ፀሎት

 እንድንፀልይ የፈቀደልን አምላክ የተመሰገነ

ይሁን!

ሰው ወደ እግዚአብሔር መቅረብና መነጋገር

የሚችልበት የመጀመሪያ መንፈሳዊ መንገድ ጸሎት

ነው፡፡

ጸሎት እግዚአብሔር እና ሰዎች የሚገናኙበት ድልድይ

ነው፡፡ ያዕቆብ በፍኖተ ሎዛ እንዳየው መሰላል ከሰማይ

እስከምድር የሚደርስ መወጣጫ ነው፡፡

ጸሎት ከውስጥ የሚመነጭ የልብ መቃተት ስለሆነ

ቃላት ብቻ ሊገልፁት አቅም የላቸውም። በተመስጦ

ልብ፣ በመንፈሳዊ ሀሳብ፣ በተሰቀለ ሕሊና ወደ

አምላካችን የምንነጠቅበትና ከፈጣሪያችን ጋር

የምንነጋገርበት ስለሆነ ጸሎት ከቃላትም በላይ ነው፡፡

በዝምታ እያለን በህሊና ልንመሰጥ እንችላለን፡፡ ጸሎት

እግዚአብሔር የናፈቀ ልብ ሲቃ ነውና ለእግዚአብሔር

ያለን ፍቅር ይለካበታል፡፡ሰውና እግዚአብሔርን ማገናኘት

የሚችለው በዚህ ዓይነት ከልብ ፈንቅሎ የሚወጣ

ጸሎት ስለሆነ ከዚህ መንፈሳዊ ሕብረት ውጪ ሆኖ

የሚጮህ ጩኸት ረብ የለሽ የቃላት ጋጋታ ነው፡፡

ለጸሎት በተነሳህበት ጊዜ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት

እንደቆምክ አስብ፡፡ "ዋላ ወደ ውሃ ምንጮች

እንደሚናፍቅ አቤቱ እንዲሁ ነፍሴ ወደ አንተ

ትናፍቃለች፣ ነፍሴ ወደ ህያው አምላክ ተጠማች፡፡ መቼ

እደርሳለሁ? የአምላክንስ ፊት መቼ አያለሁ?(መዝ

41÷2)። በእውነት ዝናምን እንደምትናፍቅ ደረቅ መሬት

እግዚአብሔርን መናፈቅና መጠማት ይህ አይደለምን?

እግዚአብሔር የሚቀበለው ጸሎት በንጹህና በተሰበረ

ልብ የሚቀርበውን ብቻ ነው፡፡ "የኃጥአን መሥዋዕት

በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነው፣ የቅኖች ጸሎት ግን

በእርሱ ዘንድ የተወደደ ነው፡፡" ምሳ.15÷8) ስለዚህ

ኃጢአት የከበደው የተጨነቀ ሰው ምን ማድረግ

አለበት? "መልሰኝ እኔም እመለሳለሁ" ይበል(ኤር

31÷18)።

አንተም ዛሬ መጸለይ ያለብህ ጸሎት ይህ ነው። ከበደሌ

ፈጽሞ እጠበኝ ከኃጥያቴም አንጻኝ እኔ መተላለፌን

አውቃለሁና፡፡" (መዝ 50÷2)

