ነገሩ ሁሉ እንደ ጥርስ ነው መሰል እህል ያላመጠበትን የመጀመሪያ ቀን የሚያስታውስ የለም።
ነገሩ ሁሉ እንደ ጥርስ ነው መሰል
እህል ያላመጠበትን የመጀመሪያ ቀን የሚያስታውስ የለም። ለነገሩ እህል ከማላመጣችን በፊት የፈረደባትን የ'ናታችንን ጡት ነክሰናል.. በሁለት የፊት ጥርስ እና ድድ የጡት ጫፍን ቅርጭው ይዘን.. ሁሉም እናቶች እሰይ ልጄ ጥርስ አበቀለች ብለው እንዳልተደሰቱ በምስራቻቸው ተነክሰዋል... ያውም እስከሚደሙ
****************************************
ይህ የራሴ ያገለገለኝ ንብረቴ ፡ ለሆነ አመት አፌ ሲከፈት ነጫጭ ሆኖ ተደርድሮ፡ ግጥም ብሎ አፌን ሞልቶ የልጅነት ቆንጆ ሳቅ አልፈጠረልኝም?
ቆሎ ... ከቆሎም ሳይንገረገብ በደረቁ ጣ ጣ ጣ እያለ የተቆላ ሽንብራ አልከካሁበትም? መለልታ ከአንጓ ሳለይ ሸንኮራ አልመጠጥኩበትም? ይባስ ብዬ ተደብቄ እየሰረኩ ስኳር ቅሜ እየቆረጫጨምኩበት ይህ ጥርሴ እስኪቦረቦር ድረስ አንጀቴን በወለላ ጣዕም አላራስኩበትም?
ይህ የልጅነት ጥርሴ ለምን ከእኔ ኖሮ ፡ ከእኔ እንዳልተፈጠረ በአመታት ውስጥ ነቅነቅ አለ? ለምን መነቃነቁ አሰጋኝ? ለምን ... ለምን ያ ቆሎም ቆንጥሮ ያቀበለ፡ ሸንኮራም ሸንሽኖ ያጎረሰ የገንዛ እጄ፡ የእጄ ጣቶች ከድዴ የተሰካን ጥርስ አነቃንቆ ለመንቀል ታገለ?
እኔ በ እኔ አልተጣላንም? ያውም በልጅነቴ?
ብተወዉ በስብሶ በሽታ፡ ብነቅለው - ክብር አሳጥቼ - ከቤቴም ደጃፍ አፈር ምሼ ሳልቀብረው፡ ደብቄ በትንሽ ብልቃጥ ሳላስቀምጠው... ይባስ ብዬ ወደ ጣርያ፡ ያውም አሻግሬ ለወፍ እና ለአይጥ ዘምሬ 'ያንቺን ለኔ የኔን ላንቺ' እያልኩ መወርወሬ.. ተሻግሮ ወይ በእኛ ቤት፡ ወይ በእነ አሹ ቤት ጣሪያ ቋ ብሎ መውደቁን፡ መጣሉን ሲያረጋግጥልኝ፡ አልያም አጥር ዘሎ በጎረቤት ተክል ወድቆ ፀ...ጥ።
በመዳፌ አስቀምጬ ቢያሻኝ በሰው መሀል ጮክ ብዬ፡ ወይ በኔና በጥርሴ መሀል በሽኩሹክታ 'አመሰግናለሁ' ብዬ አልተሰነባበትንም! ... ው ር ው ር !
እንደ ቀላል የራስን ባለውለታ ጠላት አርጎ ማየት ፡ ከዳተኝነትን፡ ልጅነቴ አውቃለች።
*******************************************
እንዳላገለገለን፡ እንዳላኗኗረን፡ የማይጠረቃው ሆዳችንን ጥያቄ እየከካ የሚመልሰው፡... የጡረታ ጊዜው ሲደርስ ክብር ያጣው
ነገሩ ሁሉ እንደ ጥርስ ይመስላል
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