ድንጋይ እንዴት ስድብ ይሆናል?

ጤና ይስጥልኝ
#ድንጋይ_እንዴት_ስድብ_ይሆናል?



ከሰሜን እስከ ደቡብ ያለውን የኢትዮጵያውያንን አንድነትስ ቢሆን ከድንጋይ በተሻለ ማን ይመሰክረዋል፡፡ አንድ ሰው እንዳ ለው «እስክስታ እና ድንጋይን ያህል የኢትዮጵያን ሕዝቦች አንድነት የሚያሳይ ባሕላዊ ገጽታ የለም»፡፡ ትግራይ ላይ ከወደ አንገት እና ትከሻ የጀመረው እስክስታ፣ አገው እና አማራ ላይ ሲደርስ አንገትን ከትከሻ ያያይዝና፤ ኦሮሚያ ላይ አንገትን ፣ ትከሻን እና ወገብን ከእጅ እንቅስቃሴ ጋር ያዛምዳል፡፡ ወላይታ እና ሐድያ ላይ ሲወርድ ደግሞ ወገብን ታክኮ ወደ ዳሌ ዝቅ ይላል፡፡ ከዚያም ደቡብ ጫፍ ሐመሮች ላይ ሲገባ እስክስታው በእግር ይጨርሳል፡፡ ያኔም ኢትዮጵያ አንድ ሰው ሆና ትታያለች ማለት ነው፡
ድንጋይም እንዲሁ ነው፡፡ ከሰሜን አኩስም እስከ ባሌ ተራሮች፣ ከምዕራብ ኦጋዴን እስከ አሶሳ፣ ኢትዮጵያ በታሪካዊ የድንጋይ ሐውልቶች የተሞላች ናት፡፡ በጣም የሚገርመው ደግሞ እነዚህ የድንጋይ ሐውልቶች ከመቃብር እና ከታሪካዊ ሁነቶች ጋር የተያያዙ መሆናቸው ነው፡፡ 
የአኩስም ሐውልት በታላላቅ የአኩስም ነገሥታት መቃብር ላይ መታሰቢያ ሆኖ ቆሟል፡፡ ከአዲስ አበባ ደቡብ 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ጀምሮ በሲዳማ፣ ወላይታ፣ ሐድያ፣ ስልጤ፣ ከምባታ፣ በሰሜን በአዋሳ ሐይቅ፣ በምዕራብ ደግሞ በአባያ ሐይቅ ተከብቦ የሚገኘውና ከ150 በላይ ታሪካዊ ሥፍራዎችን የያዘው የድንጋይ ሐውልቶች ስብስብ፣ እንደ ሰሜኑ ሁሉ የመቃብር ሥፍራዎችን እና ታሪካዊ ሁነቶችን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ በኦሮሚያ ክልል በተለይም በአርሲ እና ባሌ የምናገኛቸው ሐውልቶችም ይህንኑ የሰሜን እና ደቡብ እሴት ተጋርተው፣ አንድነታችንንም መስክረው ይሄው ዛሬም ይታያሉ
ድንጋይ ሥልጣኔያችንን ብቻ ሳይሆን ጀግንነታችንንም ሲመሰክር የኖረ ነው፡፡ መሣርያ እንደ ልብ ባልነበረበት በዚያ ዘመን ሉዓላዊነታችን ታፍሮ፣ ድንበራችን ተከብሮ፣ የኖረው በድንጋይ ጭምር ነው፡፡ ቆንጥር ለቆንጥር መወርወር፣ ተራራ ለተራራ መኖር የለመደው ሐበሻ በተራሮች ጫፍ መሽጎ ይለቅቀው በነበረው ናዳ ያለቀውን ጠላት ያህል ሌላው መሣርያችን መጨረሱን እጠራጠራለሁ፡፡ ከሜዳማ አካባቢዎች ይመጡ የነበሩት አብዛኞቹ የውጭ ጠላቶች ከመሣርያችን በላይ መቋቋም ያቃታቸው ለሀገሩ ልጅ ብቻ ይበገር የነበረውን መልክዐ ምድራችንን ነው፡፡ 
እናም ድንጋይ የታሪካችን፣ የፊደላችን፣ የሥልጣኔያችን፣ የእምነታችን፣ የቀጣይነታችን፣ የአንድነታችን፣ የኅብራችን መገለጫ ከሆነ «ድንጋይ» እንዴት ስድብ ይሆናል

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

አይሰው

እቴጌ ጣይቱ ብጡል (ብርሀን ዘ ኢትዮጵያ)

ደራሲ ዶ/ር ሀዲስ ዓለማየሁ (ሃዲስ ኣለማየሁ)