ጸሎት የአንደበትን፣ የሃሳብን፣ የነፍስን መስዋዕት

ማቅረቢያ ነው፡፡ከእግዚአብሔር ጋር የተጣላ

ሊያነጋግረው ስለማይችል ጸሎት ደግሞ የመታረቂያ

መንገድ ነው፡፡ ተሰሚነት ያለው መልካም ጸሎት

ለመጸለይ ከእግዚአብሔር ጋር የቅርብ ግንኙነት

እንዲኖርህና ስለእርሱም በቂ እውቀት ለመጨበጥ

እንድትችል መጣር አለብህ፡፡ የማይጸልይ ሰው

እግዚአብሔርን አላወቀውም፡፡ የሚጸልይ ግን

ከእግዚአብሔርን ጋር መታረቅ የፈለገና የቀደመ ክፉ

ስራውን እንየታወሰው በትህትና የተሰበረ ልብ ያለው

ነው፡፡ ሰው ወደ ጤናማ ክርስቲያናዊ ሕይወት ምልክት

ወደ ትህትና ደረጃ መድረስ የሚችለው በጸሎት ነው፡፡

የጥሩ መንፈሳዊ ሕይወት ፍሬ ትሕትና ነውና፡፡

ጸሎት ክፉ ሀሳብ ከውስጣችን የሚወገድበት ነው፡፡

ከጨለማ ኃይላት ርቆ ወደ መንፈሳዊ ሕይወት መግባት

የሚቻለው በጸሎት ነው፡፡

ጸሎት አጋንት የሚፈሩትና የሚንቀጠቀጡበት መንፈሳዊ

መሳሪያ ነው፡፡ ከወጥመዱ ያመለጠ ጸሎተኛን

ዲያብሎስ ይፈራዋል፡፡ "ይህ ሰው በጸሎቱ ኃይል

እያገኘ ነው፡፡ በመንፈሳዊ ሕይወቱ እየጠነከረ ነው፡፡

ስለዚህ እኔን ሊዋጋኝ ይነሳል እያለ ይርዳል

ይንቀጠቀጣል፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር በጸሎት

የሚፈጠረውንም ጥልቅ ግንኙነት እርሱ አስቀድሞ

ያጣው ነውና ይቀናበታል ይመቀኘዋል፡፡ ስለዚህ

ዲያብሎስ በሚችለው አቅም ሁሉ ጸሎትህን ለማስተው

ይጥራል፡፡ ጊዜ እንደሌለህ፣ እንደተጣበብክ፣

እንደደከመህና፣ እረፍት እንደሚያስፈልግህ እያሳሰበ

ጸሎትህን ለማስቆም ይታገላል፡፡ በጸሎትህ የምትታመን

የምትተጋ ብትሆንበትም ከመንገድህ ለማስነሳት

ሀሳብህን ለመበተን ሰይጣን የማይፈነቅለው ድንጋይ

የለም፡፡

ጌታ ሆይ የውስጤን የሚረዳልኝ እንዳንተ ያለማንንም

አላገኝም፣ ከአንተ ጋር ስሆን ብቻ ደህንነት ስለሚሰማኝ

ለአንተ ለአምላኬ ልቤን ከፍቼ ምስጥሬን አዋይሃለሁ፡፡

ቃልህን የምሰማ ነገር ግን የማላስተውል ደካማ ነኝና፣

ናፍቆቴን ቢገልፅልኝ እንባዬን በፊትህ አፈሰዋለሁ፡፡ይህ

አይነት ጸሎት ጥያቄ ብቻ ሳይሆን በደረጃው ከፍ ያለ እና

በእግዚአብሔር ፍቅር ያደገ ነው፡፡

ታላቁ አባት ቅዱስ ባስልዮስ "ጸሎታችሁን በጥያቄ

አትጀምሩ" እንዳለው የእግዚአብሔርን ዕጹብ ድንቅ

ባህሪያት አውቀህ በተመስጦ የምትፀልይና

የምትጠቀም ሁን፡፡

"ለፀሎት ጊዜ የለኝም" ማለት እጅግ አስፀያፊና ዘግናኝ

ኃጢያት ነው፡፡ አንድ አገልጋይ(ባሪያ) "ጌታዬን

የማነጋግርበት ጊዜ የለኝም" ቢል እንዴት ያለ ድፍረት

ይሆን? ፍጡሩስ ከፈጣሪው ጋር ለመነጋገር "ጊዜ

የለኝም" ቢል ምን ይደንቅ! ዋጋ ቢስ ለሆኑ በርካታ

ነገሮች ጊዜ ታገኛለህ፡፡ ምንም ረብ ለሌላቸው ንትርኮች

ከበቂ በላይ ጊዜ አለህ። ምነው ታዲያ ከእግዚአብሔር

ጋር መነጋገር እንደጊዜ ማባከን ቆጠርከው? ነብዩ ቅዱስ

ዳዊት ከታላቅ ቤተሰብ ጋር ሕዝብን፣ አገርን የሚመራ፣

የሚያስተዳድር፣ መሪ፣ መስፍን፣ ፈራጅ ንጉስ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ዳዊትን የምንሰማው እንዲህ ሲል ነው፡፡

