩ፡፡
የምሥራቅ ቤተ ክርስቲያንም
ቅድሚያ ሰጥታ የምታከብረው እ.ኤ.አ ጥር 6 ቀን የሚውለን
የኤጲፋንያ በዓል ነበር፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን የጌታን
ጥምቀቱና ልደቱን ጥር 6 ቀን ስታከብር እንደቆየች የእውቀትና
የታሪክ መድበል /ኢንሳይክሎፕዲያ/ ይገልጻል፡፡
7. ቤተ ክርስቲያን አንዲት ስትሆን በክርስቲያን
ዓለም ውስጥ እንዲህ ያለ ልዩነት እንዴት
ሊፈጠር ቻለ?
በመሠረቱ ዓለም ከመለያየት በስተቀር አንድ ለመሆን
ያሰበበት ወቅት ምን ጊዜ የለም፡፡ (በታሪክ እንደምንረዳው)
ልዩነቱ እንዴት እንደሆነ እንመልከት
ከጌታ ልደት አስቀድሞ /በፊት/ በ46ዓ.ዓ ጁሊዮስ የተባለው
የሮማ ቄሣር በጊዜው የከዋክብት መርማሪ የነበረው
ሶስግነስን አስጠርቶ ተመሰቃቅሎ የነበረውን የዘመናት
አቈጣጠር እንዲያስተካክል አዘዘው፡፡ ይኸም፣ ሊቅ ፈቃደኛ
ሆኖ ዓመቱንም በ12 ወሮች ከፋፍሎ እያንዳንዱን ወር
ከየካቲት በስተቀር በማፈራረቅ 31 እና 30 ቀናት
እንዲኖራቸው አድርጎ አዘጋጀ፡፡ የካቲት ወር ግን 29 ቀን
እንዲኖረው አደረገ፡፡ ነገር ግን በየአራቱ ዓመቱ አንድ ቀን ትርፍ
ስለሚመጣ በአራተኛው ዓመት የካቲት 30 ቀን እንዲሆን
ወሰነ፡፡ ጁሊየስ ቄሣርም የሮማው ሕዝብ በዚሁ እንዲገለገል
አዋጅ አወጀ፡፡
በተጨማሪም ጁሊየስ የዓመት መለወጫ መጋቢት የነበረውን
ለውጦ /አዛውሮ/ ጥር እንዲሆን አደረገ፡፡ በዚሁም
የጁሊየስን የዘመን አቈጣጠር ብዙ ሀገሮች ለ1500 ዓመታት
ያህል ሲገለገሉበት ቈይተዋል፡፡ ምክንያቱም የዓመቱ ቀናት
ተቀምረው 365 ቀን ከሩብ ሊሆን መቻላቸው ነበር፡፡ ይህም
ሆኖ የጁሊየስ አቈጣጠር ህጸጽ አልታጣበትም ምክንያቱም
11 ደቂቃ ከ14 ሰኮንድ ትርፍ ያሳይ ነበርና፡፡
ከዚህም የተነሳ እ.ኤ.አ በ1582ዓ.ም የነበረው የሮማው
ፖፖ ጎርጎርዮስ /ስምንተኛ/ የከዋክብትን ሊቃውንት ሰብስቦ
ከተመካከረበት በኋላ የዘመኑ አቈጣጠር ተሻሽሎ
እንዲሰራበት አዋጅ አስተላለፈ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሮማ
ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በጎርጎርዮስ የዘመን አቈጣጠር
መቈጠር ጀመረች፡፡ በእምነት ተከታዮቻቸው የሆኑትም
አገሮች ተቀብለው ወድያውኑ በሥራ ላይ ሲያውሉት የጀርመን
ግዛቶች ግን እስከ 17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ በጁሊዮስ
አቈጣጠር ይጠቀሙ ነበር፡፡ እንግሊዝም ብትሆን አዋጁን
የተቀበለችው በ1752ኛ.ም እ.ኤ.አ ነው፡፡ ከዚያ ወዲህ ግን
ምዕራባውያን አገሮች ተቀብለውታል፡፡
ይህም ሊሆን የቻለው በ1582ዓ.ም የተጨመሩት 10 ቀናት
ተጠራቅመው ጎርጎርዮስና ጁሊዮስ በተባለው የዘመን
አቈጣጠር መኻከል ልዩነት ስለፈጠሩ ነው፡፡
በዘመን አቈጣጠር ልዩነት የተነሣ የምዕራባውያንና
ኢትዮጵያውያን የልደት በዓልን በማክበር በ13 ቀናት
ይለያያሉ፡፡ ይሁን እንጂ በመጀመሪያው እንደተናገርኩት ዓለም
ብዙ ጊዜ ስለ ዘመን አቈጣጠር ችግር ገጥሟት እንደ ነበረ
