ጦርነት
ጦርነት ቀፋፊና አጥፊ ነገር ነው! ለአሸናፊም ተሸናፊም
ጦርነት ቀፋፊ ነገር ነው! ማንም ኢትዮጵያዊ መሞት
አይፈልግም፣ ማንም ኢትዮጵያዊ አካሉ ጎድሎ መኖር
አይፈልግም፣ ማንም ኢትዮጵያዊ በጥይትና ፈንጅ
የተቦጫጫቀ የሰው ልጅ አካል አእምሮው ውስጥ
አስቀምጦ እድሜ ልኩን በመጥፎ ትዝታ መኖር
አይፈለግም…. ማንም ልጅ ወላጆቹን፣ ማንም ወላጅ
ልጆቹን፣ የትኛዋም ሚስት ባሏን የትኛውም ማህበረሰብ
ያሳደጋቸውን ልጆቹን ገብሮ እድሜ ልኩን ፎቷቸውን እያየ
በሀዘን መቆራመት አይፈልግም! ማንም!! ጥቁር ታሪክ አለን!
ይሄን መራር ፅዋ ስንጎነጭ የኖርን ህዝቦች ነንና ምሬቱ ገና
ከህሊናችን አልደበዘዘም ! ምድራችን ላይ የፈሰሰው ደም ገና
ወደአፈር አልሰረገም! የጦርነትን አስከፊ ገፅታ ለመናገር
የታሪክ ክርታሳችንን አንድ ገፅ እንኳን ወደኋላ መግለጥ
አይጠበቅብንም ገና እዛው ገፅ ላይ ሁነን ሌላ የሰላም ገፅ
ለመፃፍ እየታገልን ያለን ህዝቦች ነን!
ግን ደግሞ ሌላ አገር የለንም!!
ከነድህነታችን ከነኋላ ቀርነታችን፣ ከነደስታና ሀዘናችን በሆነው
ልክ ተቀብላ የምታኖር ብቸኛ አገር ይችው ኢትዮጵያ ብቻ ናት!
ውስጧ ሁነን እየተነጫነጭንም ቢሆን የምንወዳት፣ ሩቅ
ሁነን እንደተስፋ ምድር የምናልማት ….ይችው ኢትዮጵያ ብቻ
ናት ያለችን! ሌላ አገር የለንም! ሀገሬ ወንዜ የምንለው ዘፈን
ለማሳመር አይደለም …በሰላም ቀን የተዳፈነ የሚመስል ፣
በምሬታችን ብዛት የጠፋ የተዘናጋ የሚመስል የነፍስ ፍቅር
ያስያዘን ሌላ አገር በምድር ላይ የለም!የትም ብንሰደድ
በየትኛውም ቋንቋና ስልጣኔ ዜግነት ጭምር ብንሸፋፈን
የልባችን ሙዳይ ሲከፈት ተሸክመናት የምንጓዘው አንዲት
አገር ብቻ አለችን ….ኢትዮጵያ! ሌላ አገር የለንም!!
ምክንያትህ ምንም ይሁን ይችን አገር ስትነካ በራስህ ላይ
ሞት አውጀሀል!
የኢትዮጵያዊያን ቁጣ የኢትዮጵያዊያን እልህ እና
ለመሰዋእትነት መዘጋጀት ሚስጥር ሌላ አይደለም… አገር
ስትነካ ‹‹የራሷ ጉዳይ›› እንል ዘንድ፣ ‹‹ምናገባን›› እንል
ዘንድ… ‹‹እዛው የበሉት ይዋጣላቸው›› እንል ዘንድ …. ሌላ
አገር የለንም ! ለነፍሳችንም ለስጋችንም በወርድና ቁመቷ ፣
በባህል ወግና ስነልቦና ተሰርታ የተሰጠችን ብቸኛ አገር
ይችው ኢትዮጵያ ብቻ ናት! ሌላ አገር የለንም ! እንኳን ህሊና
ያለው ስለነፃነት ጠንቅቆ የሚያውቅ ህዝብ ይቅርና እቤትህ
ያሳደካትን ድመት በርና መስኮት ዘግተህ ልግረፍሽ ብትላት
ጥፍሯን መዛ ወደነብርነት መቀየሯ አይቀርም …ያኔ የግፍ
ብትር በትዕቢት ያነሳህበትን ቀን እድሜ ልክህን ትረግማለህ!
ያ የተመዘዘ ጥፍር በትዛዝም በልምምጥም አይመለስም!
የኢትዮጵያ ህዝብ እንደሚባለው ጦረኛ አይደለም… ነፍጥ
መዞ አላፊ አግዳሚ ላይ የሚተኩስ ግፈኛ አይደለም!
የጀግንነቱም የጦረኝነቱም ዋና መነሻ አንድና አንድ ነው
….ሌላ አገር የለውም! ርስቱ ኢትዮጵያ ብቻ ናት ! ኢትዮጵያዊ
በአገሩ ጉዳይ ሰይጣን ሁነህ ብትመጣበት ቀንዳም ሰይጣን
ሁኖ ይጠብቀሃል …እሳት ሁነህ አገሩን ልታቃጥል ከመጣህ
ገሀነም ሁኖ ይጠብቅሃል ፣ ወንዝ ሁነህ እየጎረፍክ
ብትመጣበት ውቅያኖስ ሁኖ ይጠብቀሃል! የምንሞትለት
ምቾት … አካል የሚጎድልለት ስርዓት ኖሮን አያውቅም!
ኢትዮጵያዊ ለስርዓት አይዋጋም !ስርዓቱ እያፈነው ስርዓቱ
እየገደለው ኑሮውን ሲኦል እያደረገበት እንኳን እንኳን አገር
ሲነካ ከበደሉ በላይ የአገሩ መደፈር የሚያብከነክነውና
የሚያስቀድመው፣ የምንሞተው፣ የምንቆስለው ከበደል ሁሉ
በላይ አሻግረን ለምናያት አንዲት ኢትዮጵያ ብቻ ስለሆነ ነው!
ሌላ አገር የለንም!
አውቀህም ይሁን በስህተት፣ ሰይጣን አሳስቶህም ይሁን
ትእቢትህ ገፍቶህ ይችን አማራጭ የሌላት የነፍሳችንን
ሳንዱቅ የነካህ ቀን…. የድመቷ ታሪክ ነው የሚከሰተው!
ደመነፍሳዊ አገራችንን የመከላከል ህልውናችንን
የማስጠበቅ ቁጣ ከነፍሳችን ሰገባ ተመዞ ይወጣል …ያኔ
ማንም ስለቱን ቀና ብሎ የሚያይበት ወኔ አይኖረውም! ከዛ
በኋላ መተንኮስህ እስኪፀፅትህ ቁጣውን አታቆመውም!
እንኳን የተነኮስክ አንተ ቀርቶ እራሱ ግፍ በዝቶበት የተነሳው
ኢትዮጵያዊ ራሱን አያቆመውም! ምክንያቱም ወደፊት ይሁን
ወደኋላ፣ ወደግራ ይሁን ወደቀኝ… ኢትዮጵያዊ ሌላ አገር
የለውም! ሌላ አገር የለንም!
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