"ስለጽድቅህ ፍርድ ሰባት ጊዜ በቀን

አመሰግንሃለሁ" (መዝ 118÷164) ከዚህ የምንረዳው

ችግሩ የጊዜ ሳይሆን የፍላጎት እንደሆነ ነው፡፡

ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስ እንዳለው "ጸሎት ከሕመም

የመፈወሻ መንፈሳዊ መንገድ ነውና ላለመፀለይ በሽታን

እንኳን ምክንያት አታድርግ"።

ማርይስሐቅም "ንጹህ ጸሎት ለመፀለይ በጀመርክበት

ጊዜ ለሚመጣው ነገር ዝግጁ ሆነህ ጠብቅ፡፡" ይሉናል

ማለትም ከጸሎት ሊያደናቅፍህ ዲያቢሎስ

ለሚከፍትብህ ጦርነት የተዘጋጀህ ሁን ማለታቸው ነው፡፡

እግዚብሔር የለመንከውን እንደሚሰማህ፣ ይወድሃልና

መልስ እንደሚሰጥህ፣ መልካሙን ሁሉ ለአንተ

እንደሚመርጥልህ በፍፁም ልብህ እመን(ማቴ

21÷22) ይህ እምነት ባይኖርህ እንኳን "ጌታ ሆይ

አለማመኔን እርዳው" እያልክ ጸልይ (ማር 9÷24 )

ደግሞም እንደሐዋርያት እምነት እንዲጨመርልህ

ለም'ን (ሉቃ 17÷5 ) ለሚያምን ሁሉ ይቻለዋል

የሚለውን ድንቅ ቃልኪዳንም አትርሳ(ማር 9÷23)።

እምነት ለጸሎተኛው ጽናትን የሚሰጥ ታላቅ ኃይል ነው፡፡

ጸሎትም እምነት ያሳድጋል፡፡ አንድ ነገር እንዲሆንልህ

ጠይቀህ፡፡ ለምላሹ ጌታን ጠብቅ እንጂ ያን ቶሎ

ለማግኘት አትቸኩል፡፡ ምንም እግዚአብሔር የሚዘገይ

ቢመስልህም፣ የረሳህ ያህል ቢሰማህም፣ እርሱ ግን

የራሱ ጊዜ አለውና ጥያቄህን እንደሚመልስ እርግጠኛ

ሁን፡፡

ለመጸለይ የምትጠቀመው ማንኛውም ቃልና

እንቅስቃሴ በማስተዋል መሆን አለበት። ምክንያቱም

ጸሎት በቀጥታ ከእግዚአብሔር ጋር የምታደርገው

ግንኙነትና ውይይት ነው፡፡ ስለዚህ የእያንዳንዷ የፀሎት

ቃል ጣዕሟን ማጣጣም ስለቻልክ ማቋረጥ

አያሰኝህም፡፡ አባቶች ቅዱሳንም በአፋቸው ውስጥ

ካለው የጸሎት ጣዕም የተነሳ ጸሎትን አቋርጠው ሌላ

ነገር ለመናገር አይፈቅዱም ነበር፡፡ አንተም በዚህ ስጋዊ

ዐይን በማያየው ልዩ የጸጋ መንገድህ ወደ ፈጣሪህ

ገሥግስና ችግርህን፣ ደስታህን፣ ሁለንተናህን አዋየው፡፡

ጉድለትህን እንዲሞላ ባለማቋረጥ ጠይቀው፣

የምትሻውን እንደፈቃዱ የጠየከውን ሁሉ ይዘህ

ትገኛለህ።

እንድንፀልይ የፈቀደልን አምላክ የተመሰገነ

ይሁን!!

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

አይሰው

እቴጌ ጣይቱ ብጡል (ብርሀን ዘ ኢትዮጵያ)

ደራሲ ዶ/ር ሀዲስ ዓለማየሁ (ሃዲስ ኣለማየሁ)