ግልጽ ቢሆንም ኢትዮጵያ ግን በዘመነ ኦሪትም ሆነ በዘመነ
ሐዲስ እንደ ንጋት ኮከብ የሚያበሩ ልጆች ስለነበሯት በቊጥር
ግራ አልተጋባችም፡፡ ቀድሞም ዛሬም ባህልዋንና ቀመርዋን
እንደያዘች ትገኛለች፡፡
ስለዚህ የኢትዮጵያ አቈጣጠር ደግሞ እንደሚከተለው
እንመልከት፤
8. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ
ቤተክርስቲያን አቈጣጠር
በዘመናችን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
የጌታ ልደት ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት እንደሚያከብሩት
ለምን አታከብርም? የሚል ጥያቄ በየአቅጣጫው ከተሰማ
ውሎ አድሯል፡፡ አንድ ነገር መታወቅ ያለበት ግን የኢትዮጵያ
ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በዓለ ልደትን 29 ቀን
የምታከብረው ብቻዋን ሳትሆን ከእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን
ጋር በመሆኑ ነው፡፡
በቀን አከባበር ስለተፈጠረው መለያየት ምክንያቱንና የነገሩን
ምንጭ ከእነማስረጃው አትቶ "በእንተ ልደት ድንግልናዌ"
በሚል ርዕስ የእስክንድርያው ሊቅ ዮሐንስ አቤል ሄረም ጽፎት
ይገኛልና ከዚያ መመልከት ይጠቅማል /አንቀጽ 84/ ዓይነተኛ
ጉዳዩ ግን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
በመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃነት የተመሠረተ ነው ብላ
ስለአመነችበት እንጂ ብዙ ዘመናት ሲሠራበት በመቈየቱ
ወይም ደግሞ የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ስለምታከብረው
ብቻ አይደለም፡፡
በቅዱሳት መጻሕፍት ስለ አለው ማስረጃ እንደሚከተለው
እንረዳለን፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ የተጸነሰበትም ቀን ጌታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ በድንግል ማኅፀን ለተጸነሰበትና
ለተወለደበት ቀን መነሻ ሆኖ የሚገኝበት አለ፡፡ ይኸንም
ለመረዳት ወንጌላዊ ሉቃስ የጻፈውን እንመልከት፡፡ በይሁዳ
ንጉሥ በሄሮድስ ዘመን ከአብያ ክፍል የሆነ ዘካርያስ የሚባል
አንድ ካህን ነበረ፡፡ ሚስቱም ከአሮን ልጆች ነበረች፡፡ ስምዋም
ኤልሳቤጥ ነበረ፡፡ ሁለቱም በጌታ ትእዛዝና ሕግጋት ሁሉ
ያለነቀፉ እየሄዱ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ፡፡
ኤልሳቤጥም መካን ነበረችና ልጅ አልነበራቸውም፣ ሁለቱም
በዕድሜያቸው አርጅተው ነበር፡፡ እርሱም በክፍሉ ተራ
በእግዚአብሔ ፊት ሲያገለግል፣ እንደ ካህናት ሥርዓት ወደ
ጌታ ቤተ መቅደስ ገብቶ ለማጠን ዕጣ ደረሰበት፡፡ በዕጣንም
ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ በውጭ ቁመው ይጸልዩ ነበር፡፡ የጌታም
መልአክ በዕጣኑም መሠዊያ ቀኝ ቆሞ ታየው፡፡ ዘካርያስም
