Ethiopia
ብዙ ዐዋቂዎች በጥቂት ታዋቂዎች በተዋጡባት ምድር ላይ እኖራለሁ፡፡ ብዙ ገንዘብ አልባ የአይምሮ ሐብታሞች በጥቂት የፈረንካ ባለጠጋ መሐይማን በተጋረዱባት ፕላኔት ላይ እገኛለሁ፡፡ ብዕር የጨበጡ፣ መጽሐፍ ያነገቡ ዐዋቂዎች፣ ብረት ባነገቡ፣ ሳንጃ በወደሩ ታዋቂዎች በተደፈጠጡባት ዓለም ላይ እዋኛለሁ፡፡
አደባባዩ በታዋቂዎች ግሪሳ ካፍ እስከገደፉ ተሞልቷል፡፡ ታዋቂዎች ሲያስነጥሱ እልፍኝ አላዋቂዎች “እግዚሐር ይማራችሁ!” ለማለት ወረፋ ይይዛሉ፡፡ ዐዋቂዎች ቢያልፉ ግን ቀባሪ እንኳ የላቸውም፤ የታዋቂዎች የቀትር ጥላ ጋርዷቸዋልና፡፡
መቅረዞቹ ጋን ተደፍቶባቸዋልና ብርሃናቸው ከጋናቸው ሊወጣ አልቻለም፡፡ ዐዋቂዎች ከጋናቸው ከወጡ ጥላቸው በታዋቂዎች ላይ ያርፍና ታዋቂዎችን ይጋርዳቸዋልና፡፡ ታዋቂነት ነግሦ ዐዋቂነት ተዋርዷል፡፡
አንድ ዐዋቂና ሌላ ታዋቂ ከአደባባይ ቢገኙ፤ ብዕርና ደብተር ለታዋቂው ይጎርፉለታል፤ ፊርማውን እንዲያኖርበት፡፡ጥበበኛም ይህን በማየት ሌላ ጥበብ ሌላ ዕውቀት ይጨምራል፣ እንዲህም ሲል ይቀኛል፣ “አላዋቂዎች የታዋቂዎችን ፊርማ ለምን ይሰበስባሉ?፣ ዕውቀት ሊገበዩበት ነው? . . . አይደለም፡፡ ጥበብ ሊገዙበት ነው? . . . አይደለም፡፡ ማስተዋል ሊያተርፉበት ነው? . . . አይደለም፡፡ አላዋቂዎች የታዋቂዎችን ፊርማ የሚሰበስቡት ታዋቂውን ለማወቃቸው በቂ መረጃ እንዲሆናቸው ነው፡፡ ዐላዋቂዎች ከዐዋቂዎች ዕውቀትን ባለመቅሰም ብቻ ሳይሆን፣ ታዋቂዎችንም በማወቅ ታዋቂ መሆን ይፈልጋሉ፡፡
የዚህች ምድር ክበብ በታዋቂዎች ሳይሆን በዐዋቂዎች ተመሥርቷል፡፡ የሚያሳዝነው ግን ዓለምን ዐዋቂዎች ሳይሆኑ ታዋቂዎች ይነዷታል፡፡ በዚህች ዓለም ላይ ከአንድ መሪ ነኝ እመራለሁ ባይ ታዋቂነት እንጂ ዕውቀት አይፈለግበትም፡፡ ቲፎዞ እንጂ ማስተዋል አይጠየቅበትም፡፡ እንዲያማ ባይሆን ኖሮ መሪዎች ከአደባባይ ሳይሆን ከጓዳ ይፈለጉ ነበርና፤ ካደባባይ መዋል ያዋቂዎች ጠባይ አይደለምና፡፡ ዐዋቂዎችና በትረ መንግሥት ሰኔና ሰኞ ሆነዋል፡፡
ዐዋቂዎች ብዙ አድምጠው ጥቂት ይተነፍሳሉ፤ ጥቂቷም እስትንፋሳቸው ዓለምን ጋት ያህል ያንፏቅቃታል፤ . . . ወደ ከፍታዋ፡፡ ሆኖም ዓለም እስከ አሁን ድረስ በሮቿን ለዐዋቂዎቹ ከርችማባቸዋለች፡፡ ቆልፋባቸዋለች፡፡ ስለዚህም ጦርነት፣ ረሃብ፣ እርዛት፣ በሽታ፣ ስደት፣ ስርቆት፣ ስስት፣ ዝሙት፣ ማዳላት፣ ስንፍና ድንቁርና ከልፍኟ ከትመዋል፡፡ በትረ ሥልጣኑ በታዋቂዎች እጅ ነውና፣ ባምላክ አምሳል የተበጁ ነፍሳት በታዋቂዎች አፈሙዝ ምላጭ ሥር ናት
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