ነባሩ

 ነባሩን የኢትዮጵያ ማኅበረ ፖለቲካዊ አንብሮ ጥላሸት በመቀባት “ለውጥ” ለማምጣት የታገለው ያ ትውልድ፣ካበጀው ይልቅ የፈጀው አያሌ መኾኑን ቆጥሮ መድረስ አያዳግትም፡፡ ኢትዮጵያችን ዳግም የታነጸችበትን የሃገረ መንግሥት ምሥረታ ሂደት የተለየ ቀመርና መስፈርት አበጅቶ ከማነወር፣ ወሰንና ወደር አልባ የጭቆና ሀቲቶችን በመደርደር ትናንትን በጽልመት እስከመሞሸር ትውልዱ ያልሞከረው አልነበረም፡፡ በዚህ ብቻ ግን አላበቃም፡፡ የኢትዮጵያውያንን ዘመናት የተሻገረ የአንድነትና 

የውሕደት ታሪክ ወደጎን በመግፋትም “ጨቋኝ” እና “ተጨቋኝ” ፈጥሮ ማቆሚያ ወደሌለው ግጭትና ቀውስ ለመውሰድ ሞክሯል፤በዚህም ሳቢያ ያልፈበረከው የሀሰት ተረክ ያልወጠነው የፍጅት ተረት አልነበረም፡፡ በዚህ ስሁት መስመር ውስጥ ደግሞ ከሻዕቢያ እስከ ህወሓት፤ ከኦነግ እስከ ኦብነግ ቀዳሚ ሰልፈኞች ኾነው መጥተዋል፣አንዳንዶቹም አልፈዋል ፤ ጥቂቶቹም እያለፉ ነው፤በተለይም ደግሞ ድኅረ 1983 በፖለቲካው መድረክ አሸናፊ ኾኖ የወጣው ህወሓት በአፋአዊነት ይራመድ የነበረውን አቋም ወደገዢ ዕሳቤነት ለመለወጥ የሄደበት ርቀት አዳዲስ ችግሮች እንዲወለዱ መግፍኤ ኾኗል፡፡በዚህም ሳቢያ እንግዳ የኾኑ የፖለቲካ ጠባያት ክሱት ሲኾኑ ታዝበናል፡፡ አብሮ የመኖርም ይኹን የመቀጠል ዕጣችን ላይ ትልልቅ ጋሬጣዎች ሲዘነጠፉም ለማየት በቅተናል፡፡ ለዚህ ነው፣ በኢትዮጵያችን የዛሬ እውነታ ውስጥ ህወሓት የችግሮቹ የጡት አባት ከመኾን የዘለለ ሚና የለውም ለማለት የምንደፍረው፡፡ የህወሓት ሕልውና መጥፋት 

ኢትዮጵያ የተጣቧት ችግሮች እንዲቀንሱ ያለው ፋይዳ ትልቅ ቢኾንም የነገሮች ማሳረጊያ ሊኾን ግን አይችልም፡፡ ህወሓት በማኅበረ ፖለቲካችን ውስጥ ያነበራቸው ዕሳቤዎች፣ መዋቅሮች ናሕገ መንግሥታዊ ደገፎች የድርጅቱን ሕጋዊ ሰውነት በማክሰም ብቻ የሚጠፉ አድርጎ ማሰብም ሲበዛ ተላላነት ነው፡፡ 

ድርጅቱ ቆሞ በሰደፉ፣ ሞቶ በሰንኮፉ ማጋደል የሚያስችሉ አደገኛ ሽብልቆችን የቀረቀረባቸው መታጠፊያዎች አሉ፡፡ መንግሥት በድርጅቱ ላይ እየወሰደ ያለው ሕግን የማስከበር ዘመቻ ውጤቱ ምሉዕ የሚኾነውም እነኚህን ቀስቶች በወግ በወጉ መንቀል ሲችል ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ዓይኑን አፍጥጦና ጥርሱን አግጥጦ የሚታየው ዜጋ ጠል ፖሊሲ እልባት የሚያገኝበትን መንገድ መፈለግ ተገቢ ይኾናል፡

፡ ይኽ ደግሞ “ታቦት” ኾኖ የኖረውን ሕገ መንግሥት ጠልቆ 

ከመፈተሽ ይጀምራል፡፡ሲቀጥል ደግሞ ለዜጎች ባይተዋርነት ታህታይ ምንጭ 

የኾነውን አስተዳደራዊ መዋቅር መከለስ ለነገ የሚባል አጣዳፊ ሥራ አይደለም፡፡ የሃያ ሰባት ዓመታቱን የዜጎች ዕልቆ ቢስ 

ፍዳና መከራ አስቀምጠን ያለፉትን ኹለት ዓመታት እውነታ 

ብንገመግም እንኳን ዘውግን ማዕከል ያደረገው አስተዳደር በዚሁ ከቀጠለ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ተጨማሪ ሰቆቃ ከመስፈር 

የሚዘልል ዓላማ እንደሌለው መረዳት እንችላለን፡፡ መንግሥት 

ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የመጪው ዘመን አሸናፊ ሀቆች 

እንዲኾኑ ቁርጠኝነቱ ካለው፣ ህወሓት ወለድ ሕማማት በመሉ 

ተሻጋሪና ተንከባላይ ዕዳ ኾነው የቀጣዩ ትውልድ የጠብና የንትርክ አጀንዳነታቸው እንዲያበቃ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በጉዳዮቹ ላይ መፍትሔ ማስቀመጥ ይጠበቅበታል፡፡ 

የባሕልና የቋንቋ ልይይቶች የኢትዮጵያዊያን ጌጦች እንጂ 

መጠፋፊያ አለመኾነቸውን ፍትሓዊ መልስ በመስጠት የግጭት ነጋዴዎችን ሕልም ማምከን ይኖርበታል፡፡ ኢትዮጵያ ከዘመን 

አመጣሽ ሕገ መንግሥትም ኾነ መዋቅር በላይ መኾኗንም 

በተጨባጭ እርምጃ ማሳየት ይገባዋል፤በህወሓት ብቻሳይኾን 

በእርሱ ብቃይ አስተሳሰቦች ላይ ሙሉ ድል መጎናጸፍ የሚቻለውም ይኽ ሲኾን ብቻ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ያለው መንገድ “አለባብሰው ቢያርሱ…” እንዲሉ አዙሪቱን ከመድገም፣ ድጡን ማጥ ከማድረግ የሚሻል አይኾንም፡፡ በትውልድ ነገ ላይ ታሪካዊ ስህተት መፈጸምም ይኾናል፡፡ ለዚህም ሲባል መንግሥት አሁን ለገባንበት ችግር ምንጭ በኾነው ድርጅት ላይ ከሚወስደው እርምጃ ጎን ለጎን ሕጋዊና መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት ተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚጀምርበት ቀን ነገ ሳይኾን ዛሬ መኾኑን ነው ።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

አይሰው

እቴጌ ጣይቱ ብጡል (ብርሀን ዘ ኢትዮጵያ)