ባየው ጊዜ ደነገጠ፣ ፍርሃትም ወደቀበት፡፡ መልአኩም እንዲህ
አለው፡፡ ዘካርያስ ሆይ ጸሎትህ ተሰምቶልሃልና አትፍራ፣
ሚስትህ ኤልሳቤጥም ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፣ ስሙንም
ዮሐንስ ትለዋለህ ደስታና ተድላም ይሆንልሃል፣ በመወለዱም
ብዙዎች ደስ ይላቸዋል፡፡ በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናልና /ሉቃ.1፡
5-15/፡፡
ወንጌላዊ ከተረከው የተገኘ ቅርጸ ሐሳብ የቱ ነው? ተብሎ
ቢጠየቅ ትክክለኛ ጥያቄ ሆኖ ይገኛል፡፡ ፍሬ ሐሳቡ መልአኩ
ገብርኤል ለዘካርያስ ስለመጥምቁ ዮሐንስ መወለድ
ያበሠረበት ጊዜ መቼ ነው? የሚለው ነው፡፡ ይኸ በዕብራውያን
ዘንድ በዓለ አስተሥርዮ ተብሎ ይከበር የነበረው ቀን መሆኑ
ነው፡፡ በዓለ ሥርየትም ሲባል ደግሞ በዕብራውያን አቈጣጠር
በሰባተኛው ወር ማለት /ጥቅምት አሥር ቀን የሚውል ታላቅ
በዓል ነው/ /ዘሌ.16፡29-34/፡፡ /ዘኊ.29፡7-11/፡፡
እነሆ ዘካርያስ ወደ ቤተ መቅደስ በገባ ጊዜ መልአኩ
ያበሠረው በዚህ ጊዜ ነው፡፡ /ሉቃ. 1፡8-10፡21/፡፡ ይህ
ዘካርያስ የተበሠረበት ቀን በአይሁድ በዓለ ሥርየት የዋለበት
በዕብራውያን የዘመን አቈጣጠር ጥቅምት 10 ቀን ለመሆኑ
ከጥንት አባቶች ዮሐንስ አፈወርቅ ማር.ዮሐንስ መስክረዋል፡፡
አሁንም ደግሞ ይህ ቀን ከኢትዮጵያ የቀን አቈጣጠር ያለው
ተዛምዶ እንደሚከተለው ነው፡፡ መጀመሪያ ነገር በባሕረ ሐሳቡ
የአቈጣጠር ሕግ እንደሚታወቀው ሁሉ 5500ዓመተ ዓለምን
በዐቢይ ቀመር፣ በንዑስ ቀመር፣ በማዕከላዊ ቀመር ተተንትኖ
ተከፋፍሎ ውጤቱ የ5500 ዓመተ ዓለም ተረፈ ቀመር 9 ሆኖ
ስለሚገኝ አንድን ለዘመን አትቶ መንበሩ 8 ይሆናል፡፡
8x11=88-60=28 አበቅቴው 28 ካለፈው የተያዘ 11
የጨረቃ እና ዕለቱ 28 አበቅቴ ሲደመር ሠረቀ ሌሊቱ፣ 10
ሆኖ መጥቅዑም 2 ይሆናል፡፡ በሠረቀ ሌሊቱ 10+4=14
ጨረቃ ሆነ፡፡
እንግዲህ 14 የጨረቃ ሌሊት ይዘን እስከ መስከረም 16 ቀን
ብንሄድ በዚያን ጊዜ የጨረቃ ብርሃን 29 መሆኑን ያሳየናል፡፡
መስከረም 18 ቀን ደግሞ የጨረቃ ብርሃናዊ ልደት ነው፡፡
የአይሁድ የቀዳማዊ ወርኅ ታሥሪን /መባቻ/ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ፀሐያዊ አቈጣጠር መስከረም ስለ አላለቀ እንዲህ
እያልን እሰከ መስከረም 27 ቀን እንሄዳለን፡፡ በዕብራውያን
ጥቅምት 10 ቀን ሲሆን በእኛ ደግሞ መስከረም 27 እንደነበረ
እንረዳለን፡፡
በዚሁ ዘካርያስ ልጅ እንደሚወልድ ተበሠረ፡፡ ዘካርያስም ይህን
አገልግሎት ከፈጸመ በኋላ ከበዓለ ሥርየት በኋላ እስከ
15ኛው የጥቅምት ጨረቃ በዓል ስለአልነበረ ወደ ቤቱ ገባ
መጥምቁ ዮሐንስ ተጸነሰ፡፡ ይህም ሊቁ ኢትዮጵያዊው ቅዱስ
ያሬድ ከሁለት ቀንም በኋላ ኤልሳቤጥ ጸነሰች፡፡ በማለት
አስረድቶናል፡፡ አቡን /ብርሃነ ሕይወት/ ድጓ የታኅሣሥ
ገብርኤል/ ቅዱስ ያሬድ ከሁለት ቀን በኋላ ኤልሳቤጥ ጸነሰች
ያለው ቀንና ዘካርያስ ልጅ እንደሚወልድ እስከ ተበሠረበት
ድረስ ያለው ቀን ብንደምረው ከመስከረም ይዘነው የመጣን
27 ቀን፣ የክህነት አገልግሎቱን ፈጽሞ ወደ ቤቱ እስከ
ተመለሰበት ድረስ ያለው ጊዜ 3 ቀን፣ 27+3=30 ቀናት
ይሰጠናል፡፡
ሐዋርያው ሉቃስ ወደ ጻፈው ቃል እንመለስ
መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ኤልሳቤጥ ከጸነሰች በስድስተኛው
ወር ወደ ቅድስት ድንግል ማርያም መላኩ፣ እና ቅዱስ
ሉቃስም ዮሐንስ ከተጸነሰ በኋላ ኢየሱስ ክርስቶስም
በስድስተኛው ወሩ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ
ሥጋን፣ ከነፍስዋ ነፍስን ነሥቶ ሰው የሆነበት ዕለት፣
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የትርጓሜና
የቊጥር መምህራን በማያሻማ መልኩ ተንትነው ቀምረው
ለዚህ ትውልድ ማድረሳቸው እግዚአብሔር ከእነሱ ጋር እንደ
ነበር ቋሚ ማስረጃ ነው፡፡
እንግዲህ የዮሐንስ ትንቢታዊ መጸነስ ክርስቶስ ሰው
ለሚሆንበት ቀን የዕለታት ፋናው እያበራ ክርስቶስ ተጸንሶ
እስከ ተወለደበት ዕለት ያደርሰናል፡፡
9. ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መጋቢት 29 ቀን
ተጸንሶ ታኅሣሥ 29 ቀን ስለመወለዱ፤
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መቼ ተጸንሶ መቼ እንደተወለደ
ለማወቅና ለመረዳት ሐዋርያው ሉቃስ ወደተለመልን የአኀዝ
ቊጥር እንመለሳለን፡፡ እነሆም በስድስተኛው ወር መልአኩ
ገብርኤል በናዝሬት ወደም ትኖር ወደ ድንግል ማርያም ተልኮ
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደምትጸንስና እንደምትወልድ
ነገራት /ሉቃስ. 1፡26-38/ ይህም ቀን በኢትዮጵያ
አቈጣጠር መጥምቁ ዮሐንስ ከተጸነሰበት ዕለት ጀምሮ
ተቈጥሮ መጋቢት 29 ቀን መሆኑ እንገነዘባለን፡፡
ለምሳሌ ጥቅምት፣ ኅዳር ታኅሣሥ፣ ጥር፣ የካቲት፣ መጋቢት
ድምር 6 ወር ነው፡፡
ስለዚህ መጋቢት 29 ቀን ቃል /ቃለ እግዚአብሔር ወልድ/
ሰው ሥጋ የሆነበት፤ በድንግል ማኅፀን ያደረበት፤ በዓለ
ትስብእት ነው፡፡ አሁን /ሰው የመሆኑ/ ሰው የሆነበት ቀን
ከተረዳን፤ የተወለደበት ቀንና ወር ለማረጋገጥ ከመጋቢት 29
ቀን እስከ ታኅሣሥ 28 ቀን ጳጒሜን ጨምሮ ያለው ጊዜ 275
ቀናት ይሆናሉ፡፡
ይህም 275 ለ30 ሲካፈል 9 ወር ከአምስት ቀን ይሆናል፡፡
ይህም ማለት ከመጋቢት 2 ቀን፣ ከሚያዝያ እስከ ኅዳር
መጨረሻ ወር ያሉት ወራት (8x30=240) ቀናት፣ 5 ቀናት
የጳጒሜን፣ 28 ቀን ከታኅሣሥ፤ አጠቃላይ ድምር 275 ቀናት
ናቸው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከርሠ ድንግል 9 ወር
ከአምስት ቀን ከቈየ በኋላ በዕለተ ሠሉስ ታኅሣሥ 29 ቀን
በ1ዓ.ም ከሌሊቱ 7 ሰዓት እስከ 10 ሰዓት ባለው ጊዜ
በቤተልሔም ተወለደ፡፡ /ጊዮርጊስ ወልደ አሚድ ገጽ 158 እና
159/፡፡
ይህም በሒሳባዊ መንገድ የሚደረስበት ስለሆነ
አያጠራጥርም፡፡ ሕጋዊ የሆነ የወንድ ልጅ በእናቱ ማኅፀን
ተጸንሶ እስከሚወለድበት ጊዜ ድረስ የሚቈይባቸው ቀናት
ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ለመሆኑ ከብዙ ዘመናት ጀምሮ
ታምኖበት የቈየ ነው፡፡ አንዳንድ የቀናት መብዛትና ማነስ
የሚታየው ህጸጽ አይነካውም /ኢሳ.7፡14፣ ገላ. 4፡4/፡፡
እነሆ ምሥራቃዊ ኮከብ ሰብአ ሰገልን የተወለደው ሕፃን እስከ
አለበት ቦታ እየመራ እንዳደረሳቸው ሁሉ ወንጌላዊው
ሉቃስም እያነጣጠረ ያመለከተው ዘካርያስ የተበሠረበት
ኮከባዊ ቀንም ፋናውን እየተቈጣጠረች ለምትከታተል
ኢትዮጵያዊት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሕፃኑ
ኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ተወለደበት እንዳደረሳት ታምናለች፡፡
ስለዚህ ኢትዮጵያዊት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
የጌታን ልደት ታኅሣሥ 29 ቀን በታላቅ ምሥጋና
ታከብረዋለች፡፡ /ማቴ. 2፡1-11፣ 2ጴጥ.1፡19-21/፡፡
ከኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጋር በዓለ ልደትን የሚያከብሩ
አገሮች ወይም አብያተ ክርስቲያን፣ ግብጽ፣ ሶርያ፣ ህንድ፣
ኢትዮጵያ፣ አርመን ሲሆኑ ከሩቅ ምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት
ደግሞ የግሪክ ኦርቶዶክስ የሩሲያ ቤተ ክርስቲያን ናቸው፡፡
አውሮፓውያን በዓለ ልደትን የሚያከብሩት ከእኛ 13 ቀናት
ቀደም ብለው ነው፡፡ ይህም ማለት በእኛ አቈጣጠር ታኅሣሥ
16 ቀን ነው እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቈጣጠር
December 25 ቀን ነው፡፡ ልዩነቱ ለማወቅ የኢትዮጵያ ቤተ
ክርስቲያን በዓለ ልደትን የምታከብረው ታኅሣሥ 29 ቀን ነው
ይህም ማለት ከ29-16=13 ቀናት ወይም 16+13=29
ቀን ይሆናል፡፡ ይህ ቁጥር የሚያሳየን አውሮፓውያን ከእኛ
በ13 ቀናት ቀድመው በዓለ ልደትን ሲያከብሩ ኢትዮጵያውያን
ግን ከ13 ቀናት በኋላ ቈይተው ታኅሣሥ 29 ቀን በዓለ
ልደትን ያከብራሉ፡፡
10. ጌታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ታኅሣሥ 29 ቀን
ለመወለዱ የመሰከሩ ሊቃውንት
1. ማሪ.ኤፍሬም ሶርያዊ
2. ሰዒ.ድ ወ/በጥሪቅ
3. መበንጋዊ/ማኅቡብ
4. ጊዮርጊስ ወልደ አሚድ
5. ወልደ መነኮስ
6. በዲድስቅልያ አንቀጽ 29 ገጽ 37
7. የኢትዮጵያ መምህራን ሁሉ ናቸው
11. የልደት በዓል አከባበር በኢትዮጵያ ከሕዝቡ
ጋር ያለው ግንኙነት
በኢትዮጵያ የገና /የበዓል ልደት አከባበር/ ገና በዋዜማው
ጀምሮ የአከባበሩ ሥርዓት ይጀመራል፡፡ ከቀኑ 7 ሰዓት ጀምሮ
በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት "ዋዜማ እምርኅቅ ብሔር
በማለት ዋዜማ ይቈማል፡፡ ይትባረክ ኮከብ መርሖሙ" ሰላም
"ይእዜኒንትልዋ ለሰላም" ምስባክ ይሰበካል፣ ወንጌል
ይነበባል በመጨረሻም "አድኅነነ ሕዝበከ" ተብሎ የዋዜማ
ፍጻሜ ይሆናል፡፡ ከምሽቱ 2 ሰዓት ሲሆን የጌታን መወለድ
የምሥራች የሚያበሥሩ የአብያተ ክርስቲያናት ደወሎች ለ5
ደቂቃ ድምጻቸውን ያስተጋባሉ፡፡ ካህኑም ሆነ ሕዝቡ /ከልሂቅ
እስከ ደቂቅ/ ነጭ የባህል ልብሳቸውን እየለበሱ ወደ ቤተ
ክርስቲያን ይመጣሉ፡፡ ከዚያም ካህናቱም ሕዝቡም
በማኅሌት፣ በጸናጽል በከበሮ "ዮም ተወልደ ቤዛ ኲሉ ዓለም"
እያሉ በኅብረት እየዘመሩ እስከ ቅዳሴ ይቈያሉ፡፡ ቅዳሴ
ተቀድሶ ሠርሆተ ሕዝብ የቅዳሴ ፍጻሜ ከሆነ በኋላ በ9 ሰዓት
ወደየቤታቸው ይሄዳሉ፡፡
ከነጋም በኋላ ዘመድ ከመጠየቅ አስቀድመው በአካባቢው ያሉ
ድሆች ጠርተው በአንድ ላይ ዘመድም ሆነ ድሃው ሁሉ በአንድ
ላይ በቤት የተገኘውን አብረው ይቀምሳሉ፡፡ ስጦታም
ይለዋወጣሉ፡፡ ቤታቸውንም ቀጤማ ፊላ በመጐዝጐዝ፣ አበባ
በማዘጋጀት ያሳምሩታል፡፡ የሚበላውም የሚጠጣውም
በሰፊው ይቀርባል፡፡ ማለት ዳቦ በመጋገር፣ ጠላ በመጥመቅ፣
ጠጅ በመጣል፣ በግ፣ ደሮ በማረድ ሰንጋውን በመቈረጥ
በዓሉን ያከብራሉ፡፡ የልደት ዕለት መሶቡ ሁሉ ሳይቀር በተለይ
በከተማ አካባቢ አጊጦ ይውላል፡፡
ስለዚህ "ልደትሶ በኲሉ ልደት ጸውአኒ በካልዕ ዕለት"
ተብሏል፡፡ የሀገሬው ሰውም እሰይ ጌታ ተወለደ ዲያብሎስ
ልቡ ነደደ እያሉ መንፈሳዊ ስሜታቸውን ይገልጻሉ፡፡
12. እረኞችና ባህላቸው
እረኞቹ በዚሁ ዕለት በቡድን በቡድን ሆነው ገናን ይጫወታሉ፡፡
ብትራቸውን እየሸለሙ በማቈራቈስ ደስታቸውን ይገልጻሉ፡፡
ይህ የሚደረገው "ዮም መላእክት ወሰብእ አሐደ መርዓተ
ኮኑ" ዛሬ ሰውና መላእክት አንድ ሆነዋል ከሚለው በማያያዝ
ነው፡፡ ሉቃስ 2፡15፡፡
ብትሩም ሸልምልም መሆኑ በያዕቆብ ብትር ምሳሌ ነው፡፡
ያዕቆብ ልብን ለውዝ ኤርሞን ከሚባሉት እንጨቶች እርጥብ
በትርን ወስዶ በበትሮቹ ውስጥ ያለው ነጭ እንዲታይ ነጭ
ሽመልመሌ አድርጎ ጣላቸው፡፡
የጣላቸውንም በትሮች በጐቹ ውኃ ሊጠጡ በመጡ ጊዜ
በውኃ ማጠጫው ገንዳ ውስጥ በጎቹ ፊት አኖራቸው፡፡ በጎቹ
ውኃ ሊጠጡ በመጡ ጊዜ ይጎመጁ ነበር፡፡ በጎቹም በትሮቹን
አይተው ከመጎምጀታቸው የተነሣ ፀነሱ፣ በጎቹም ሽመልመሌ
መሳይና ዝንጉርጉር ነቁጣም ያለበትን ወለዱ /ዘፍ. 29፡
37-40/
ያዕቆብ የራሱ የሆነው ጥሪት ንብረት ለመለየት ሲል መልአኩ
በሕልም በነገረው መሠረት በመታዘዙ የእግዚአብሔር በረከት
አገኘ፡፡ በጎቹም በዙለት፡፡ ያ ባህል ያ ልምድ በእረኞቻችን
የሚፈጸመው ከጥንት ተያይዞ የመጣ ነው፡፡ ይኸም ሁሉ
የፍቅር ምልክት ነው፡፡ እረኞችና መላእክት አብሮ መዋላቸው
ሰውና እግዚአብሔር የታረቁ መሆኑን የሚያስረዳ ነው፡፡
"ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር
ብለው አብረው አመስግነዋልና እንግዲህ የልደት
አከባበር በኢትዮጵያ ይህን የመሰለ ነው"
"ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን"

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

አይሰው

እቴጌ ጣይቱ ብጡል (ብርሀን ዘ ኢትዮጵያ)